ሉዋ – የሲዳማዎች ባሕላዊ መገለጫ

የሲዳማ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆኑ ወንዶች በሕይወታቸው ውስጥ ሦስት ደረጃዎችን ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። እነሱም በሉዋ መሳተፍ፤ መገረዝ እና የሽምግልና ደረጃዎችን መያዝ ናቸው። «ሉዋ» ከብሔሩ ጥንታዊ ባሕላዊ እሴቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ የሲዳማ ብሔረሰብ ተወላጆች ከየጎሳው ተውጣጥተው እና በትውልድ ዑደት ተደራጅተው በማኅበረሰቡ ማህበራዊ፤ አስተዳደራዊ፤ መንፈሳዊ ጉዳዮች የላቀ ተሳትፎ ለማድረግ የሚሰበሰቡበት ባሕላዊ ተቋም ነው።

የሲዳማ ብሔረሰብ የማንነቱም መግለጫ ነው። ብሔረሰቡ አሁን ወደሚኖርበት አካባቢ መጥቶ ከመስፈሩ አስቀድሞ ይገለገልበት የነበረ ባሕላዊ ተቋም እንደሆነ የብሔሩ ተወላጆች ይናገራሉ። ‹‹ውሃን ከጥሩ ነገር ከሥሩ›› እንዲሉት ተረት ተወላጆቹ እንደሚሉት፤ ባሕሉ የራሱ የሆነ ታሪካዊ አጀማመር ያለው ነው። ይህም ጥንት ከብት የሚያግዱ ልጆች ነበሩ። እነዚህ ልጆች ታዲያ ከብት እያገዱ ባሉበት ወቅት ብቸኝነት እንዳይሰማቸው ጊዜያዊ ጎጆ ይሠራሉ። በጎጆውም ከመካከላቸው ታላቅ የሆነውን መሪያቸው ተደርጎ ይሾማል። ተከታዩን ደግሞ ጃለዋ ይሉታል። ከዚያም ቡድን መሪ በማድረግ ይሰይማሉ። ወደዚሁም ምግብ አቅርበው ይመገባሉ። ይሄም አባቶች በእነዚህ ልጆች ድርጊት በብርቱ እንዲሳቡ ያደርጋል። ይወድዱታልም፤ ለምን እኛም ተመሳሳይ ሥርዓት አንፈጥርም በማለት ይስማሙና ፈጥነው አሁን መላው የሲዳማ ተወላጅ እየተገለገለበት የሚገኘውን የአሁኑን «ሉዋ» ተቋም ይፈጥራሉ።

ዓለም አቀፍ ታሪክ ፀሐፊው ብራው ካምፐር ስለአጀማመሩ እንዳለው፤ ሲዳማ በሉዋ ሥርዓት መገልገል የጀመረው በዳዋ ዳብቾ (ቦረና) የሚባል ስፍራ ይኖር በነበረበት ጊዜ ነው። ጥንት ይኖር የነበረው በቀይ ባሕር አካባቢ፤ በአፋር፤ በኤጄርሳ ጎሮ፤ በድሬዳዋ፤ በጎዴ ሲሆን፤ ያኔ ታዲያ ይተዳደር የነበረውም በ “ሀላሌ” መርህ ነበር። ከዚህ አንጻርም አምስቱ የሉዋ ቡድኖችም የተፈጠሩት በደዋ ዳብቾ ይኖር በነበረበት ከ17ኛው ትውልድ በፊት ነው። ይህም ሉዋ ከጠላት በመፋለም ድል ያገኘው ዳዋ ዳብቾ ላይ በነበረበት ወቅት ነው። የሲዳማ ሉዋ ሥርዓት የተጀመረው በዚሁ በዳዋ ነው ማለት ይቻላል።

የመጀመሪያው ሉዋ የጋዳ እና ዳልቻ ኩንቼ ሉዋ በመባል ይጠራል። ሳልፋ ወደ ተባለ ሥፍራ የዘመተው የሲዳማ ብሔረሰብ ወደ ፉልዋም ተጉዞ ሰፍሮ እንደነበርም አንስቷል።

ከአካባቢው ተወላጅ አዛውንቶች እንደሚናገሩት፤ ሲዳማ በዚህ ደረጃ የጀመረው ሉዋ የተሰኘው ተቋም በርካታ ማህበራዊ፤ አስተዳደራዊና መንፈሳዊ ፋይዳዎች አሉት። በአባልነት የሚያቅፋቸው ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች ጥንካሬን፤ አርአያነትን፤ አስታራቂነትን፤ ለሰላም መቆምን፤ እንዲሁም ሌሎች በጎ ምግባሮች እንዲቀስሙ ያስችላል። እንደ ‹‹ሞቴ›› እና ‹‹ወማ›› ያሉ ሌሎች ባሕላዊ ተቋማትም አጋዥ ሚና አላቸው። በተጨማሪም ሕዝቡን ከውጭ ጠላት ወረራ የመከላከል ተግባርም በሉዋ አመራር አባላት ይመራል።

በአንድ የሉዋ ሥልጣን ዘመን በማኅበረሰቡ መካከል ሰላም፤ ደህንነትና አንድነት እንዲሰፍን ማድረግም የሉዋ አባላት እና የመሪያቸው ተልዕኮ ነው። እናም በዚህ በሉዋ ሥርዓት ሁሉም ወንዶች እንደየትውልዱ ይሳተፉበታል። በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ከበሬታ እና ተቀባይነት ከማጎልበት አኳያም ወሳኝ ሚናን ይጫወታል ሲል በየካቲት 2003 ዓ.ም የታተመ የሲዳማ ብሔር ታሪክና ባሕል መጽሐፍ ያመለክታል፡፡

በመጽሐፉ እንደተጠቀሰው፤ አንድ ወንድ በሉዋ በመታቀፍ የሚፈለግበትን ኃላፊነት መወጣት ግድ ይለዋል። ይሄን ኃላፊነት ያልተወጣ ግለሰብ በማኅበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ባላቸው ማህበራዊ ክዋኔዎች የሚኖረው ተሳትፎ ውስን ይሆናል።

የሲዳማን ታሪክ የያዘውን መጽሐፉ አርታዕ የሆኑት አቶ ሱራፌል ገልገሎ በመጽሐፉ ላይ እንዳመለከቱት፤ ሉዋ የተሰኘው ይሄው ባሕላዊ ተቋም የራሱ አደረጃጀትና ባሕላዊ ሥርዓት አለው። የሚመራውም ይሄንኑ ተከትሎ ነው። በሂደቱም በሉዋ ከሚሳተፉ ተወላጅ ወንዶች ባሻገር ሌሎችም እንደሚሳተፉበት ይወሳል። ከሚሳተፉት መካከልም ጋሮ፤ ሞቴ፤ ጪምዬ ማሳላኖ፤ አያንቶ ይጠቀሳሉ። በዚህ ተሳትፎ አደረጃጀት የሚታይ አቻነት አለ፤ ሆኖም አቻነቱ ዕድሜ አይደለም። ይልቁንም የሚታየው ከትውልድ ቆጠራ አንፃር ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንድ ሕፃን ገና ከእናቱ ማህፀን ከመውጣቱ ወዲያውኑ በአባቱ የሉዋ ዑደት ውስጥ ይገባል። በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ እንዲህ ዓይነቱ የእድሜ ዑደት ሥርዓት በኢትዮጵያ የተጀመረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው ሚሊኒየም ውስጥ እንደሆነ የቅድመ ታሪክ ተመራማሪዎች ይጠቁማሉ።

የቅድመ ታሪክ ተመራማሪዋ ኤሄርት ስለዚሁ ስትገልጽ፦ ይሄ እድሜን መሠረት ያደረገ ዑደት የጎልማሶች ደረጃን ያጎናጸፋቸው የጋራ ሥርዓት ውስጥ ያለፉ ጎልማሶችን ያቀፈ ነው። ቅድመ ታሪክ ተመራማሪዋ አዲስ የጎልማሶች ቡድንም እንዲህ ዓይነቱን ሥርዓት የሚጀምረው በየስምንት ዓመት ገደማ እንደሆነም አስፍራለች፡፡

የሲዳማ ቋንቋ አርታዕ ዮሐንስ ላታሞ የሲዳማ ሉዋ በወጣትነት እድሜ ክልል ያሉትን ይመለከታል። ይሁንና ግን እንደዬ ትውልድ ምድባቸው በተለያዩ የዕድሜ ክልል የሚገኙትንም የሚያቅፍበት አለ። በሲዳማ ባሕል አንድ ሰው ከወጣትነት ወደ ሽምግልና የሚያደርገውን ሽግግርም የሚፈፅመው በሉዋ ሥርዓት ውስጥ ሲያልፍ ብቻ ስለመሆኑም ያነሳሉ። በመሆኑም ሰውየው ወደ ሽምግልና ደረጃ ለመድረስ በጎልማሳነቱ የግድ ቀድሞ የግርዛት ሥነ ሥርዓት መፈጸም ይጠበቅበታል ይላሉ።

እንደ እሳቸው ሃሳብ፤ ግርዛቱ በራሱ ታሪካዊ አመጣጥ አለው። በሰሜን እና ምስራቅ አፍሪካ ቀደምት ነዋሪዎች በነበሩ የአፍራሳን ነገድ ሕዝቦች ከክርስቶስ ልደት በፊት 9000 ዓመት ጀምሮ ሲከናወን የቆየ ነው። የሲዳማ ብሔረሰብ ግርዛትን መቼ እንደ ጀመረ ባይታወቅም የሲዳማ ብሔረሰብ አካል ከሆነው ከእነዚሁ የኩሽ ነገድ ከሆኑት የአፍራሳን ነገድ ሕዝቦች እሴት ስለመሆኑ የታሪክ መዛግብት ያመላክታሉ፡፡

ግርዛት በሉዋ ሥርዓት ወደ ሽምግልና ለመሸጋገር አንዱ ቅድመ ሁኔታ በመሆን እያገለገለ ያለ ሲሆን፤ አንድ የሉዋ አባል ከስምንት ዓመት በኋላ ለሚያገቡት የሉዋ ልጆች አባት የሚሆነውም የራሱ ሉዋ ዘመን ከማለፉ በፊት ይሄንኑ ግርዛት ፈፅሞ ሲገኝ ነው። ያለበለዚያ የሉዋ አባላትን እንደ አባት ተቀብሎ ለማብላት አይችልም። ክብርም የለውም፤ በራሱ የሉዋ ዘመን በመገረዝ ሥርዓቱን ያላሟላ ግለሰብ (Katela) ይሰጠዋልም ይላሉ።

የግርዛት ክወና ሥነ ሥርዓቱ ረጅም ቢሆንም የሉዋን ሥርዓት የሚከተል እንደመሆኑ መጠን የእድሜ ገደብ እንደሌለው ያነሳሉ። ተወላጁ ከሉዋ ሥርዓት በኋላ ሰባት ዓመታት ከመሙላቱ አስቀድሞ ‘ግዳይ ጥያለሁ፤ ታጥቂያለሁ እና ልገረዝʾ ሲልም የቀዬውን ወንድ የዕድሜ ባለፀጎች ፈቃድ ይጠይቃል። ሽማግሌዎቹም አባትህን፤ አጎትህን አልብሰህ ተመርቀሃል፤ የሻፌታ ቅቤ እና የእርድ ከብት አዘጋጅተሃልን? ሲሉ ይጠይቁታል። ሽማግሌዎቹ ይሄን እና ሌሎች የግርዛት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላቱ ሲያረጋግጡም የግርዛት ሥርዓቱን እንዲፈጽም ይፈቅዱለታል።

ከግርዛቱ አስቀድሞም ለሚገረዘው ሰው የቅርብ ረዳት የሚሆን ወጣት ይመረጣል። ወጣቱ ተገራዡ በድንኳን በሚቆይባቸው ጊዚያት ብቸኝነት እንዳይሰማው የሚያጫውትና ሲያገለግለው የሚቆይ ነው። የግርዛቱ ቀን ሲቃረብ የአካባቢው ሰው ተገራዡ የሚቆይበትን ዳስ ይሠራል። ዳሱ ተገራዡ የሚቆይበት ከቀርከሃ የተተከለ ጓዳና የሰው ማረፊያ ሳሎን ያሉት ነው። በዳሱ ዙሪያም አጥር ይታጠራል። በግርዛቱ ወቅት የሚቀመጥበትን ቁርበት የምታቀርበው ሚስቱ ባሕላዊ ሥርዓት የፈፀመች መሆን አለባት፡፡

በስለታም ቢላዋ ግርዛቱን የሚፈፅመው ሰውም በሲዳማ ብሔረሰብ ተወላጆች ዘንድ ዘመድ የዘመዱን ደም ማፍሰስ የለበትም ተብሎ ስለሚታመን ከተገራዡ ዘመድ መካከል መሆን የለበትም። በመሆኑም ከሲዳማ ጎሳ ውጭ የሆነ ሰው ይመጣና ሰውዬውን ይገርዘዋል። በዚህ መልኩ የግርዛት ሥነ-ሥርዓት የፈፀመ ግለሰብም (barcimino) ወይም (magalaale qafino) ይባላል። ይሄን ሥርዓት በማለፍ ወደ ሽምግልና ደረጃ የደረሰ ግለሰብ በኋላም በኅብረተሰቡ ውስጥ የተለየ ከበሬታ እና ኃላፊነትን ይቀዳጃል። ለምሳሌ ፦በሸንጎ ቦታ የሚካሄድ ውይይትን ይመራል። ገበታ ሲቀርብም ቀድሞ ይቆርሳል። ወንዝ ወይም ድልድይም ቢሆን ቀድሞ የመሻገር ማህበራዊ ከበሬታ የሚሰጠውም ይሄው በሉዋ ባሕል ወደ ሽማግሌነት ደረጃ የተሸጋገረ የብሔሩ ተዋላጅ ነው፡፡

አባቶች እንደሚሉት፤ በሉዋ ሥርዓት ‹‹ጪሜሳ›› የሆነ ተወላጅ ራሱን በሥነ-ሥርዓት የመምራት ዕድል ያገኛል። ለሀገር ሰላም ፈጣሪን የመለማመን ዕድልም በማህበረሰቡ ይቸረዋል። አስተውሎ የመናገር፤ ግጭት የመፍታት፤ ችግሮች ሲፈጠሩም በጥልቀት የማየት ዕድል ያገኛል። በመረጃ ላይ ተመስርቶ ችግሩን መርምሮ የመፍታት ኃላፊነትም ይኖረዋል።

ከሲዳማ ተቋማት አንዱ የሆነው ሉዋ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው አያሌ ተግባራት የሚከወንበት ነው። ከየጎሳው ተውጣጥተውና በትውልድ ዑደት ተደራጅተው የሚሳተፉበት ወንዶች በማህበራዊ ኑሯቸው እርስ በርስ ለመረዳዳት እና ለመደጋገፍ የእድሜ ልክ ጓደኝነት እንዲፈጥሩ የሚያስችልም ነው። ጠላትን ለመመከት እና የኅብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ የጋራ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማድረጉ ረገድ ዓይነተኛ መንገድ ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡

የሲዳማ ማኅበረሰብ ለኑሮው የሚመቸውን አካባቢ እየመረጠ መኖር ሲጀምር በቀጣይነት ራስን ለመከላከል፤ ለመረዳዳት፤ አንድነትን ለማጠናከር እርስ በርስ ለመከባበር እና ማህበራዊ ሥነ-ሥርዓት ለማስፈን የተገለገለበት ተቋም ስለመሆኑም የታሪኩ መጻሕፍት ይናገራሉ። የብሔሩ አዛውንቶች እንደሚስማሙበትም ሉዋ በመባል የሚታወቀው የሲዳማ ባሕላዊ የአኗኗር መርህ የብሔሩ መለያ እና የማንነት መግለጫ ጥንታዊ ባሕላዊ ተቋም ነው። በደምሳሳው የብሔሩ ማህበራዊ ሕይወት ከሉዋ ጋር በእጅጉ ተቆራኘ ነው፡፡

ሉዋ የሲዳማ ተወላጅ ማኅበረሰብ ወቅቶችን ለይቶ ለማስታወስም ይጠቀምበታልም። ዕድሜን ለመገመትና ዘመን ለመቁጠር የሚገለገልበት ቀን መቁጠሪያ (ከላንደር) እንደሆነም ነው የዕድሜ ባለ ፀጋ ተወላጆቹ የሚናገሩት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ተሰማ ታኣ ለመጽሐፉ በሰጡት ሃሳብ ፤ የአንድን ሰው ዕድሜ ለመናገር የሉዋውን እና የጋዳውን ስም ማወቅ በቂ ነው። በዚህ ጊዜም ሰውየው በማን ዘመን እንደተወለደ እና ዕድሜው ስንት እንደሆነ በትክክል መናገር ይቻላል። ምናልባት ከአንድ ክስተት ወዲህ ሦስት ሉዋ ተፈራርቆ ከሆነ የእያንዳንዱ ሉዋ ዘመን ስምንት ዓመት በመሆኑ ክስተቱ 24 ዓመት ያስቆጠረ መሆኑን ለመረዳት እንደሚቻልም ያወሳሉ።

የዕድሜ ባለፀጋው ሌዳሞ ኪአ እንዳሉት፤ ሉዋ የራሱ አከዋወን ሥርዓት ያለው ነው። አምስት ዑደቶች ያሉት ሲሆን፤ ቅደም ተከተሉን ጠብቀው ዘሩን በስምንት ዓመት የሚያበቁበት ሂደትም አለው። እነዚህ ሉዋዎች ቀዳሚው ወደ ሽምግልና እየገባ፤ ከአባት ወደ ልጅ ይሸጋገራሉ። አምስቱ ዑደቶች ማለትም ግማሽ ዙሮች ለ40 ዓመታት የሚቆዩበትም ነው። ሙሉ የሉዋ ዑደት በ80 ዓመታት የሚጠቃለል ይሆናል። በዚህ መርህ ታዲያ አንድ የተወለደ ሕፃን አባቱ ወደ ‹‹ጪመሳነት›› ሲሸጋገር የሉዋ ሥርዓት ቢያከብር በልጅ እና በአባት መካከል የ40 ዓመታት የትውልድ ክፍተት ይኖራል።

በእያንዳንዱ ጎሳ የሉዋው ሥነ-ሥርዓት የሚካሄድ በት ወቅት በወራት ሊለያይ ይችላል የሚሉት የዕድሜ ባለፀጋው የሁሉም ጎሳ የሉዋ ዙር የሚጀምርበት ዓመት (wogga) ግን ተመሳሳይነት እንዳለው በምሳሌ አስረግጠው ያስረዳሉ። ይህም የአባት ሉዋ ‹‹ፉላላ›› ከሆነ የእሱ ልጆች ደግሞ ‹‹ዋዋሳ›› የተባለውን ሉዋ ይቀላቀላሉ። ‹‹ሄርቦራ›› በሚል ስያሜ የሚታወቁት የ‹‹ዳራራ›› ሉዋ ልጆች ደግሞ የ‹‹ሞጊሳ›› ሉዋ አባላት እንደሚሆኑ ያብራራሉ።

እኚሁ አባት ስለ ሉዋ የራሱ ቅድመ ዝግጅት ያነሳሉ። ምንም እንኳን የሉዋ ድግግሞሽ በየስምንት ዓመቱ ቢሆንም ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ተግባሩ ከሰባተኛው ዓመት ነው የሚጀምረው። ዝግጅቱ የሉዋ መሪውን (ጋዳና) ረዳቶቹን የመምረጥ ሂደቶችን ያካትታል። ሆኖም የጋዳና ሥልጣን ከአባት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ባለመሆኑ በርካታ ሂደቶቹን አልፎ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈፀም ስለመሆኑም ያብራራሉ። ለአብነት አዲስ የሚገባው ሉዋ መሪዎቹን የሚመርጠው ሉዋ ከመግባቱ ከአንድ ዓመት በፊት ነው ይላሉ። የምርጫ ሂደቱም የተለያዩ ባሕላዊ ሥርዓቶችን ተከትሎ ስለመፈፀሙም ይጠቅሳሉ።

በሂደቱ ውስጥ የጎሳ መሪዎች ትንግርት ነጋሪዎች ሞራ አንባቢዎች እና ኮከብ ቆጣሪዎች ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው የሚናገሩት ሌንዳሞ፤ እነዚህ አካላትና ተቋማት የሉዋውን መሪ ምርጫ እና ሉዋ የሚገባበትን ወቅት በጥንቃቄ መክረው ይወስናሉ። ሆኖም እነዚህ ባሕላዊ መሪዎች የጋዳና አመራረጥ ሂደት ሥርዓቱን ተከትለውና አይተው ካልወሰኑ በተወላጆቹ ዘንድ ዘመኑ የሰላምና የጥጋብ አይሆንም ተብሎ ስለመታመኑም ያወሳሉ።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You