ይጠናቀቃሉ ተብሎ ከተያዘላቸው ጊዜ ላይ ተጨማሪ በርካታ ዓመታትን የጠየቁ፣ ከተመደበላቸው በጀት በላይ ብዙ ገንዘብ የቀረጠፉ፣ ያልቃሉ የሚል ተስፋ የተጣለባቸው ቢሆንም ሊያልቁ ባልቻሉ ፕሮጀክቶች ምክንያት ሀገሪቱ ብዙ ዋጋ የከፈለችባቸው፤ የህዝቦች የቅሬታ መነሻ ሆነው የከረሙ በርካታ ትላልቅ የመንግስት ፕሮጀክቶች ከለውጡ በፊት ነበሩ። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ መንግስት ስልጣን ከተረከበበት ማግስት ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ የሰራው የፕሮጀክቶቹ ችግር ምን ነበረ የሚለየውን መለየት ላይ ነው። ሀገሪቱን ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ እና ህዝቡን ለቅሬታ የዳረጉ የእነዚህ ፕሮጀክቶች ችግሮችን መፍታት እና አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት በቀጣይነት ትኩረት የተሰጠው ስራ ነበር።
የለውጡ መንግስት በወሰዳቸው ቆራጥ እርምጃዎች ከተያዘላቸው ጊዜ ተጨማሪ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩ ፕሮጀክቶች መካከል የተወሰኑት ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል። በተለይም 2013 በርካታ ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁበት ብሎም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ የነበሩት ደግሞ ተስፋ ለምልሞ የታየበትም ነበር።
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከነበሩ ፕሮጀክቶች ውስጥ ጥቂት የማይባሉት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ፣ በርካቶች ደግሞ ከነበሩበት አስቸጋሪ ሁኔታ ወጥተው ወደ ግንባታ እንዲገቡ በመንግስት በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል። ከነዚህ እርምጃዎች መካከል አንዱ በአንድ ኮንትራክተር ተይዘው የነበሩ ፕሮጀክቶች በተለያዩ አቅም ባላቸው ንዑስ ኮንትራክተሮች እንዲያዙ እና በጥራት እንዲጠናቀቁ ማድረግ ነው ።
በዚሁ መሰረት በጥቃቅን ምክንያቶች ሳይጠናቀቅ የቆየው የገናሌ ዳዋ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ የተጠናቀቀበት፣ የቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ተጠናቆ ስራ የጀመረበት፣ የሞጆ-መቂ-ባቱ መንገድ የመሳሰሉ ትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑበት እንዲሁም ከታቀደለት ጊዜ ከስምንት ዓመት በላይ ተጓቶ የነበረው የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ተጠናቆ ወደ ምርት የገባበት ዓመት ነው።
ከሁሉ በላይ የኢትዮጵያዊያን ምልክትና የማንነት መገለጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የለውጥ አመራሩ በያዘው ጠንካራ አቋም እና በወሰዳቸው ቆራጥ እርምጃዎች በመታገዝ አመርቂ ውጤቶች የተመዘገበበት ነው። ምንም እንኳ ሀገር በውስጣዊ እና በውጫዊ ችግሮች ተወጥራ ብትገኝም እነዚህን ጫናዎችን በመቋቋም ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ያከናወነችበት ዓመትም ነበር።
ይሁን እንጂ ከለውጡ በፊት በነበሩት ዓመታት የኮንትራት አስተዳደር ችግሮች፣ የወሰን ማስከበር ፣ ቆራጥ የፖለቲካ ውሳኔ እጦት፣ በቂ ጥናት ሳይካሄድ ወደ ግንባታ መገባት፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በሚደረጉ የዲዛይን መለዋወጥ፣ የፕሮጀክት ገንቢ አካላት አቅም አናሳ መሆን ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ያልተጠናቀቁ እንዲሁም ጊዜ እና ገንዘብ የናረባቸው ጥቂት የማይባሉ ፕሮጀክቶች ዛሬም አሉ።
2014 ዓ.ም በተለያዩ ምክንያቶች የተጓተቱ ፕሮጀክቶች የሚጠናቀቁበት እንደሚሆን ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል። ከታያዘላቸው ጊዜና በጀት ተጨማሪ በርካታ ዓመታትን እና በጀት ቅርጥፍ አድርገው የበሉ እና ግንባታቸው ገና ጅምር ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች የሚጠናቀቁበት ዓመት እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን ።
ይህንን ለማሳካት ለፕሮጀክቶች መጓተት ዋነኛ ማነቆ እየሆኑ ያሉ ችግሮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ ይገባል ። የለውጥ መንግስቱ ከመጣ ወዲህ የወሰዳቸውን ቆራጥ እርምጃዎች በአዲሱ ዓመትም አጠናክሮ መቀጠል አለበት። አሁንም በአንድ ኮንትራክተር የተያዙ ፕሮጀክቶችን ኮንትራክተሩ አቅም ላላቸው ጠንካራ ንዑስ ኮንትራክተሮች እንዲያከፋፍል የማድረግ እርምጃዎች መቀጠል አለባቸው። መሰል እርምጃ አንድም የኮንትራክተሮችን የአቅም እጥረት ችግር በመድፈን ፕሮጀክቶቹ እንዲፋጠኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ከዚህም ባሻገር የሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የሀገር ሀብት እንደመሆናቸው የኮንትራክተሮችን አቅም የማሳደግ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ለዚህም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ተገቢውን ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታዎችን ማመቻቸትን ይጠይቃል። የተቋማት አቅምን ማሳደግ፣ የግሉ ዘርፍ በተለይም የኮንትራክተር እና የአማካሪዎችን ማነቆዎችን መፍታት ላይ መንግስት ትኩረት አድርጎ ሊሰራ ይገባል። ይህ የኮንስትራክሽን ዘርፍን ማነቆዎችን ለመፍታት ትኩረት ተድርጎ መሰራት ካለባቸው ተግባራት አንዱ ሊሆን ይገባል።
የበርካታ ፕሮጀክቶች የችግር መሰረት እና አናት እየሆነ ያለውን የወሰን ማስከበር ችግሮችን ለመቅረፍ መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። የግል የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ቤቶች ብቻ ሳይሆን የመንግስት መሰረተ ልማቶች ጭምር በጊዜ አለመነሳት ለፕሮጀክቶች መጓተት ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ተስተውሏል። ምሱና እና ብልሹ አሰራር ሌላው በምክንያትነት የሚጠቀስ ነው። በመሆኑም በአዲስ ዓመት ከፌዴራል እስከ ወረዳ ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን በማጠናከር ችግሩን ለመፍታት ሊረባረቡ ይገባል። ከዚህም ባሻገር በዘርፉ የሚስተዋለውን የገንዘብ እና የጊዜ ብክነትን ለማስቆም አዳዲስ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግም ወሳኝ ነው።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም