አስተማማኝ የሠላም ዋስትና ለማረጋገጥ የምክክር ባሕልን ማዳበር ይገባል

አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ አስተማማኝ የሠላም ዋስትና ለማረጋገጥ የምክክር ባሕልን ማዳበር እንደሚገባ የሠላም ሚኒስትር አስታወቀ።

“የሠላም ባሕልን ማዳበር” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሠላም ቀን ምክንያት በማድረግ በትናትናው ዕለት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ በሠላም ሚኒስትር የሠላም ግንባታ ሥራ አስፈፃሚ አወቀ አጥናፉ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የሠላም ዋጋ በምንም ሊተመን የማይችል ለሰው ልጆች ሁሉ አስፈላጊ የሆነ መሠረታዊ ነገር በመሆኑ በኢትዮጵያ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ አስተማማኝ የሠላም ዋስትና ለማረጋገጥ የምክክር ባሕልን ማዳበር ይገባል።

የአንድ አካባቢ የሠላም እጦት ለሌላው አካባቢ ሠላም እጦት ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥር መሆኑን ያነሱት አወቀ (ዶ/ር)፤ ሠላም የአንድ ወገን ብቻ ባለመሆኑ ለዘላቂ ሠላም ግንባታና ፅናት ሁሉም በባለቤትነት መሥራት አለበት ብለዋል።

በሠላም ማጽናት ሂደትም ምክክር የማይተካ ሚና እንዳለው ገልፀው፤ በሀገሪቱም የምክክር ኮሚሽን በየአካባቢው የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል እንደሚሆን እና እስካሁን ባለው ሂደትም በየአካባቢው መሠረታዊ ችግሮች እንዲፈቱ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አስታውቀዋል።

በመሆኑንም በዚህ የምክክር ሂደት ላይ በተለይም የሠላም እጦት ዋነኛ ተጠቂ ሴቶችና ወጣቶች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸውና የምክክር ባሕልን በማዳበር ለዘላቂ ሠላም የበኩላቸውን እንዲወጡ አወቀ (ዶ/ር) አሳስበዋል።

አወቀ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ሚኒስትሩ በሠላም ጉዳይ ተዋናይ ኃይሎችን በማካተት በሠላም ግንባታ ላይ ሊሠሩ የሚገባቸው ጉዳዮችና አካላትን በማሳተፍ የማኅበረሰቡን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል የሠላም ፖሊሲ በቅርቡ በመንግሥት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ፖሊሲው የሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለመጠቀም ሠላምን ለማስፈን የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ጨምሮ ያካተተ ነው። እንደፀደቀም የሥራ መመሪያ በማድረግ ማኅበረሰቡ የሠላም መፍትሔው በእጁ እንዳለ በማመላከት አስተማማኝ የሠላም ዋስትና ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ዋና ተጠሪን በመወከል የተመድ የልማት ፕሮግራም ዋና ኃላፊ ሳሙኤል ዱኤ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የሠላም ቀን ስናከብር ሠላም ማለት ግጭት የሌለበት ማለት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ጥረትና ርብርብ በዘላቂነት የሚጠይቅ ሂደት መሆኑን መረዳት አለብን ብለዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የሀገራዊ ምክክር ግጭቶችን በንግግርና ውይይት በመፍታት የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ሀገሪቱ ለሠላም ያላትን ቁርጠኝነት የሚሳይ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ሴቶችና ወጣቶችን በማብቃትም ለሀገር እድገት ብሎም ሠላምን ማጽናት የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸው፤ ወጣቶችና ሴቶችን በሠላምና ፀጥታ ግንባታ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ለማሳደግና ለማብቃት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጋራ የሚሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You