ብሔራዊ ሙዚየም ከዛሬ ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል

– ቅርሶቹ ደረጃውን የጠበቀ እድሳት ተደርጎላቸዋል

አዲስ አበባ፡– በሙዚየሙና ምድረ ግቢ እድሳት ምክንያት ተዘግቶ የቆየው ብሔራዊ ሙዚያም ከዛሬ ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆን ተገለጸ። የሙዚየሙ እድሳት ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም መታየት ያለባቸው ዋና ዋና ቅርሶች ደረጃውን የጠበቀ እድሳት እንደተደረገላቸው ተጠቁሟል።

ሙዚየሙ ትናንት ምሽት የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከፍቷል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ እድሳቱ ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም መታየት ያለባቸው ዋና ዋና ቅርሶች ደረጃውን የጠበቀ እድሳት ተደርጎላቸው ለጎብኚዎች ክፍት ሆነዋል። የተቀሩት ቦታዎችም በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃሉ ብለዋል።

“እድሳቱ ሦስት ዓይነት ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የመጀመሪያው ምድረ ግቢው ነው ብለዋል። በግቢው ውስጥ የሚገኙ ዛፎች ከ70 እና 80 ዓመታት በላይ የቆዩ ስለሆኑ በንፋስ መቋቋም ተስኗቸው አደጋ ማድረስ ጀምረው ነበር። በአንድ ተሽከርካሪ እና በአንድ የኤ ቲ ኤም ማሽን ላይ ጉዳት እንዳደረሱ ገልጸው፤ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ምድረ ግቢው እድሳት እንዲደረግለት መወሰኑን ተናግረዋል።

“ዛፎቹ ሲቆረጡ ዝም ብሎ ‹ና ቁረጥ› ማለት ሳይሆን በዕፅዋት ባለሙያ ተጠንተው ነው” ያሉት የታሪክ ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ ሀገር በቀል እና ጠንካራ የሆኑት ዛፎች እንዳልተቆረጡ ተናግረዋል። ምድረ ግቢውን የማስተካከል ሥራውም ሙሉ በሙሉ እንዳልተጠናቀቀና በሚቀጥሉት 15 ቀናት እንደሚጠናቀቅ ጨምረው ተናግረዋል።

“ሁለተኛው እድሳት ራሱ ሙዚየሙ ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ 1965 ዓ.ም የተሠራው ሙዚየም የውሃ ማፋሰሻው የተስተካከለ ባለመሆኑ መሠረቱ ላይ ችግር ፈጥሮ እንደነበር ተናግረዋል። የቅርስ ማሳያ ላይ የተቀመጡ ቅርሶችም ለእርጥበት የመጋለጥ ዕድል ተጋርጦባቸው እንደነበር ጠቅሰው፤ ዘመናዊ የውሃና እርጥበት መከላከል ሥራ እንደተሠራ ተናግረዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ሦስተኛው የብሔራዊ ሙዚየም እድሳት ውስጥ ላይ ያለውን የሙዚየም ቋሚ ኤግዚቢሽን ማዘመን ነው። ከመስከረም 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታሪካዊ አርኪዮሎጂ ክፍሉ በዘመናዊ መንገድ ተሠርቷል። የፓንቶሎጂ ክፍሉ ከእዚህ በፊት ይታይበት ከነበረው የጥንት የድንጋይ መሳሪያ በተጨማሪ ሥነ ሕይወትንም እንዲጨምር ተደርጓል። የሥነ ሕይወት ዝግመተ ለውጥን በሚያሳይ ሁኔታ ታድሷል ብለዋል።

ለብሔራዊ ሙዚየሙ እድሳት የፈረንሳይ መንግሥት የሙያ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የሚታዩ ዋና ዋና ቅርሶች ለዕይታ ተዘጋጅተው እንደተጠናቀቁ ተናግረዋል። በታደሰው እና ቀጣይ በሚታደሰው ሙዚየም ውስጥ የሚታዩት ቅርሶች ከእዚህ በፊት እንደነበረው የሚታየውን ቅርስ በዓመተ ምህረት እና በዘመነ መንግሥት ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ገለጻዎችና ማብራሪያዎች የተደረጉበት ነው ብለዋል። ቅርሶቹን በገለጻና ማብራሪያ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እስከ ታኅሣሥ ወር ድረስ ሊቆይ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

“ቅርስ ከሕክምና ያላነሰ ውስብስብ ዘርፍ ነው” ያሉት የታሪክ ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ እንደ ሥነ ሥዕል፣ ሸክላ እና ቆዳ የመሳሰሉ ቅርሶች ላይ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጠንካራ እንደሆኑ፤ ቅሪት አካል እና ጂኦሎጂ ዘርፎች ላይ ግን የውጭ ባለሙያዎች ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ቅርስ በአንድ ወይም በጥቂት ባለሙያ የሚጠና ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ሙያ የሚያስፈልገው እንደሆነ አመልክተው፤ የኢትዮጵያ የቅርስ ባለሙያዎች እንደ ብራና ባሉ ቅርሶች ለውጭ ባለሙያዎች ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርጉ እና በቅርስ አያያዝ ኢትዮጵያውያን ተመራጭ እንደሆኑ ተናግረዋል። ተባይ እና ሌሎች ጎጂ ነገሮችን መከላከል ላይ ደግሞ የውጮቹ ሀገራት የተሻሉ ናቸው ብለዋል። ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን በያዝነው ሳምንት መከበሩ ይታወሳል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You