ዘመን፤ ብሔራዊ ጥቅሞችን የማስጠበቅ እና የማስቀጠል ጉዳይ፤ ዓለም አቀፋዊ የተቃርኖ አጀንዳ ሆኖ ዓለምን በአንድም ይሁን በሌላ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል፤ ወዳልተገባ ግጭት እና አለመረጋጋት ውስጥም ከቷል። ባለንበትም ዘመን ፍትሐዊነት የሌላቸውን ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የሚደረጉ ጥረቶች፤ ዓለምን ዳግም ወዳልተገባ አለመተማመን እየወሰዱ ነው ።
ፍትሐዊነት ዓለም አቀፍ መርሕ እንዲሆን በቀደሙት ዘመናት ዓለም ብዙ ዋጋ ከፍላለች። አምባገነኖች በኃይል፤ ሴረኞች በሴራ ፍትሐዊ ያልሆኑ ጥቅሞቻቸውን እውን ለማድረግ የሄዱበት ያልተገባ መንገድ፣ መላውን ዓለም ብዙ ዋጋ አስከፍሏል ፤ የሀገራት ሕዝቦችን ለተለያዩ ደም አፋሳሽ የርስ በርስ ግጭቶች እና ጦርነቶች ዳርጓል።
በሴራ እና በኃይል ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የተደረጉ ጥረቶች፣ ከዚህም ባለፈ ዓለምን በተለያዩ ጎራዎች ለይቶ ጠላትነትን በመፍጠር፣ ዓለም ከመቼውም ጊዜ በላይ የሕልውና ስጋት ውስጥ እንድትወድቅ አድርጓል፤ ለዚህም በቀዝቃዛውን ጦርነት ወቅት ዓለም ገብታበት የነበረውን አጣብቂኝ ማስታወስ የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት አመላካች ነው።
ችግሩ እንደ ሀገር እኛን ኢትዮጵያውያንን የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን የአደባባይ ሚስጥር ነው፣ ዛሬ ላይ በመሠረታዊነት ሀገራዊ ፈተና የሆኑብን ችግሮቻችን በአንድም ይሁን በሌላ የዚሁ የትናንት ዓለም አቀፋዊ እውነታ ጥላ ስለመሆናቸው የስድስት አስርት ሀገራዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትርክቶቻችን ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው።
ከነበርንበት እና ዛሬም ካለንበት ስትራቴጂክ ጂኦ ፖለቲካል አካባቢ አኳያ፣ በየዘመኑ የተነሱ ኃይሎች ትኩረት እንደነበርን፣ እነሱ ፍትሐዊ ያልሆኑ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ከሄዱባቸው የጥፋት መንገዶች የተነሳ በግጭት አዙሪት ውስጥ ለመኖር የመገደዳችን እውነታ ለማንም የተሰወረ አይደለም።
ይህ ራሳቸውን ሁሌም ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጨምሮ በአካባቢው ብሔራዊ ጥቅሞች አሉን የሚሉ የተለያዩ ኃይሎች፣ አለን የሚሉትን ጥቅሞቻችውን በተለመደው የሴራ መንገድ ለማስጠበቅ የሚሄዱባቸው መንገዶች፣ ከኢትዮጵያ አልፎ በአካባቢው ሕዝቦች የመልማት መብት ላይ ትልቅ ፈተና ሆኗል።
ችግሩ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦችን ለከፋ ድህነት እና ኋላ ቀርነት ዳርጓል። የዕጣ ፈንታቸውን ያህል ተደርጎ የሚወሰደው ድህነት እና ኋላ ቀርነታቸው በራሱ ግጭቶችን በማስፋት እና ለግጭቶች ተጨማሪ ጉልበት በመሆን የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ሠላም እና መረጋጋት እንዳይኖራቸው አድርጓል።
የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች በዘላቂነት ለሠላማቸው እና ለልማታቸው የሚያደርጓቸው ጥረቶች፣ በውጪ ሴራ ትርጉም ያለው ፍሬ እንዳያፈራ ተደርጓል። ከዚህም አልፎ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ቤተሰብነታቸውን እያጡ የራሳቸው ባልሆኑ የተቃርኖ አጀንዳዎች ጠላት ሆነው የሚተያዩበትን ሁኔታ ሲፈጥር ቆይቷል።
የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦችን ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት ማስቀጠል የሚያስችሉ አስተሳሰቦች እንዳይሰፉ፣ ከዚህ ይልቅ የልዩነት እና የጠላትነት ትርክቶችን በማስፋት አካባቢው ከግጭት አዙሪት እንዳይወጣ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች በብሔራዊ ጥቅም ስም ሲዘመሩ መስማት ዛሬም ድረስ የተለመደ ሆኗል።
ይህ ችግር አሁን ላይ እንደ ሀገር ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው በመወሰን ከድህነት እና ከኋላቀርነት ለመውጣት የሚያደርጉትን ትግል፣ እንደ ሀገር የጀመሩት ድህነትን ታሪክ የማድረግ መነቃቃት በሁለንተናዊ መልኩ እየፈተነ ነው። እንደ ትናንቱ የአካባቢውን ሀገራት አብሮ የማደግ ተፈጥሯዊ የለውጥ ጉዞም እየተገዳደረ ነው።
ፍትሐዊነት ዓለም አቀፍ መርሕ በሆነበት በዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ፣ ከራሳቸው ተርፎ ለአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ተስፋ የሚሆን የለውጥ ንቅናቄ ውስጥ መገኘታቸው ዘላቂ ለሆነ የጋራ ተጠቃሚነት እና አብሮ የማደግ መነሳሳት መንገድ መሆኑ ታውቆ ሊበረታታ እንጂ በተቃርኖ እሳቤ ሊፈተን የሚገባ አልነበረም።
ይህን ታሪካዊ እውነታ ከማንም ይልቅ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች በአግባቡ ሊረዱት እና ከራሳቸው ቀጣይ ብሩህ ዕጣ ፈንታ ጋር አስተሳስረው ሊያጤኑት ያስፈልጋል። ትናንት ከውጪ ጣልቃገብነት ጋር በተያያዘ እንደ አንድ ቤተሰብ ለራሳችን ላልሆነ አጀንዳ ከከፈልነው ያልተገባ ዋጋ አ ኳያ አሁናዊ መንገዳችንን ልንመረምረው ይገባል።
የአካባቢው ሀገራት ብሔራዊ ጥቅሞች በአንድም ይሁን በሌላ የተሳሰሩ ናቸው፣ አንዳችን የሌላችን ብሔራዊ ጥቅም አካል ነን። እነዚህን ጥቅሞች ማስከበር የጋራ ኃላፊነታችን ነው። የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች የመልማት ፍላጎት እውን ሊሆን የሚችለው ይህን እውነታ በአግባቡ መገንዘብ ስንችል እና ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ ስንሆን ብቻ ነው ።
ከዚህ ውጪ የውጪ ኃይሎችን የጥፋት አጀንዳ ተሸክሞ በመሄድ የሚገኝ ትርፍ/ብሔራዊ ጥቅም አለ ብሎ ማሰብ ከብዙ ትናንቶች ስህተት ለመማር ፈቃደኛ አለመሆን እና ከአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች የዘመናት የመልማት ፍላጎት በተቃርኖ መቆም ነው። ከግጭት አዙሪት ወጥተው የራሳቸውን እድል በራሳቸው እንዳይወስኑ የማድረግ የጠላትነት ተልዕኮም ነው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም