ኢትዮጵያ በመጪው መጋቢት ወር መጨረሻ 4ኛውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ታካሂዳለች፡፡ለእዚህም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ከብሄራዊ ፕላን ኮሚሽንና ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
መረጃዎቹ እንደሚገለጹት፤ ቆጠራው እንዳለፉት ጊዜያት ሳይሆን በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በሁለቱም የከተማ አስተዳደሮች የሚካሄድ ይሆናል፡፡ በአምስት የክልል ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ ፣ በኦሮምኛ ፣ በትግርኛ፣ በሶማሊኛ፣ በአፋርኛ የሚካሄድም ይሆናል፡፡
ለቆጠራው ወደ 200ሺ የሚሆኑ የቆጠራ ጣቢያዎች፣ 152 ሺ የቆጠራ ማእከላት የተዘጋጁ ሲሆን፤ ለእነዚህም 152 ሺ ባለሙያዎች እና 38ሺ ተቆጣጣሪዎች ይሰማራሉ፣ 180 ሺ ታብሌት ኮምፒውተሮች እንዲሁም ኤሌክትሪክ ቢጠፋ በሚልም ተንቀሳቃሽ ቻርጀሮች ተዘጋጅተዋል፡፡ ቆጠራው በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደግፎ የሚካሄድ ሲሆን፣ ይህም በቴክኖሎጂው በመጠቀም ቆጠራውን ባካሄዱ ሀገሮች ተሞክሮ ላይ ተመስርቶ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
ቴክኖሎጂው ተአማኒነት ያለው ቆጠራ በመላ ሀገሪቱ ለማካሄድ እንደሚያስችል የታመነበት ሲሆን፣ በዚህም ባለፉት ቆጠራዎች የታዩ ቅሬታዎች በድጋሚ ሊከሰቱ የሚችሉበት እድል እንዳይኖር የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል ፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ህዝብ የተመለከቱ መረጃዎች የሚሰበሰቡበት ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ቢያንስ በየአስር ዓመቱ እንዲካሄድም ይመክራል፡፡ ቆጠራው ምን ያህል ህዝብ አለ የሚለው ጥያቄ ብቻ የሚመለስበት ብቻ ሳይሆን በርካታ መረጃዎች የሚጠናከሩበትም ነው፡፡
የህዝብ ቁጥርን ማወቅ የቆጠራው ዋናው አስፈላጊ ጉዳይ ተደርጎ ቢወሰድም፣ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው ህዝብ ምን ያህል ስለመሆኑ፣ ስለዕድሜ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ የመኖሪያ ቤት፣ ወዘተ ዝርዝር መረጃ የሚሰበሰብበት ነው፡፡ ዘመናዊ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ መረጃ ለምርምር ፣ ለንግድ ሥራ፣ ለእቅድ፣ ወዘተ ይጠቅማል፡፡ በምርጫ ወቅትም የህዝብን ወኪሎች ለመለየት ያገለግላል፡፡
ሀገሪቱ ቆጠራውን ካካሄደች ከአስር ዓመት በላይ ሆኗታል፡፡ ቆጠራው ከጸጥታና ደህንነት ችግር ጋር በተያያዘ ከአንዴም ሁለቴ መተላለፉ ይታወሳል፡፡ አሁንም አንዳንድ ወገኖች ሰላምና መረጋጋት በሀገሪቱ እንደሌለ በመግለጽ በዚህ የፖለቲካና ደህንነት ችግር ወቅት ቆጠራ ማካሄድ አደጋ እንዳለው ቢገልጹም መንግሥት አሁን አንጻራዊ ሰላም እና ደህንነት መኖሩን በመግለጽ ቆጠራውን በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቅቋል፡፡
የህዝብና ቤቶች ቆጠራ በየአስር ዓመቱ መካሄድ ያለበት ከመሆኑ አኳያ እንዲሁም በሀገራችን ቆጠራው ከተካሄደ ከአስር ዓመት በላይ መሆኑ በራሱ የቆጠራውን መካሄድ ወሳኝ ያደርጉታል፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ወቅታዊና ትክክለኛ ነው፡፡
እንደሚታወቅው፤ ለሀገራችንም የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ፋይዳ ብዙ ነው፡፡ ሀገራዊ እቅድ የሚዘጋጀው፣ ትምህርቱ የሚስፋፋው፣ ጤናው የሚጠበቀው፣ ልማቱ የሚካሄደው ወዘተ፣ በህዝብ እና ቤቶች ቆጠራ መረጃዎች ላይ በመመስረት ነው፡፡ ምርጫ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲካሄድ፣ የማንነት ጥያቄዎች ሊመለሱ የሚችሉት፣ የህዝብ ውክልናዎች የሚታወቁት በዚሁ መረጃ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ሀገሪቱ በ2012 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ታካሂዳለች፡፡ በዚህ ምርጫ የህዝብ ወኪሎችን ለማወቅ፣ የህዝቡን ዕድሜ ለመለየት፣ ድምጽ ለመስጠት የሚመዘገበው በምርጫው ሂደት ወቅት ሊታወቅ ቢችልም አጠቃላይ የህዝቡ ብዛት ምን ያህል ነው የሚለውን ለመመለስ በግምት መስራት አያስፈልግም፤ በመሆኑም ቆጠራው መካሄድ ይኖርበታል፡፡የቆጠራው ውጤት ሀገሪቱ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች የምታከናውናቸውን ተግባሮች ለማቀድ ይጠቅማታል፡፡ይህ ከህዝብ ብዛት ባሻገር በርካታ መረጃዎች የሚሰበሰቡበት ቆጠራ፣ በአግባቡ ከተካሄደ የህዝብን ጥያቄ የሚመልሱ እቅዶችን ለማዘጋጀት ፋይዳው ከፍተኛ ይሆናል፡፡
ለክልሎች እና ለከተማ አስተዳደሮች በጀት የሚመደበውም በህዝብ ብዛት ላይ ተመስርቶ እንደመሆኑም የህዝቡ ብዛት ስንት እንደደረሰ ማወቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ውስን የሆነው የሀገሪቱ ሀብት በግምት ላይ ወይም ወቅታዊ ባልሆነ መረጃ ላይ ተመስርቶ መከፋፈል የለበትም፡፡የቆጠራው መካሄድ ለዚህ ወሳኝ ይሆናል፡፡፣
የቆጠራው መረጃዎች ክልሎች እና ህዝቦች በትምህርት፣ በጤና በመሰረተ ልማት፣ በመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ ወዘተ ያሉበትን ደረጃ የሚያመለክቱ እንደመሆናቸው፣ ክልሎች መደገፍ ባለባቸው ላይ እንዲደገፉ ለማድረግ የመረጃዎቹ ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ሀገራችን ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ ራእይ ሰንቃ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገርም እንዲሁ እየሠራች ነው፡፡ እነዚህ ሥራዎች በራሳቸው ወቅታዊ መረጃ ይፈልጋሉ፡፡ ለማን እንዴት መሥራት እንዳለብን ለማወቅ የቆጠራው መረጃዎች ወሳኝ ናቸው፡፡
ይህም የቆጠራው መረጃዎች የልማት ወሳኝ ግብአት መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ እነዚህ መረጃዎች ይሰበሰቡ ዘንድ ሁሉም ወገን መተባበር እንዲሁም ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ቆጠራው በተያዘለት መርሀ ግብር ይካሄድ ዘንድ የመገናኛ ብዙኃን በቆጠራው ፋይዳ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር ማከናወን ይኖርባቸዋል፡፡ ከማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እንዲሁም ብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን መረጃዎችን በማሰባሰብ በተለያዩ መንገዶች ለህዝብ እንዲደርሱ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የተለያዩ ዘርፎች ባለሙያዎች በህዝብና ቤቶች ቆጠራ መረጃዎች ፋይዳ ላይ ትንታኔዎችንና ማብራሪያዎችን እንዲሰጡ በማድረግ ግንዛቤ የማስፋቱን ተግባር አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡
የቆጠራው መረጃዎች የማያስፈልጉበት ቦታ እንደማይኖር ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ወገን ባለድርሻ አካል መሆኑን አውቆ ቆጠራው እንዲሳካ ከመንግሥት ጎን በመቆም ለስኬቱ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ህዝቡም ተገቢውን መረጃ በመስጠት መተባበር ይጠበቅበታል፡፡ ይህም ለቆጠራው ስኬት ከግለሰብ አንስቶ ሁሉም ወገን ኃላፊነት እንዳለበት ያመለክታል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011