በኦሮሚያ ክልል የበርካታ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ወደ ማድረግ የተሸጋገሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቃቸው ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።
በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ ካልቻሉት ፕሮጀክቶች አንዱ ሂዲ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ነው። የሂዲ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በምስራቅ ሸዋ በአዳኣ ወረዳ በ200 ሚሊዮን 795 ሺህ ብር በ2002 ዓ.ም ነበር የተጀመረው። የግንባታው ሥራ ሲጀመር በ2011 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞለትም ነበር። በእቅዱ መሰረት እስካሁን ግድቡ ተጠናቆ ለአርሶ አደሮች መተላለፍ የነበረበት ቢሆንም ፕሮጀክቱ አልተጠናቀቀም። የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ መረጃ እንደሚያመላክተው እስካሁን ድረስ የፕሮጀክቱ 98 በመቶ ማጠናቀቅ ነው የተቻለው።
250 ሄክታር መሬት ማልማት እንደሚችል ተስፋ የተጣለበት ይህ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት 500 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ይችላል ተብሎ የግንባታው ሥራው እየተካሄደ ሲሆን ከ200 ሚሊዮን 795 ሺህ ብር የጨረታ ዋጋ ውስጥ እስከ 2013 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ 123 ሚሊዮን 792 ሺህ ብር ክፍያ መፈጸሙን የቢሮው መረጃ ያሳያል።
በኦሮሚያ የግብርና ቢሮ የኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ዳባ እንደሚሉት፤ የሂዲ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ ቆይቷል። ከችግሮቹ ሁሉ ዋነኛው ችግር ግን ፕሮጀክቱ በርካታ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች የሚበዛበት በመሆኑ የግንባታ እቃዎች ከውጭ ነው የሚገቡት ። የፕሮጀክቱ ሲቪል ሥራ በጊዜ የተጠናቀቀ ሲሆን ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ አልተቻለም።
ኤሌክትሮ መካኒካል እቃዎች ከውጭ ሀገራት የሚገቡ እንደመሆናቸው የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋል። የውጭ ምንዛሪ ግን በተፈለገበት ጊዜ ማግኘት ከባድ ነበር። በውጭ ምንዛሪ ችግር ምክንያት ነው የፕሮጀክቱ ግንባታ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ በላይ ጊዜ መፍጀቱን አብራርተዋል።
የሲቪል ሥራዎችም ተጠናቀው፤ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ መሰረት ባለመጠናቀቃቸው ቀድመው የተሰሩ የሲቪል ሥራዎች ጭምር የተለያዩ ጉዳቶች አጋጥሟቸው እንደነበር አቶ ተፈሪ ያነሳሉ። ጉዳት ያስተናገዱ ቦታዎችን የመጠገን ሥራም የግድ አስፈላጊ በመሆኑ በትኩረት ሲሰራ እንደነበር ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ ተፈሪ ማብራሪያ፤ ችግሩን ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ በ2013 በጀት ዓመት ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ታቅዶ ነበር። ነገር ግን በ2013 ዓ.ም የምንዛሪ ችግር ስላልተፈታ ፕሮጀክቱ ሊያልቅ አልቻለም። አሁን ግን የውጭ ምንዛሪ ችግር ተፈቷል። ከውጭ ሀገራት መግባት ያለባቸው አብዛኞቹ እቃዎች ከውጭ ሀገራት ገብተዋል። እነዚህን ማሽነሪዎች የመግጠም ሥራ ብቻ ነው የሚቀረው። በ2014 በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአርሶ አደሮች ይተላለፋል ተብሎ እቅድ ተይዞለታል።
ፕሮጀክቱ በታዘለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ ኢኮኖሚው ላይ የራሱ የሆነ ጫና ማሳደሩን የተናገሩት አቶ ተፈሪ፤ የደረሰው ኢኮኖሚያዊ ጫና ግን እስካሁን እንዳልተጠና በማብራራት፤ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ የደረሰው ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እንደሚጠና ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አማካሪ አቶ ዘየደ ተሾመ እንደሚሉት፤ በክልሉ በርካታ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው፤ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶቹ በሶስት ይከፈላሉ። ትላልቅ የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች፣ መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች እንዲሁም አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ናቸው። ሁለት ትላልቅ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በተያዘው የ2014 በጀት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን ሁለቱ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የትላልቅ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ቁጥር ወደ አራት እንደሚያሳድገው ይናገራሉ።
በመሰራት ላይ ያሉት መካከለኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የሂዲ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን ጨምሮ 16 ሲሆኑ 16ቱም ፕሮጀክቶች በ2014 በጀት ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብሎ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ነው። ይህም የመካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ቁጥር ወደ 20 የሚያሳድግ ይሆናል።
ከአሁን ቀደም በክልሉ ውስጥ የሚገነቡ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በተለያዩ ምክንያቶች ፕሮጀክቶች ሲጓተቱ የነበረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጓተቱትን እንዲሁም በቅርብ ጊዜ የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች በፍጥነት በመጨረስ ከፕሮጀክቶቹ መገኘት ያለበትን ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ ነው። አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች እስከ ሶስት ዓመት ሲፈጁ የነበሩ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በአንድ ዓመት በማጠናቀቅ ለአርሶ አደሮች እንዲተላለፍ እየተደረገ ነው።
የእያንዳንዱን ፕሮጀክቶች ችግር በማጥናት መፍትሄ እየተሰጠ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች በ2014 በጀት ዓመት ተጠናቀው ለአርሶ አደሮች እንዲተላለፉ አስፈላጊው ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22/2013