ከሲዳማ ክልል ከ36 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ይቀርባል

አዲስ አበባ፡- በምርት ዘመኑ ከ36 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን የሲዳማ ክልል ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማቅመም ባለሥልጣን አስታወቀ። ዘንድሮ ወደ ውጭ ከሚላከው የቡና ምርት 200 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ይገኛልም ተብሏል።

የክልሉ ቡና ፍራፍሬና ቅመማቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በ170 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ቡና በስፋት ይለማል። ከዚህ ውስጥ 142 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማው ምርት የሚሰጥ ነው።

የቡና ምርታማነት የሚጨምሩ ፓኬጆችን በአግባቡ መጠቀም በተቻለበት በ1 ሄክታር 11 ኩንታል የቡና ምርት ይገኛል ያሉት አቶ መስፍን፤ በዘንድሮው የምርት ዘመንም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የቡና ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።

ከሚሰበሰበው ምርትም 36 ሺህ 100 ቶን በላይ የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፤ ይህንን ለማድረግም አስቀድሞ 204 ሺህ ቶን እሸት ቡና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲሰበሰብ ይደረጋልም ብለዋል። ወደ ውጭ ከሚላከው የቡና ምርት 89 በመቶው የታጠበ ሲሆን 11 በመቶው ደግሞ ደረቅ ቡና ነው።

ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ በመላክ ረገድ በተለይም ከ2014 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ተከታታይ የምርት ዘመናት የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡንና ዘንድሮም የሲዳማ ቡና በዓለም ገበያ ደረጃውን ይዞ እንዲቀጥል ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል።

ዘንድሮ ከሚላከው የታጠበ የቡና ምርትም 75 በመቶው 1ኛ ደረጃን፣ 24 በመቶው 2ኛ ደረጃን እንዲሁም 1 በመቶው ብቻ 3ኛ ደረጃን እንዲይዝና ደረጃው ከዚያ በታች እንዳይሆን ለማድረግ መታቀዱንም ገልጸዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ዘንድሮ ወደ ውጭ ከሚላከው የቡና ምርት 200 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ታቅዷል። ይህም ክልሉ በዘርፉ የሚጠበቅበትን አስተዋፅዖ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያበረክት ያደርጋል።

የዓለም የቡና ዋጋ የሚወሰነው በእንግሊዝና አሜሪካ ሀገራት በሚገኙ የቡና ገበያ ማዕከላት እንደሆነ ያስረዱት አቶ መስፍን፤ በተለይ በ2014 የምርት ዘመን በግል ኢንዱስትሪዎች የዓለምን የቡና ዋጋ ባላማከለ ሁኔታ የምርት ዋጋ ከፍ ብሎ መሸጡንና በ2015 ደግሞ በዝቅተኛ ዋጋ መሸጡን ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት ለማጥበብ በ2016 ዓ.ም ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገዙ መደረጉን አስታውሰዋል።

በተያዘው የምርት ዘመንም የዓለምን የገበያ ዋጋ በተከተለ ሁኔታ ግብይት እንዲፈጸምና አርሶ አደሩም ሆነ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ማኅበራት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራም ተጠቁሟል።

ቡና ለክልሉም ሆነ እንደ ሀገር የተሻለ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ዘርፍ እንደመሆኑ እንደ ትልቅ ሀብት የሚታይ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይ አምራች አርሶ አደሮች የቡና ዛፎችን በመትከልና ኮምፖስት መጠቀምን ጨምሮ የቡናን ጥራትና ምርታማነትን የሚጨምሩ ፓኬጆችና ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ።

ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ብቻም ሳይሆን በክልሉ ቡና በኩታ ገጠም የማልማቱ ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነም ተነግሯል።

በክልሉ በአሁኑ ወቅት በግል፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራትና በአክሲዮን የተደራጁ 450 የእሸት ቡና መፈልፈያ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ለነዚሁ ኢንዱስትሪዎች ኃላፊዎችን በየወረዳው ለሚገኙ ልማት ባለሙያዎች የቡና ጥራትን ማስጠበቅ በሚያስችሉ ሂደቶችና ቅድመ ጥንቃቄዎች ዙሪያ ሰሞኑን ሥልጠና መሰጠቱንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

አምሳሉ ፈለቀ

አዲስ ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You