
ሕዝባችን ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት በተለያዩ የለውጥ አጋጣሚዎች ውስጥ አልፋለች። እነዚህን አጋጣሚዎች ለቡድን እና ለግል ዓላማ ለማዋል በተደረጉ ያልተገቡ ጥረቶች የተነሳ ሀገርን እና ሕዝብ ብዙ አላስፈላጊ ዋጋ ለመክፈል ተገድደዋል። ሀገራዊ የለውጥ መነሳሳቶቹም በአብዛኛው ተፈጥሯዊ ዓላማቸውን ሳያሳኩ ቀርተዋል።
የአንድ ግለሰብ፣ ማኅበረሰብም ሆነ ሀገር ቀጣይ ዘመን እጣ ፈንታ የሚወሰነው በውስጣቸው በሚኖር የመለወጥ መሻት/ መነሳሳት እንደሆነ የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁራን የሚስማሙበት የጋራ እውነት ነው። በዘመናት ውስጥ ያለው የሰው ልጅ የለውጥ ጉዞም የሚያመለክተው ይህንኑ እውነታ ነው።
በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ግለሰብ፤ ማኅበረሰብም ሆነ ሀገር በሕይወት ድባቴ ውስጥ እስካልገባ ድረስ፣ በአንድም ይሁን በሌላ ነገን ከዛሬ በተሻለ መልኩ የሚያይበት የፍጥረታዊ ጸጋ ባለቤት ነው። ጸጋው ለሕይወት ትርጉም እንዲኖረው ከማስቻል ባለፈ ተስፈኛ እንዲሆን ያስችለዋል።
ይህ በየትኛውም የዓለም ክፍል ለሚፈጠር ግለሰባዊ፤ ማኅበረሰባዊ እና የለውጥ መነቃቃት እንደ አንድ ፍጥረታዊ ምክንያት ተደርጎ የሚቆጠር፤ በትውልድ መካከል የሚኖርን ተለውጦ የመገኘት መሻት ወደ ተጨባጭ የሕይወት ሽግግር የሚያደርስ መንገድ ነው። መንገዱ በብዙ መንገጫገጮች የተሞላ፤ ስኬታማነቱም ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶችን ከመካድ የሚነሳ ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ የግለሰቦች እና የቡድኖች አበርክቶ ማኅበረሰቡ የደረሰበትን የአስተሳሰብ ደረጃ /አስተሳሰቡ የፈጠረውን የለውጥ መሻት የሚሸከሙ አማራጭ ሃሳቦችን ማፍለቅ ፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ተነሳሽነት መፍጠር ነው። የማኅበረሰቡን የለውጥ ፍላጎቶች ተጨባጭ የሚያደርጉ ተራማጅ /አሻጋሪ ሃሳቦችን ማፍለቅ እና በሃሳብ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት ነው።
የእዚህ ዘመን ፖለቲከኝነት መገለጫውም የተሻሉ የለውጥ ሃሳቦችን በማቅረብ፣ የማኅበረሰቡን የለውጥ መሻት እውን ማድረግ ነው። የማኅበረሰቡን የለውጥ መሻት ተፈጥሯዊ ሂደት በአግባቡ ተረድቶ ሂደቱን ሊያሳልጡ የሚችሉ ሃሳቦችን ይዞ መገኘት፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት የሚጠይቅ ነው። ከሁሉም በላይ ዕውቀት ተኮር ራዕይን የሚፈልግ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው አሁናዊ ተሞክሮም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም ፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተነሱ የማኅበረሰብ የመለወጥ ፍላጎቶች ስኬታማ የሆኑት፤ ከፍ ያሉ አማራጭ ሃሳቦችን ይዘው በተነሱ እና ሃሳቦቻቸውን በሃሳብ ገበያ መሸጥ በቻሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች አማካኝነት ነው።
ትናንትን በራሱ መልክ ተቀብለው፤ ዛሬን በራሱ ቀለም መሥራት ፤ ነገን ደግሞ በትናንት እና በዛሬ ህብር የተሻለ አድርገው ማየት በቻሉ እና ለእዚህ የሚሆን የተለወጠ ማንነት ባላቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች አማካኝነት ነው። የብዙዎች የእድገት እና የሥልጣኔ መሠረትም ይኸው ነው።
በአንዳንድ ፖለቲከኞች ዘንድ የሚታየው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። በየዘመኑ በተፈጠሩ የለውጥ ምዕራፎች ውስጥ በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የሕዝባችንን የመለወጥ መሻት መምራት የሚያስችል የተለወጠ ማንነት መፍጠር አልቻሉም፤ በእዚህም ሀገርን በሁለንተናዊ መንገድ መለወጥ የሚያስችሉ ሕዝባዊ የለውጥ ማዕበሎች ከንቱ ሆነው ቀርተዋል።
የሕዝባችን የለውጥ መሻት ወደ ተጨባጭ ተስፋ መለወጥ የሚያስችሉ አስተሳሰቦችን ተሸክሞ ወደ ሃሳብ ገበያው ከመምጣት ይልቅ ፤ ኃይል እና ሴራን መሠረት ካደረገው የቆየ የፖለቲካ ባሕላችን የሚቀዱ የፖለቲካ አሰላለፎች በዝተው፤ በትውልድ መካከል የተፈጠሩ ማኅበረሰባዊ የመለወጥ መሻቶች ከስኬት ርቀው ቆይተዋል።
ይህ ዘመናት ያስቆጠረ የፖለቲካ ባሕላችን ዛሬም ትውልዱ በብዙ መሰዋዕትነት የጀመረውን ለውጥ ለማናወጥ ሲፍጨረጨር ይገኛል። አብዛኞቹ ፖለቲከኞቻችን ኃይልን ታሳቢ ባደረጉ ፉከራ እና ቀረርቶዎች አደባባዮችን ሞልተው ታይተዋል። ቁስሎችን በማከክ እና በማድማት ይህንንም እንደ አዋጭ የፖለቲካ ስትራቴጂ ቆጥረው በድፍረት የሚንቀሳቀሱ፤ በእዚህም ሕዝባዊ ተቀባይነት ለማግኘት የሚውተረተሩም ጥቂት አይደሉም ።
በሕዝብ ውስጥ ለውጥ አስፈንጣሪ አጀንዳዎችን ከመፍጠር እና ለሕዝብ ሁለንተናዊ የመለወጥ መሻት ራስን ከማስገዛት ይልቅ ፤ ሕዝብን ከለውጥ ተስፋ የሚያራርቁ የጥፋት መንገዶችን ሳይቀር የፖለቲካ አማራጮች አድርገው መውሰድ ፤ በዚህም ሀገራዊ የፖለቲካ መድረክን ማጣበብ የፖለቲካ ፋሽን። በዚህም እንደ ሀገር የከፈልነው እና እየከፈልነው ያለው ያልተገባ ዋጋ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ይህ ዘመኑን የማይዋጅ የሕዝባችንን የዘመናት የለውጥ መሻት ወደ ተጨባጭ ተስፋ መለወጥ የማያስችል ከአሮጌነት የሚመነጭ የጥፋት መንገድ፤ መቼም ቢሆን ሀገርን አያጸናም ፤ ዘላቂ የሥልጣን ምንጭ ሊሆንም አይችልም። የጥፋት ዘር ከመሆን ባለፈም ማንንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አይደለም፤ ለዚህም የእስከ ዛሬ ጉዟችን ተጨባጭ ማሳያ ነው።
አሁን ሀገር እና ሕዝብ የሚፈልጉት አማራጭ የለውጥ ሃሳቦችን እና ለአማራጭ ሃሳቦች የተገዛ የፖለቲካ ባሕል ነው። የለውጥ መሻቶችን ተጨባጭ የሚያደርጉ ያደጉ አሻጋሪ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳቦችን እንጂ፤ ተነስ ፤ አምጽ፣ ታጠቅ የሚሉ በሴራ የተሞሉ የጥፋት አማራጮችን አይደለም!
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም