በክልሉ ከፊል አርብቶ አደሮች ከ120 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ እያለሙ ነው

ሰመራ፦ በአፋር ክልል ከፊል አርብቶ አደሮችን የእርሻ ሥራ በማለማመድ በአሁኑ ጊዜ ከ120 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በማልማት አበረታች ውጤት መገኘቱን የአፋር ክልል እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አህመድ፤ በዱብቲ ወረዳ ያለውን የእርሻ ሥራ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሪፖርተሮች ባስጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት፤ ለውጡን ተከትሎ በተሠሩ የመስኖና የተለያዩ ሥራዎች ቀደም ሲል ምንም ባልለሙ አካባቢዎች ጭምር የእርሻ ሥራዎች እየተስፋፉ ናቸው። በክልሉ በዘንድሮው ዓመት 133ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ በአሁኑ ጊዜ ከ120 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በማልማት አበረታች ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።

ከለውጡ በፊት በክልሉ የነበረው የእርሻ እንቅስቃሴ አነስተኛ እንደነበር አውስተው፤ ከለውጡ በኋላ ግን ከፊል አርብቶ አደሮችን ግንዛቤ እያስጨበጡ ወደ እርሻ የማስገባት ሥራ በመሠራቱ ለውጥ መታየት እንደቻለ ተናግረዋል።

ከእንስሳት ጋር ተቆራኝቶ የቆየውን የክልሉን ማህበረሰብ ወደ እርሻ ሥራ ማስገባቱ ፈታኝ እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ከፊል አርብቶ አደሩ ባገኘው ግንዛቤ እና በሠራው ሥራ ጥቅም እያገኘ መሆኑን ተከትሎ በራሱ ተነሳሽነት የእርሻ ሥራውን እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአፋር ክልል እርሻ ምርታማ የሚሆንባቸው የመኸር እና የበልግ ወቅቶች እንደሆኑ ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በበጋ መስኖ ማልማት እንደተቻለና በክልሉ ለመስኖ ሥራ የሚውል ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ከለውጡ በኋላ በግብርና ማሻሻያ ኢንሼቲቮች በተሠሩ ሥራዎች በምግብ ራስን ለመቻል የሚያስችሉ የእርሻ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው ተጠቁሟል።

ክልሉ ከፍተኛ የውሃ፣ የመሬት እና የሰው ኃይል አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤እነዚህን አቅሞች በማቀናጀት ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን አቶ አህመድ አስታውቀዋል። በእዚሁ መሠረት፤ በተለይ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሾ፣ አኩሪ አተር፣ ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ ሰብል ምርቶች ላይ ውጤት እየተመዘገበ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

እንዲሁም ከፍተኛ አካባቢዎች ላይ ይታወቅ የነበረው የጤፍ ምርት አሁን ላይ በከፊል አርብቶ አደሮቹም ውጤታማነቱ እየታየ መሆኑን አቶ አሕመድ ተናግረዋል። ከፊል አርሶ አደሩ በክላስተር የማረስ ልምድን እያስፋፋ መምጣቱን እና የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ልውውጥ የሚያደርግ በመሆኑ በአንድ ሄክታር የሚገኘው ምርታማነት እያደገ መጥቷል ብለዋል። የክልሉ ከፊል አርብቶ አደር ተረፈ ምርቱን ለእንስሳት መኖነት በመጠቀም ተጨማሪ ጥቅም እያገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

የዱብቲ ወረዳ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ኃላፊ አቶ መሃመድ ኑር አሊ በበኩላቸው፤ በወረዳው ሰሊጥ ፣ በርበሬ፣ ሽንኩርት፣ ፓፓዬ፣ ማሾ እየተመረተ መሆኑን ገልጸው፤ ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር ተያይዞ ለ100 ሄክታር መሬት የሚሆን የብርቱካን ችግኝ በወረዳው እየለማ መሆኑንም አስረድተዋል።

ወረዳው በአፋር ክልል በአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ ከሚለሙ ኮሪዶሮች በሰብል ልማት በቀዳሚነት የሚጠቀስ እንደሆነና 27 ሺህ ሄክታር በኢንቨስትመንት ሊለማ የሚችል መሬት እንዳለው አስረድተዋል። በማህበረሰብ አቅም የሚለማ 7ሺህ 584 ሄክታር መሬት ስለመኖሩም ገልጸዋል።

ለሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቅርበት የሚገኝ መሆኑንና ለኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መሥመር ቅርብ መሆኑ ለአልሚዎች ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው ብለዋል። በመስኖና በፓምፕ ሊለማ የሚችል ወደ 34 ሺህ ሄክታር ያህል መሬት በወረዳው መኖሩንም አቶ መሃመድ ኑር አስረድተዋል። ይህን አቅም በመጠቀም ማህበረሰቡን ከተረጂነት ለማላቀቅ እየተሠራ መሆኑን አቶ መሀመድ ኑር ተናግረዋል።

ገበያን በተመለከተ በሽንኩርት፣ በቲማቲም፣ በጤፍና፣ በሀባብ፣ በማሾና በስንዴ ምርት ላይ ከሸማቾች ጋር ትስስር የተፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከለውጡ በፊት አፋር ክልል ምንም አይበቅልበትም የሚል አስተሳሰብ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን መንግሥት በግብርና ዘርፍ ያደረጋቸውን ኢኒሼቲቮች በክልሉ መተግበር ከጀመሩ ወዲህ የአፋር መሬት የሰጡትን ሁሉ ማምረት እንደሚችል በተጨባጭ ታይቷል ብለዋል።

የወረዳውን ማህበረሰብ ከተረጂነት ለማላቀቅ አዳዲስ መሬቶች ወደ ልማት እየገቡ መሆኑን፤ መንግሥት የሰጣቸውን የልማት አቅጣጫዎች እና የተፈጠሩት ግንዛቤዎች ውጤት ማፍራታቸውን አቶ መሃመድኑር አስረድተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You