
አሜሪካ የኤር ፎርስ ዋን አካል እንዲሆን ከኳታር በስጦታ የተበረከተላትን እና በተወሰኑ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ትላልቅ ደጋፊዎች ጭምር ትችት ያስከተለውን አውሮፕላን ተቀበለች።የፔንታጎን ዋና ቃል አቀባይ ሻን ፓርኔል ባወጡት መግለጫ፤ “የመከላከያ ሚኒስቴር በሁሉም የፌዴራል ሕጎች እና ደንቦች መሠረት ቦይንግ 474ን ከኳታር ተቀብሏል” ብለዋል።
አውሮፕላኑ፤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ይፋዊ አየር መጓጓዣ የሆነው ኤር ፎርስ ዋና አካል ሆኖ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ማሻሻያ ይደረግበታል።ዋይት ሃውስ ስጦታ ሕጋዊ ነው በሚለው አቋሙ ቢጸናም፤ ከሳምንት በፊት አውሮፕላኑ መሰጠቱ በተገለጸበት ወቅት ትልቅ ውዝግብ አስነስቶ ነበር።ከኳታር ንጉሳዊ ቤተሰብ በስጦታ የተበረከተው አውሮፕላን ዋጋ 400 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ዋይት ሃውስ አዲሱ አውሮፕላን በትራምፕ የሥልጣን ዘመን መጨረሻ ወደ ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መዘክር ይዘዋወራል ብሏል።
ፕሬዚዳንቱን ለማጓጓዝ የግዴታ መካተት ያለባቸውን ተጨማሪ የደህንነት ሥርዓቶች ለማሟላት እና ለማሳደግ ዓመታትን ሊወስድ ይችላል ተብሏል።ከእነዚህ የደህንነት ሥርዓት ማሻሻያዎች መካከል በኒውክሌር ፍንዳታ የሚመጣን ኤሌክትሮ ማግኔቲክ ኃይል ግፊት እንዲቋቋም ማድረግ እና በረራ ላይ እያለ ነዳጅ መሙላት መቻል ይገኙበታል።
‘በሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ኤንድ ኢንተርናሽናል ስተዲስ’ የመከላከያ እና ደህንነት ክፍል ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ማርክ ካንሲያኒ፤ እነዚህን ማሻሻያዎች ማከናወኛ ወጪው በቀላሉ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተናግረዋል።ትራምፕ ከሳምንት በፊት የአውሮፕላኑን መምጣት በደገፉበት ንግግራቸው፤ “እየሰጡን ያለው ስጦታ ነው” ብለው ነበር። በስጦታ የተበረከተውን አውሮፕላን ውድቅ ማድረግ “ሞኝነት” መሆኑንም ተናግረዋል።
የአሜሪካ ሕገ መንግሥት፤ የመንግሥት ኃላፊዎች ያለ ኮንግረስ ፈቃድ ከውጭ መንግሥታት ስጦታ እንዳይቀበሉ የሚከለክል ‘የኢሞሊውመንት አንቀጽ’ ተብሎ የሚታወቅ ድንጋጌ አለው። የአሁኑ አውሮፕላን የኮንግረሱን ፈቃድ አላገኘም።ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስጦታው ለመከላከያ ሚኒስቴር እንጂ ለራሳቸው ቀጥታ የተበረከተ አለመሆኑን በመጥቀስ፤ የአውሮፕላኑ መምጣት ሕጋዊ ስለመሆኑ ይከራከራሉ። ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ እንደማይጠቀሙትም ይገልጻሉ።
አሁን በሥራ ላይ ባሉት የኤር ፎስር ዋን ዝርዝር እ.አ.አ ከ1990 ጀምሮ በሥራ ላይ የነበሩት ሁለት 747-200 አውሮፕላኖች እና በርካታ አነስተኛ 757 አውሮፕላኖችን ያካትታል።ትራምፕ፤ በቀጥታ ለዋይት ሃውስ ቦይንግ ሁለት 747-8 አውሮፕላኖችን እንዲያቀርብ ውል በተፈጸመለት አውሮፕላን ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።የትራምፕ አስተዳደር ቡድን አባላት በፕሬዚዳንቱ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን ጊዜ ለመረከብ ተደራድረው የነበረ ቢሆንም በተደጋጋሚ መዘግየት አጋጥሟል። ቦይንግም አውሮፕላኖቹ ለተጨማሪ ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት ለአገልግሎት እንደማይደርሱ አስታውቋል።
ትራምፕ ሁለተኛ ሥልጣን ዘመናቸው በተጀመረ በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ባለቤትነቱ የእርሳቸው በሆነው ማር-አ-ላጎ ሪዞርት አቅራቢያ በፓልም ቢች የሚገኝን የኳታር አውሮፕላን በድብቅ ጎብኝተው ነበር።ፕሬዚዳንቱ፤ አውሮፕላኑ በአጋሮች መካከል የተደረገ ቀላል ልውውጥ እንደሆነ በመግለጽ ጉዳዩ በምላሹ የሚሰጥ ምንም ነገርን እንዳላካተተ ይከራከራሉ።
“የመከላከያ ሚኒስቴር እጅግ ይፋዊ እና ነጻ በሆነ ልውውጥ ያለ ምንም ክፍያ 40 ዓመት የሞላውን ኤር ፎርስ ዋን በጊዜያዊነት የሚተካ 747 አውሮፕላን በስጦታ አግኝቷል” ሲሉ በትሩዝ ማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል። የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሞሃመድ ቢን አብዱልራህማን ቢን ጃሲም አል ታህኒ የአውሮፕላኑ መላክ “የመንግሥት ለመንግሥት ዝውውር” መሆኑን ተናግረዋል።”በኳታርም ሆነ በአሜሪካ በኩል (ጉዳዩን) ከግላዊ ግንኙነት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ጉዳዩ በሁለት መከላከያ ሚኒስቴሮች መካከል ነው” ብለዋል።
እነዚህ ገለጻዎች ግን ኮንግረስ ውስጥ ከሚገኙ የትራምፕ አጋሮች እና ቀኝ ዘመም መገናኛ ብዙኃን ጭምር ስምምነቱን በተመለከተ እየተነሱ ያሉትን ትችቶት ለማብረድ እምብዛም አልተሳካላቸውም።የኬንታኪ ግዛት የሪፐብሊካን ሴናተር ራንድ ፖል፤ “አግባብ የሌለው ሆነም አልሆነ ነገርየው እየፈጠረ ያለውን የሕገ ወጥነት ምስል የሚያካክስ አይደለም” ሲሉ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።”(የኳታርን) የሰብአዊ መብት ታሪክ መመዘን አቅማችን በእዚህ ትልቅ ስጦታ ምክንያት ይጋረድ እንደሆን አስባለሁ” ሲሉም ተደምጠዋል።
ሌላኛው የቴክሳስ ሪፐብሊካን ቴድ ክሩዝ በበኩላቸው፤ ስጦታውን መቀበል “ግዙፍ የስለላ እና የክትትል ችግር” እንደሚጋርጥ ገልጸዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም