አዲስ አበባ:- ኢትዮጵያ የምታካሂዳቸው የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና መሰል ሕጋዊ አሠራሮች የሀገርን ጥቅም ባስጠበቀ፣ ተወዳዳሪነትን በሚጨምርና በአፍሪካ ያላትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በሚያስከብር መልኩ እንዲተገበር ትኩረት መሰጠቱን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።
በ11ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የግልግል ዳኝነት ኮንፍረንስ ላይ ንግግር ያደረጉት የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር)፤ የግልግል ዳኝነት የግጭት መፍቻ ዘዴ በኢትዮጵያ እንዲያድግ ፍትሕ ሚኒስቴር ትኩረት መስጠቱን አመልክተዋል።
የግልግል ዳኝነት ውስብስብ እና ግዙፍ የንግድ ልውውጦች የሚዳኙበት የግጭት መፍቻ ዘዴ ሲሆን፤ አካሄዱ ያልተወሳሰበ፣ ወጪ ቆጣቢና ጊዜ የማይወስድ የንግድ ውል ስምምነት እንዲቀጥል የሚያስችል በመሆኑም በመሠረታዊነት ከመደበኛው ፍርድ ቤት ይለያል ብለዋል።
በመደበኛው ፍርድ ቤት የሚታዩ ጉዳዮች በአብዛኛው ቀጣይ ግንኙነትን በሚያጠናክር መልኩ አይዳኙም። በተለይ ከንግድ ሁኔታ አንጻር ሲታይ አሸናፊና ተሸናፊ የሚኖርበት ሁኔታ ስለሚኖረው ተመካሪ አይደለም።
የግልግል ዳኝነት አሠራር እንዲስፋፋ አዋጅና ደንቦች ተዘጋጅተዋል። ባለሙያዎች የግልግል ዳኝነት ሥልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
መንግሥት ሃገርን በሚጠቅም ሁኔታ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በማውጣት የተለያዩ ርምጃዎችንም ወስዷል ያሉት ኤርሚያስ (ዶ/ር)፤ በፊት ዝግ የነበሩ የንግድና የፋይናንስ ዘርፎችንም ክፍት ማድረጉን ገልጸዋል። በትግበራው ምክንያትም የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እየጨመረ እንደሚቀጥልም እምነታቸውን ተናግረዋል።
ኤርሚያስ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በቅርቡ የተወሰደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢትዮጵያን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንደሚያደርጋት ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ከሰሐራ በታች ካሉ ሀገራት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የምታስመዘግብ ሀገር ናት። በማዕድን፣ በኢነርጂ፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ፣ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ይሠራሉም ነው ያሉት።
በዚህ ሂደት ያለመስማማቶችና ግጭቶች ሲኖሩ ቦታዎች እና አስማሚዎች ወይም ገላጋዮች በብዛት ከአፍሪካ ውጭ ለንደን፣ ሲንጋፖር፣ ሆንግኮንግ ወይንም አሜሪካ ለመሄድ በመገደዳችን ምክንያት ከፍተኛ ገንዘብ ይወጣል። ሀገር በቀል አሸማጋዮችም ስለማያድጉ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
ኮንፍረንሱ ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰም ይረዳል፣ አዲስ አበባ የዓለማቀፍ ዲፕሎማቶች መቀመጫ ከመሆኗ ባሻገርም የኢኮኖሚ የቱሪዝም ማዕከል፣ የኮንፍረንስ ማዕከል ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል ብለዋል።
ፍርድ ቤቶች የሚመሩበት የሕግ ሥርዓት አለ። የሚፈጀው ጊዜ እና ከሚወጣው ገንዘብ አንጻርም በመደበኛው ፍርድ ቤት ከሚታየው ጋር ሲነጻጸር በግልግል የሚዳኙት ዝቅ ይላል ሲሉም ተናግረዋል።
የግልግል ዳኝነት ክርክር ያላቸው አለመስማት ያጋጠማቸው ወገኖች በስምምነት ወይም በውላቸው መሠረት እንዲፈጸምላቸው የሚፈልጉትን አስማሚ፣ ገላጋይ ወይንም ዳኛ መርጠው የሚከራከሩበት፣ ማስረጃ የሚያቀርቡበት ነው።
አሠራሩ በኢትዮጵያ ሲሠራበት የኖረ እና በፍትሐብሔር ሕጉም እውቅና የተሰጠው መሆኑንም አመልክተዋል።
የማሊ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ታሕቦ ቻካካ ኒይሬንዳ እንዲህ አይነትና መሰል ኮንፍረንሶችን ማድረግ የግልግል ዳኝነት ልምድ እንዲዳብር፣ እውቀትና ተሞክሮ ለማወቅ እና ለመረዳት ያስችላል ብለዋል። ከሌሎች ሃገራት ጋር ለመገናኘት ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም