
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደችው 6ተኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርኢትና ኮንፍረንስ ‹‹የበለጸገ ኮሜሳ ለሥርዓተ-ጾታ አካታችነት ምላሽ ሰጪ አህጉራዊ ውህደት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና በአረንጓዴ ኢንቨስትመንቶች፣ የእሴት ሰንሰለቶች፣ ቱሪዝምና ማዕድን ለመክፈት›› በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። ይህ ኹነት የ21 አባል ሀገራት ከ250 በላይ ሥራዎቻቸውን ይዘው የቀረቡበት ሲሆን ኢትዮጵያም ይህንን ኹነት በድምቀት አስተናግዳ እንግዶቿን ሸኝታለች።
የንግድ ትርኢቱን መርቀው የከፈቱት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚንስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በንግዱ ዘርፍ ላይ ሴቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ እምቅ አቅምን መግለጥ ብቻ ሳይሆን የልማት ሕጎችን እንደገና እንደ መጻፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የነጋዴ ሴቶች ፌዴሬሽን ኮሜሳ መሥራች አባል እንደ መሆኗ የኮሜሳ ቁልፍ አላማዎችን በመደገፍ ይህንን ኹነት አስተናግዳለች በማለት ገልጸው እንደ ሀገር ይህን ኹነት ስናስተናግድ ቃላችንን ወደ ተግባር ለመቀየር በሀገር አቀፍ፣ በአህጉር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁርጠኛ ነን ሲሉ ገልጸዋል። ካሳሁን (ዶ/ር) በንግግራቸው ሴቶች ለረጅም ጊዜ በፋይናንስ ውስንነት፣ በአስተዳደር ችግሮች እና በተጨናነቀ መሠረተ ልማቶች እና በፖሊሲዎች ውስጥ ሆነው የንግድ ሥርዓት ሲያከናውኑ በመቆየታቸውን ያላቸውን አቅም በአግባቡ አልታየም ሲሉ ተናግረዋል። የቀጣዩዋ አፍሪካ አላማም ንግድን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ሁሉን አቀፍ ንግድን ማረጋገጥ እና የጾታ እኩልነት የጎንዮሽ አጀንዳ ሳይሆን ለለውጥ እንደ ዋና ሞተር ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ሚንስትሩ ገልጸዋል።
እንደ ካሳሁን (ዶ/ር) ገለጻ ኢትዮጵያ በእርስ በርስ ትስስር እንዲሁም አብሮ በመሥራት የምታምን ሲሆን ፤ በሃሳብ ደረጃ ያለ ሳይሆን ተግባራዊ የሆነ የጋራ የብልፅግና መንገድ ነው። የተቀናጀ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) እንዲሁም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ሥርዓት እውን ለማድረግ የሴቶች ሙሉ ተሳትፎ ላይ መገንባት አለባቸው ብለን እናምናለን ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ በርካታ አፍሪካውያን የተሳተፉበት የንግድ ትርኢት ላይ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ሥራዎቻቸውን ይዘው የቀረቡበት እና ከሌሎች በንግዱ ዘርፍ የተሠማሩ እና ረጅም ልምድ ያላቸው ሴቶች ጋር የልምድ ልውውጥ አድርገዋል። ወጣቶች በልቦናቸውን ያለው ሃሳብ ወደ ሥራ መቀየር እና ትልቅ ደረጃ ላይ ማድረስ እንጂ በሃሳብ ደረጃ መቀመጥ ብቻውን የሚስማሙበት ጉዳይ አይደለም። በዚህ የንግድ ትርኢት ላይ ሃሳባቸውን ወደ ሥራ በመቀየር እና አገልግሎት በመስጠት በትንሹ የጀመሩትን የሥራ ፈጠራ በሀገራቸው አልፈው አፍሪካ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅ ተቋምን መገንባትን ህልማቸው ያደረጉ ወጣቶች ተገኝተዋል።
በንግድ ትርኢቱ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር አምባሳደር ሳልማ ማሊካ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ሴቶችንና ወጣቶችን ያሳተፈ አህጉራዊ ውህደት ውጤታማ መሆኑ ጥርጥር የለውም ያሉ ሲሆን የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የኮሜሳ አባል ሀገሮች የበለጠ ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባም አመልክተዋል። አምባሳደሯ በንግግራቸው አጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት የሴቶች እና ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም ተሳታፊነት የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በሥራዋ በርካታ ሴት ጠንካራ ገበሬዎችን የምትወክል እና ሥራዎቿን በተመለከተ በግል ማህበራዊ ገጹዋ ላይ በምታጋራቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች በርካታ ተከታዮችን አፍርታለች። በዚህም በምትሠራቸው የግብርና ሥራዎች በርካታ ወጣቶች ወደ ዘርፉ ገብተው እንዲሠሩ መነሳሳትን ፈጥራለች።
በቅርቡም የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን እንድታገለግል ተመርጣለች። በረከት ገበሬዋ፤ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደችው 6ተኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ(ኮሜሳ) ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርኢትና ኮንፍረንስን በተሳካ ሁኔታ ለማዘጋጀት ተራውን በርካታ የሀገሯ ሴቶችን እንዴት በዚህ መድረክ ማሳተፍ ይችላል የሚለውን ስታቅድ መቆየቷን አስታውሳለች።
የኢትዮጵያ ሴት ነጋዴዎች ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን ኃላፊነቱን ከተረከበች በኋላም ይህንን አህጉር አቀፍ የሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርኢት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሴቶችን ባሕላቸውን፣ ሥራዎቻቸውንና አቅማቸውን እንዲስተዋውቁ ተደርጓል በማለት ገልጻለች። በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አቅም ያነሳቸውን ሴቶች በማበረታታት በሰው ሠራሽም ሆነ በተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ወደኋላ የቀሩ ሴቶችን የሚያስፈልጋቸውን ድጋፎች በማድረግ በንግድ ትርኢቱ ሥራዎቻቸውን ይዘው እንዲሳተፉ ማድረግ ተችሏል።
የንግድ ትርኢቱ በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ በኤክስፖርት ደረጃ ምርታቸውን ይዘው ነገር ግን እድል ባለማግኘት በንግዱ ዘርፍ የተሠማሩ ሴቶችን ከሌሎች ነጋዴዎች ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ እድል የፈጠረ ነው ስትል ገልጻለች። በዚህም በተለያዩ ዘርፎች ሥራዎቻቸውን ለማሳደግ የሚጥሩ ወጣቶችን ለማሳተፍ እድል የፈጠረ ሲሆን ከሌሎች ልምድ ካላቸው ነጋዴዎች ጋርም ጥሩ የልምድ ልውውጥ መድረክ እንደነበር ገልጻለች።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀችው በዚህ የሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርኢት የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበራት በስሩ ባሉ የክልል ማህበር የተወጣጡ ሴቶችን በመልመል ባሕላዊ ምግብና አልባሳትን፣ የእደ-ጥበብ ውጤቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች፣ ቡና አምራቾች ሥራዎቻቸውን ይዘው ቀርበዋል።
ፀሐይ ብዙሃኔ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን በመወከል የጉራጌ ፣ ስልጤና እና ሀላባ ማኅበረሰብ አልባሳት መገልገያ እቃዎች እንዲሁም በክልሉ በስፋት የሚገኙ እና የሚታወቁባቸው የባልትና ውጤቶች ይዛ ቀርባለች። ፀሐይ ይህንን እድል በክልሎች በተቋቋሙ የሴት ነጋዴ ማህበር አማካኝነት በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት መገኘቷን ገልጻለች። ኹነቱ በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ እንደ ሀገር መልካም ተሞክሮ ነው በማለት የምትገልጸው ፀሐይ በዚህ ኹነት የመጀመሪያ ተሳታፊ ሆና በመቅረቧም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ጋር ልምድ ለመለዋወጥ ለሴት ነጋዴዎች እድሉ መሰጠቱ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጻለች ።
ሴቶች በባህሪያቸው ትኩረት ሰጥተው አንድን ሥራ የሚያከናውኑ በመሆናቸው በሚሰማሩበት ማንኛውም ዘርፍ ስኬታማ መሆን ይችላሉ የምትለው ፀሐይ የተለያዩ ባሕላዊ ምግቦችን እና ልብሶችን ወደ ገበያ ይዛ ስትቀርብ ወላጅ እናቷ ከጀርባ ሆነው እንደሚያግዟትም ትናገራለች። መሰል የንግድ ትርኢቶች እና የሥራ ፈጣሪዎችን አቅም የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎች ከሌሎች ተጠቃሚዎች ጋርም ሆነ የንግድ ሥርዓት ጋር ያላቸውን ግንኙነቶች የሚያጠናክሩ መድረኮች እንዲሁም ሥራዎቻቸውን የሚያስተዋውቁባቸው የንግድ ትርኢቶች መስፋፋት እንደሚገባቸው ጠቁማለች።
በስድስተኛው የሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርኢት ላይ ሙሉ ለሙሉ በእጅ የሚሠሩ የእደ-ጥበብ ውጤቶችን ይዛ የቀረበችው ዛምቢያዊቷ ወጣት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ ቢዝነሷን ለማሳደግ ጥሩ እድል እንደፈጠረላት ገልጻለች። ወጣት ካሊንጋ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣች ሲሆን በዛምቢያ የሚገኘው የኮሜሳ አካል አማካኝነት እድሉን እንዳገኘችም ትገልጻለች። ዲዛይነር ካሊንጋ ወጣት እና ወደዚህ ሥራ ከገባች ገና አንድ ዓመት ሲሆን በዚህ የንግድ ትርኢት ላይ መገኘቷ በዘርፉ ከተሠማሩ ሥራ ፈጣሪዎች የተገኙበት ይህ የንግድ ትርኢት አፍሪካውያን ጋር ለመተዋወቅ እና ልምድ ለመለዋወጥ እድል ያገኘችበት መሆኑን ትገልጻለች።
ወጣት ካሊንጋ የእደ-ጥበብ ውጤት የሆኑ ቦርሳዎችን፣ ቁልፍ መያዣዎችን እና ሌሎች ምርቶቿን ይዛ የቀረበች ሲሆን የራሳቸውን ሥራ ይዘው ለሚገቡ ወጣቶች ማበረታቻ እና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አስታውሳ ወደፊት በዓለም ላይ በፋሽን ኢንዱስትሪው እጅግ ታዋቂ ከሆኑ ብራንዶች እኩል መጠራት የሚችል ስሟን መገንባት የወደፊት ህልሟ እንደሆነ ትናገራለች።
ሌላኛዋ በንግድ ትርኢቱ ላይ የዲዛይን ሥራዎቿ ይዛ የቀረበችው ወጣት ዲዛይነር ሰብሪን አብዱራህማን ናት። ዲዛይነር ሰብሪን የመጣችው ከሐረሪ ክልል ሲሆን የሐረሪ ክልልን ባሕል የሚያስተዋውቁ አልባሳት፣ የጌጣጌጥ ሥራዎች ይዛ በመቅረብ እና ራሷም በዚህ አለባበስ አጊጣ ሥራዎቿን በማስተዋወቅ በቦታው የተሳተፉ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የትርኢቱ ተሳታፊዎችን ቀልብ መሳብ ችላለች። ሰብሪን ወጣት እንደ መሆኗ የሐረር ባሕላዊ ልብሶችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ዲዛይን የምታደርግ ሲሆን ሁለት ዓመት ያህል ጊዜ በሥራዋ ቆይታለች። ሰብሪን የተለያዩ ምርቶችን ይዘው የቀረቡ ዲዛይነሮች ጋር መተዋወቅ መቻሏን ገልጻ ከእነዚህ ወጣት ዲዛይነሮች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እና ለገበያ ትስስር ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን አንስታለች።
ለሶስት ቀናት በቆየው በዚህ የንግድ ትርኢት የተለያዩ ወጣት ሴቶች እና ልምድ ያላቸው ነጋዴዎች ሥራዎቻቸውን ይዘው ቀርበዋል። በዚህም አዳዲስ የሥራ ሃሳቦችን ለማስተዋወቅ ወደገበያው ይዘው የቀረቡ ተሳታፊዎችን የተመለከትን ሲሆን ከዛምቢያ፣ ማዳጋስካር፣ ቡሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ ጁቡቲ 21 አባል ሀገራት እና 250 በላይ ተሳታፊዎች ሥራዎቻቸውን ይዘው የቀረቡበት ነው።
ኢትዮጵያ ባስተናገደችው በዚህ ትርኢት ላይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ፣ በቆዳ ውጤቶች በባልትና፣ በባሕል አልባሳትና ፋሽን ኢንዱስትሪ ላይ የተሠማሩ እንዲሁም አዳዲስ የሥራ ፈጠራዎችን ማለትም ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት የምታስገባቸውን ምርቶች ሊተኩ የሚችሉ የሥራ ሃሳቦችን በማሳያ ደረጃ ይዘው የቀረቡ ወጣት ሴቶች በንግድ ትርኢቱ ላይ ተሳትፈዋል።
መድረኩ ከንግድ ትርኢት እና ከግብይት ባለፈ ሀገራቱ እርስ በርስ ያላቸውን ልምድ ለመለዋወጥ እና ቀጣይ ሥራዎችን በተመለከተ የጋራ ኮንፍረንስ የተካሄደበት ሲሆን ለሀገራችንም ሆነ ለአፍሪካ በንግድ ሥርዓት ውስጥ እድገት ለማምጣት በምታደርገው ጉዞ የራሱ የሆነ ዐሻራን የሚያሳርፍ ነው።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም