በዜጎች ታላቅ መስዋዕትነት የዛሬ ሦስት ዓመት የተወለደው ሀገራዊ ለውጥ ከዋዜማው አንስቶ እስከ አሁን ያደረገውን ጉዞ ኢትዮጵያውያን ሲዘክሩ ሰንብተዋል። ለውጡን እውን ለማድረግ የተከፈሉ መስዋዕትነቶች፣ ለውጡ ከመጣ በኋላም መንግሥት በገባው ቃል መሰረት የተከናወኑ ሥራዎች፣ ያጋጠሙ ፈተናዎችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች በዚህ ታላቅ ወቅት ተዳሰዋል።
ከዚህ በተቃራኒው የቆሙ ኃይሎች ግን በተለመደው የጥፋት ሥራቸው ተጠምደው ሰንብተዋል። ኢትዮጵያውያን ድላቸውን በሚያስቡበት በዚህ ወቅት አንገታቸውን እንዲደፉ ያደረጉ ጥቃቶችን በዜጎች ላይ ፈጽመዋል። በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በተፈፀሙ ጥቃቶች አሁንም በርካታ ንፁሃን ዜጎች ውድ ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል። ሌሎች በርካቶችም በሥጋት ውስጥ እንዲኖሩ ተገድደዋል። ከዚህ ሁሉ ጀርባ ግን እነዚህ ጥቃቶች መንግሥት አሁንም ብዙ በርካታ የቤት ሥራዎች እንዳሉበት ያመለከቱ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ የተፈፀመውን ጥቃት አውግዘው፣ በሁሉም ቦታ ለደረሰው ጥቃት በክልልና በፌዴራል መንግሥት በቅንጅት የአፀፋ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥፋተኞችን ወደ ሕግ ለማቅረብና ይህን አይነት ግድያዎች እንዲቆሙ ለማድረግ ከመንግሥት ጎን ሆኖ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።
ድርጊቱ ኢትዮጵያውያን የአገራዊ ለውጡን ጉዞ እያሰቡ ባለበት በዚህ ወሳኝ ወቅት መፈፀሙ፣ የለውጡን አጀንዳ ለማስጣልና ሌላ አጀንዳ ለመስጠት እንደመሞከርም ይቆጠራል። ኢትዮጵያም በዚህና መሰል ድርጊቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ውድ ልጆቿን ማጣቷ ያንገበግባታል። ከዚያ በመለስ ግን ኢትዮጵያ ግዙፍ አጀንዳዎች ያላት ሀገር እንደመሆኗ፤ ጠላቶቿ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት አጀንዳ አድርገው የሚያመጧቸውን ሁሉ አንጠልጥላ አትወዛወዝም። ጠላቶቿም ይህን በሚገባ ያውቃሉ። ሀገሪቱ ዜጎቿን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ብልጽግና የሚወስዱ በርካታ አጀንዳዎች አሏት።
ጥቃቶቹ ቡድኖቹ አሁንም የዜጎች እና የሀገሪቱ ሥጋቶች መሆናቸውን አመላክተዋል። መንግሥት በእነዚህ አካባቢዎች የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ እየወሰደ ያለውን የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ሥራ አሁንም አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዛቢዎች ናቸው። መንግሥት ቢሆን፣ በትህነግ አጥፊ ቡድን ላይ በወሰደው እርምጃ ሀገሪቱን እዚህም እዚያም ይፈፀምባት ከነበረ ጥቃት መታደግ ተችሏል እየተባለ ባለበት ሁኔታ ጥቃቶቹ ለምን ይህን ያህል ሊደርሱ እንደቻሉ ገምግሞ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል።
እነዚህ ቡድኖችና አባሎቻቸው በአብዛኛው ህብረተሰቡ ውስጥ ተሸጉጠው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ጭምር ተሰግስገው እንደሚገኙ እየተጠቆመ ነው። ህዝብ ውስጥ የተሸጎጠ ጠላት ማለት ደግሞ እንደ ሰብል ውስጥ አረም ነው። እነዚህን ሃይሎች ለቅሞ ለማውጣት የህዝቡ ሚና ከፍተኛ ነው።
በዚህ ረገድ ደግሞ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ምህዳርን ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራችን ይገኛሉ። ፓርቲዎቹ በርካታ አባላት ያላቸው እንደመሆናቸውም ህዝቡ ዘንድ ለመድረስ ዕድል ይኖራቸዋል።
ከዚህ አኳያ ሰሞኑን አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርጊቶቹን ማውገዛቸውና ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ መግለፃቸው የሕግ የበላይነት ለማስከበሩ ሥራ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ፓርቲዎቹ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ድርጊቶቹን አውግዘው መንግሥት የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር አሳስበዋል። ማንነትን መሰረት አድርጎ የሚፈፀም ጥቃት እንዲቆም ጠይቀዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ እናት ፓርቲ፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በጋራ መግለጫቸው እንዳሉት፤ የፌዴራሉ መንግሥትና የየክልል መንግሥታት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።
ፓርቲዎቹ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈፀመውን ዘር ተኮር ጥቃት በማውገዝ መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር ነው የጠየቁት። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለልተኛ ኮሚሽን በማቋቋም በጥልቀት መርምሮ ውጤቱን ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግም አሳስበዋል። ፓርቲዎቹ በእንዲህ አይነት አገራዊ አደጋ ወቅት በጋራ እንደሚሠሩም በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
ፓርቲዎቹ ድርጊቱን ማውገዛቸውና በማንነት ላይ እየተፈፀመ ያለው ጥቃት እንዲቆም፣ መንግሥትም ሕግን እንዲያስከብር እና የጥቃቱ ፈፃሚዎች ተይዘው ለሕግ እንዲቀርቡ እንዲያደርግ መጠየቃቸው የመላው ኢትዮጵያውንም ጥያቄ ነውና ተገቢና ወቅታዊ ነው።
ይሁን የሕግ የበላይነት የማስከበሩ ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው መሆን የለበትም። በዚህ የኢትዮጵያውያንን አጋርነት በሚጠይቅ ወሳኝ ወቅት ላይ ፓርቲዎቹ አብረው ለመሥራት ማረጋገጫ መስጠታቸውም ትልቅ ስፍራ ይኖረዋል።
አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ እና ድርጊቱን ለማስቆም በመንግሥት በኩል እየተከናወነ ባለው ተግባር የፖለቲካ ፓርቲዎችና አባሎቻቸው አጋርነት ወሳኝ ነው። እናም ፓርቲዎች ተገቢ የሆነውን የሕግ የበላይነት እንዲከበር የመጠየቅ እርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የጠየቃችሁት በተግባር እንዲገለጽ በማድረጉ ዘረገድ በሚከናወነው ሥራ ውስጥም ሚናችሁን በሚገባ መወጣት ይኖርባችኋል። ለዚህ ደግሞ አባሎቻችሁን በመያዝ የመፍትሄው አካልም ሁኑ!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/ 2013 ዓ.ም