
የኢትዮጵያን የባሕል ስፖርት ለማሳደግ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የተለያዩ እቅዶችን አውጥቶ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ፌዴሬሽኑ ከሚያደርጋቸው ጥረቶች አንዱ የኢትዮጵያ የባሕል ስፖርቶች ከተለመደው ዓመታዊ የባሕል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የዘመናዊ ስፖርቶች ውድድሮች ተካተው ፉክክር እንዲደረግባቸው ማስቻል ነው። በእዚህም መሠረት ለዓመታት ተቋርጦ ከወራት በፊት በተጀመረው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር ላይ የባሕል ስፖርቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ፉክክር ሊደረግባቸው ችሏል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር በእዚህ ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች ለዓመታት ተቋርጠው የቆዩ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ዳግም እንዲጀመሩ የሚያደርገውን ጥረት ተከትሎ፣ ለዘጠኝ ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችም በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። ከ2008 ዓ.ም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት በመጪው ሰኔ መጀመሪያ በጅማ ከተማ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው 6ኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታ ዳግም መካሄድ ሲጀምር ከዘመናዊው የኦሊምፒክ ስፖርቶች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶችም የውድድሩ አካል እንደሚሆኑ ታውቋል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ይህንኑ 6ኛው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችን የውድድር ደንብ በተመለከተ ከቀናት በፊት ከብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ጋር ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የሁሉም ፌዴሬሽን ተወካይና ተሳታፊዎች የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ተቋርጠው የነበሩ ውድድሮችን ማስቀጠል መቻሉን እና የባሕል ስፖርቶችም በእዚህ ውድድር መካተታቸውን አድንቀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን አመስግነዋል።
ከሁለት ሳምንት በኋላ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀውን የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችና የውድድር ደንቦችን በተመለከተ በተደረገው ውይይት በርካታ መሠረታዊ ጥያቄዎች ተነስተው መወያያ ሆነዋል። ፌዴሬሽኖች ካነሷቸው ሃሳቦች አንዱ የተጫዋች ተገቢነት ጉዳይ ሲሆን፤ ቀደም ሲል በመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ላይ ያለው ደንብ ተነስቶ ኃላፊነቱ ውድድሮችን ለሚመሩት ለፌዴሬሽኖች እንዲሰጥ የሚል ነው። በክለብ የሚጫወቱ ተጫዋቾች በመላ ኢትዮጵያ ጨዋታ አይሳተፉም የሚለው ደንብም አሻሚ በመሆኑ የየትኛው የክለብ ካታጎሪ ነው የማይሳተፈው ? የሚለው በግልፅ እንዲቀመጥ ተጠይቋል።
ከእዚሁ ከተጫዋች ተገቢነት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡ ተጫዋቾች መሳተፍ አይችሉም የሚለው ደንብ እንደ የስፖርት ዓይነቱ ተለዋዋጭ ቢሆን የሚል ሃሳብም ተነስቷል። በአንድ የስፖርት አይነት በትንሹ ሦስት ተወዳዳሪ ክልሎች ወይም ከተማ አስተዳደሮች ካልተሳተፉ የውድድር ዓይነቱ ይሠረዛል የሚለው ሕግ ለአትሌቲክስ ስለማይሆን ቢሻሻል የሚል ሃሳብም ተደምጧል። መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች የኦሊምፒክ መርህን ተከትሎ የሚደርግ ውድድር በመሆኑ በእዚህ ረገድ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ያለው ግንኙነት በግልጽ መቀመጥ እንዳለበትም አስተያየት ተሰጥቶበታል። የውድድሩ ሎጎም በባለሙያ ትርጉም ባለው መንገድ ቢሠራ ተብሏል።
በተጨማሪም ክለብ የሚያሠለጥኑ አሠልጣኞች ክልሎችን ያሠለጥናሉ ወይ? የሚለው ጉዳይ ግልፅ እንዲሆን የተጠየቀ ሲሆን፤ መላ ኢትዮጵያ ጨዋታ ከፌዴሬሽኖች መደበኛ የውድድር ዝግጅት ጋር በማይጋጭ መልኩ የውድድር ጊዜ እንዲስተካከል የሚሉ መሠረታዊ ሃሳቦች ተነስተዋል።
ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ የመወዳደሪያ ቦታዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ናቸው ወይ? የሚል ሲሆን፤ ከእዚሁ ጋር ተያይዞ የፓራሊምፒክ ተወዳዳሪዎች በቁጥር ትንሽ ስለሆኑ በብሔራዊ ውድድር የተሳተፉም በመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች እንዲወዳደሩ በደንቡ እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ ቀርቧል።
የሜዳሊያና ዋንጫ ሽልማቶች እንደየውድድሩ ዓይነት ቢሆን፤ የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ቢካተት፤ አንድ አሠልጣኝ ከአንድ ስፖርት በላይ ማሠልጠን አይችልም የሚለው ደንብ እንደየክልሎች ነባራዊ ሁኔታ ቢወሰን መልካም እንደሚሆንና ሌሎችም ጠቃሚ ሃሳቦች በጥያቄና አስተያየት ቀርበዋል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መክዩ መሐመድ፣ በፌዴሬሽኖች በኩል የተደረገውን ንቁ ውይይት አድንቀው፤ የተሰጡ ሃሳቦችና አስተያየቶችን እንደ ግብዓት ወስደው እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል። አብዛኛውን ፌዴሬሽኖች ተተኪ ስፖርተኞች ለማፍራት በሚያመች መልኩ የራሳቸውን ደንብ እንደሚያዘጋጁም ጠቁመዋል። አያይዘውም፣ የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ዓላማ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደመሆኑ ዓላማውን እንዳይስት እና ተተኪ ስፖርተኞች በብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች እንዳይሸፈኑ በጥንቃቄ ይሠራል ብለዋል። እንደየስፖርቱ ሁኔታ በተለየ መንገድ የሚታዩትን ከፌዴሬሽኖች ጋር እንደሚያዩም አስረድተዋል። የመወዳደሪያ ቦታዎች እና ማደሪያዎችን በተመለከተ ግን ለሁሉም ስፖርተኞች ምቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም