
የአውሮፓ ኅብረት በሶሪያ ላይ ጥሏቸው የነበሩትን የምጣኔ ሀብት ማዕቀቦች እንደሚያነሳ አስታውቋል። ኅብረቱ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው በጦርነት የደቀቀችውን ሀገር መልሶ ግንባታ ለማገዝ እንደሆነ ገልጿል። የኅብረቱ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ካያ ካላስ፣ ከኅብረቱ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በብራሰልስ ከተወያዩ በኋላ ‹‹ሶሪያውያን ሰላማዊ፣ አዲስና አካታች የሆነች ሶሪያን እንዲገነቡ ማገዝ እንፈልጋለን። የአውሮፓ ኅብረት ባለፉት 14 የጦርነት ዓመታት ሁሉ ከሶሪያውያን ጎን ነበር፤አሁንም ይቀጥላል›› ብለዋል።
የሶሪያ የሽግግር መንግሥት የአውሮፓ ኅብረት በሀገሪቱ ላይ ጥሏቸው የነበሩትን የምጣኔ ሀብት ማዕቀቦች ለማንሳት የወሰደውን ርምጃ አድንቋል። የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ አል-ሻይባኒ የአውሮፓ ኅብረትን አመስግነዋል። የኅብረቱ ውሳኔ የሶሪያን መረጋጋትና ደህንነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
የአልጀዚራው ዘጋቢ ሃሸም አሄልባራ የኅብረቱ ውሳኔ ‹‹እጅግ ወሳኝ›› ለውጥ እንደሆነ ዘግቧል። ኅብረቱ በሶሪያ ላይ ጥሏቸው የነበሩትን ማዕቀቦች ለማንሳት መወሰኑ ኅብረቱ አሁን በሶሪያ ሥልጣን ይዞ ለሚገኘው የሽግግር መንግሥት እውቅና መስጠቱን እንደሚያመለክትም አሄልባራ ገልጿል።
ኅብረቱ በበሺር አል-አሳድ የሥልጣን ዘመን እ.አ.አ በ2012 እና 2013 በሶሪያ ላይ ጥሏቸው የነበሩት ማዕቀቦች በሀገሪቱ የትራንስፖርት፣ የኃይልና የባንክ ዘርፎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። ማዕቀቦቹ የሶሪያ ባንኮች ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ሥርዓት ግንኙነት እንዳይኖራቸው እና የሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ሀብቶች እንዲታገዱ አድርገው ቆይተዋል።
የሰላማዊ ዜጎችን ተቃውሞ ለማፈን ሊውሉ የሚችሉ የጦር መሳሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ግዢ የሚከለክሉት ማዕቀቦች ግን ባሉበት እንደሚቆዩ ተገልጿል። ከእዚህ በተጨማሪም ባለፈው መጋቢት ወር በአልዋይት ማኅበረሰብ አባላት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ኅብረቱ በሰላማዊ ዜጎች፣ በተለይም ጥቂት ቁጥር ባላቸው ማኅበረሰቦች ላይ ጥቃቶች እንዲፈፀሙ ያደረጉ አካላት ላይ ማዕቀቦችን የመጣል እቅድ እንዳለው የኅብረቱ ዲፕሎማቶች ተናግረዋል።
የሶሪያ ሽግግር መንግሥት በቁጥር ጥቂት የሆኑ ማኅበረሰቦችን መብት ለማክበርና ወደ ዲሞክራሲ ሥርዓት ለመሸጋገር የገባውን ቃል የማያከብር ከሆነ፣ ማዕቀቦቹ ወደ ቦታቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ኅብረቱ አስጠንቅቋል። የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሐን ቫደፉል የአውሮፓ ኅብረት ከሶሪያ ጋር አዲስ ግንኙነት መመስረት እንደሚፈልግ ገልጸው፤ ኅብረቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያካተተ የሶሪያ መልሶ ግንባታ ተግባራዊ ይደረጋል የሚል ተስፋ እንዳለው ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ባለፈው የካቲት ወርም ሀገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት በሶሪያ ወሳኝ የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ላይ ጥሏቸው ከነበሩት ማዕቀቦች መካከል አንዳንዶቹን ማንሳቱን አስታውቆ ነበር። ኅብረቱ ‹‹የሀገሪቱን የዲሞክራሲያ ሥርዓት ሽግግር፣ መረጋጋት፣ መልሶ ግንባታ እና ኢኮኖሚያዊ ማንሰራራት ለማገዝ›› በነዳጅ ዘይት፣ በኤሌክትሪክና በትራንስፖርት ዘርፎች ላይ ተጥለው የነበሩ ገደቦችን ማንሳቱን መግለጹ ይታወሳል።
‹‹አዲሱ የሶሪያ አመራር መላው ዓለም፣ በተለይም የአውሮፓ ኅብረት የሚጠብቀውን አካታች የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት ተስፋ ሰጪ ጅምር ካላሳየ ኅብረቱ ማዕቀቦቹን ወደ ቦታቸው በመመለስ አጥፊዎችን ለመቅጣት አያቅማማም›› የሚለው ማስጠንቀቂያም በየካቲቱ የኅብረቱ ውሳኔ ተሰምቶ እንደነበር አይዘነጋም።
ሰሞነኛው የኅብረቱ ውሳኔ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሀገራቸው ቀደም ሲል በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩ ማዕቀቦችን እንደምታነሳ ካስታወቁ ወዲህ የተሰማው ሌላው ታላቅ ርምጃ ነው። ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት እያደረጉ በነበሩበት ወቅት ይህን ውሳኔያቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ፕሬዚዳንቱ በሳዑዲ ዐረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ በተካሄደው የሳዑዲ-አሜሪካ ኢንቨስትመንት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ሶሪያ የተሻለችና ታላቅ ሀገር እንድትሆን ዕድል ለመስጠት ሲባል በሀገሪቱ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች እንዲነሱ ትእዛዝ አስተላልፋለሁ። ማዕቀቦች ዓላማቸውን አሳክተዋል፤ከእዚህ በኋላ አያስፈልጉም። አሁን ሶሪያ ወደ ፊት የምትጓዝበት ጊዜ ነው። ሶሪያን ወደ ሰላምና መረጋጋት እንደሚመልስ ተስፋን የሰነቀ አዲስ መንግሥት አለ” በማለት ተናግረው ነበር።
ከሳዑዲ ዐረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን እና ከቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ይህን ውሳኔ እንዲወስኑ እንዳደረጓቸው የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ አሜሪካ ከሶሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማደስ እንደምትፈልግም ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ፕሬዚዳንቱ እቅዳቸው ገቢራዊ እንዲሆን ለሶሪያ ካቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንጻር ሲመዘን የአውሮፓ ኅብረት ውሳኔ ለሶሪያ መንግሥት ቀላልና የተሻለ ይመስላል። ትራምፕ አሜሪካ በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩትን ማዕቀቦች የምታነሳው የሶሪያ መንግሥት “የአብርሃም ስምምነት”ን በመቀበል ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመረ፣ አሸባሪ ፍልስጤማውያንን ከሀገሩ ካስወጣ እና በሰሜን ምሥራቅ ሶሪያ ለሚገኙ የእስላማዊ መንግሥት (ISIS) ማጎሪያ ማዕከላት ኃላፊነት ከወሰደ እንደሆነ ትራምፕ ከሶሪያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አህመድ አል-ሻራ ጋር በሪያድ ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት ነግረዋቸዋል።
የትራምፕ ውሳኔ ለአሜሪካና ሶሪያ ግንኙነት አስደናቂ ርምጃ ቢሆንም፤ “የአብርሃም ስምምነት”ን ተቀብሎ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመጀመር ጉዳይ ለሶሪያ መንግሥት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ እንደሚሆንበት ተንታኞች ገልጸዋል። በተለይም ሶሪያ “የአብርሃም ስምምነት”ን እንድትቀበልና ከእስራኤል ጋር መልካም ግንኙነት እንድትመሠርት የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ የፍልስጤማውያንን ጥያቄና ጥቅም የሚክድ በመሆኑ ቅድመ ሁኔታው ለዐረባዊቷ ሶሪያ እጅግ ከባድ ጥያቄ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ሶሪያን ለ24 ዓመታት ከመሩት በሺር አል-አሳድ እጅ ሥልጣን ነጥቆ ሀገሪቱን ለማስተዳደር እየሞከረ የሚገኘው የሶሪያ የሽግግር መንግሥት፣ ምዕራባውያን በበሺር አል-አሳድ የሥልጣን ዓመታት በሶሪያ ላይ የጣሏቸውን ማዕቀቦች እንዲያነሱ ደጋግሞ እየጠየቀ ይገኛል። የሽግግር መንግሥቱ ጥያቄም ከሞላ ጎደል ተቀባይነት እያገኘ ይመስላል። ሰሞንኛዎቹ የአሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ውሳኔዎች ይህን እንደሚያሳዩ ተገልጿል። ብሪታኒያ በበኩሏ፤ በ12 የሶሪያ መንግሥት ተቋማት ላይ ጥላቸው የነበሩትን ማዕቀቦች ማንሳቷን ባለፈው ወር አሳውቃ እንደነበር ይታወሳል።
ሶሪያ ለ14 ዓመታት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት አሰቃቂ ውድመትን አስተናግዳለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ ሶሪያ ከጦርነቱ በፊት ወደነበረችበት የምጣኔ ሀብት ሁኔታ ለመመለስ ከ50 ዓመታት በላይ ይፈጅባታል። የመልሶ ግንባታውን ሥራ ለማፋጠን ብዙ ኢንቨስትመንት ትፈልጋለች። ከአስር ሶሪያውያን መካከል ዘጠኙ በድህነት ውስጥ ይገኛሉ። የሀገሪቱ ጥቅል ሀገራዊ ምርት (GDP) ጦርነቱ ሲጀመር ከነበረው ዋጋ በእጥፍ አሽቆልቁሏል። የሀገሪቱ የሰብዓዊ ልማት አሃዝ እ.አ.አ በ1990 ከተመዘገበው ያነሰ ሆኗል። በ14 ዓመቱ ጦርነት ያጣችው ጥቅል ሀገራዊ ምርትም 800 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል።
የአውሮፓ ኅብረት በሶሪያ ላይ ጥሏቸው የነበሩትን የምጣኔ ሀብት ማዕቀቦች እንደሚያነሳ መወሰኑ በጦርነት ክፉ የተጎዳው የሶሪያ ምጣኔ ሀብት እንዲያንሠራራ ቀላል የማይባል አበርክቶ ሊኖረው እንደሚችል ተገልጿል። የሶሪያ የሽግግር መንግሥት በጦርነት የወደመችውን ሀገር ለመገንባት የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ዲፕሎማሲ የማደስና የማጠንከር ፍላጎት አለው። ሀብታሞቹ የባሕረ ሰላጤው ሀገራትና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በሀገሪቱ የመልሶ ግንባታ ተግባር ላይ ወሳኝ ሚና እንዲኖራቸው ይፈልጋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለሶሪያ መንግሥት ካስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንጻር የአሜሪካ ውሳኔ ገቢራዊ የመሆን ዕድሉ ምን ያህል ነው የሚለው አወዛጋቢ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የአሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ማዕቀቦች ከተነሱ የሶሪያ ምጣኔ ሀብት ከገባበት አዘቅት ወጥቶ እንዲያገግም በማድረግ ረገድ ቀላል የማይባል ድርሻ ይኖራቸዋል። የማዕቀቦቹ መነሳት በማዕቀቦቹ ምክንያት በሶሪያ ከርዳታና ከኢንቨስትመንት ታቅበው የቆዩት ሀብታሞቹ የባሕረ ሰላጤው ሀገራት ለሶሪያ መልሶ ግንባታ በጎ አስተዋጽኦ በሚኖራቸው የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሠማሩ ያስችላቸዋል። አሜሪካና አውሮፓ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው በመሆኑ ማዕቀቦቻቸውን ማንሳታቸው ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ከሶሪያ ጋር የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎችን ለማከናወን ያስችለዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም