የፈጣን አውቶብስ አገልግሎት በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1974ዓ.ም በብራዚሏ ኩሪቲባ ከተማ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። እ.ኤ.አ በ2008 የናይጄሪያዋ ዋና ከተማ ሌጎስ ደግሞ ከአፍሪካ ቀዳሚ በመሆን የፈጣን አውቶብስ አገልግሎት ልታስጀመር ችላለች።
በመቀጠልም በታንዛኒያ፣ በዩጋንዳ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በሞሮኮ ዋና ዋና ከተሞች የፈጣን አውቶብስ አገልግሎት እውን ሆኗል። ኢትዮጵያም በዋና መዲናዋ አዲስ አበባ የፈጣን አውቶብስ አገልግሎትን ለማስጀመር የዝግጅት ስራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች።
የፈጣን አውቶብስ መስመር የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት እውን መሆንም በ2012 በጀት ዓመት መጨረሻ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።በከተማዋ የፈጣን አውቶብስ መስመር ግንባታ መጀመሩ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር በቀጣይ ለሚሰሩ መሰል ፕሮጀክቶች ልምድ የሚገኝበት እንደሚሆን ይታመናል።
የፈጣን አውቶብስ መስመር ግንባታ ከግራና ከቀኝ የሚኖሩ ዜጎችን የሚያቀራርብ እንጂ በከተማዋ እንደተገነባው ቀላል ባቡር መስመር የሚያራርቅ እንዳይሆን በከፍተኛ ጥራትና ጥንቃቄ እንደሚሰራ ነው በወቅቱ የተነገረለት።
በአዲስ አበባ ሊገነቡ የታሰቡት ፈጣን አውቶብስ ብቻ የሚጓዝባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ስድስት ናቸው። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች አንዱ እና የመጀመሪያው ቢ2 ኮሪደር ከዊንጌት ተነስቶ ጀሞ ቁጥር አንድ ኮንዶሚኒየም የሚደርሰው ይገኝበታል።
ይሕ የፈጣን አውቶብስ መስመር አጠቃላይ 19ነጥብ 2 ኪ.ሜ ርዝመትና 23 የአውቶብስ መጠበቂያ ጣቢያዎች ይኖሩታል። የመንገድ ፕሮጀክቱ ከዊንጌት ተነስቶ በአውቶብስ ተራ አድርጎ በተክለ ሐይማኖት፣ በሰንጋ ተራ ሜክሲኮ፣ ከሜክሲኮ በቡልጋሪያ ቄራ አድርጎ ወደ ጎፋ በመሻገር በጀርመን አደባባይ ጀሞ የሚዘልቅ ሲሆን በጥቅሉ አምስት ክፍለ ከተሞችን አቋርጦ የሚያልፍ ይሆናል።
የግንባታ ወጪውም ከፈረንሳይ መንግስት የልማት ድርጅት በተገኘ ብድር እና በከተማ አስተዳደሩ የሚሸፈን ከ5ነጥብ9 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦለታል። ይህ ለአዲስ አበባ ከተማ ብሎም ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው የፈጣን አውቶብስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመታት ከስድስት ወር የጊዜ ቀጠሮ ተቀምጣል።
ይህ ቢ 2 ኮሪዶር ተብሎ የሚጠራው የፈጣን አውቶቢስ መስመር ፕሮጀክት ሰኔ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ራዜል – ቢኢሲ /RAZEL-BEC የተባለ ዓለም አቀፍ የፈረንሳይ የስራ ተቋራጭ የግንባታ ስራውን ለማከናወን ውል መግባቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የስራ ተቋራጩ በገባው ውል መሰረት ግንባታውን ማስኬድ ተስኖታል። ይህን ጉዳይ በሚመለከት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን የፕሮጀክቱ ስራ ተቋራጭ በገባው ውል መሠረት ግንባታውን ማስኬድ ተስኖት ስራውን ማቋረጡን አረጋግጠዋል።
ይህ በመሆኑም የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከጀሞ ሁለት አደባባይ እስከ ጀሞ ሚካኤል አደባባይ ድረስ ባለው የመሀል አካፋይ የመንገድ ክፍል ላይ የመንገድ ግንባታ ስራውን በራስ ኃይል እያከናወነ መሆኑን ያስረዳሉ።
የብዙኃን ትራንስፖርትን በማቀላጠፍ ረገድ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለውን ይህን ፕሮጀክት መንግስት እንደሚገነባ ማሳታወቁን እና ሕብረተሰቡም በጉጉት የሚጠብቀው መሆኑ ያወሱት ምክትል ዳይሬተሩ፣የተገባውን ቃል ለመጠበቅም ግንባታውን በተቃደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በራስ ሃይል ወደ ስራ መገባቱን ነው ያብራሩት።
እንደ አቶ እያሱ ገለፃ፣ ባለስልጣኑ የከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለማቃለል የዚህን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጨምሮ በሌሎች የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችም የግንባታ ሂደታቸውን ለማፋጠን በቀንና በማታ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
አሁን ላይ የአፈር ቆረጣ፣ የገረጋንቲ አፈር ሙሌት እና የሰብ ቤዝ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ከ 1 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ገደማ አስፋልት ለማንጠፍ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።
የመንገድ ፕሮጀክቱ ካለው አጠቃላይ 19 ነጥብ 2 ኪ.ሜ ርዝመት ውስጥ 3ነጥብ2 ኪሎ ሜትር የሚሆነው በባለስልጣኑ የራስ ሀይል የሚከናወን ሲሆን ቀሪው 16 ኪሎ ሜትር ደግሞ በቀጣይ በጨረታ ተለይቶ በሚያሸንፈው ኮንትራክተር የሚገነባ ይሆናል።
ከግንባታ አቅም ጋር በተያያዘ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ብቃት በሚመለከት ላቀረበላቸው ጥያቄ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሲመልሱ፣የፕሮጀክቱ ግንባታ ከፍተኛ አቅም እና ሰፊ ስራ የሚጠይቅ ነው፤ ይሑንና ይህ አይነት አስተያየት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በአሁን ወቅት የደረሰበትን የግንባታ አቅም ደረጃ በአግባቡ ካለመረዳት የሚመነጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የፈጣን አውቶብስ በቀን ለ16 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ የሚጠናቀቅ ይሆናል።የፈጣን አውቶብስ መስመር ዝርጋታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ እውን ሲሆን በአዲስ አበባ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍና ዘመናዊ የብዙኃን ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ትልቅ እገዛ ይኖረዋል
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም