በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘውን የውሃ ሀብት ለመስኖ ለማዋል የተሰራው ስራ ወደ ፊት ሊሰራ ከሚገባው ሰፊ ስራ ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ሆኖም ባለፉት ዓመታት የተሰሩ ስራዎች እንደ መልካም የሚወሰዱ መሆናቸው አያጠያይቅም። ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ከዝናብ ጥገኛ ግብርና ለማላቀቅ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ፕሮጀክቶቹ በተባለላቸው የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቁ አይታይም።
የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ ምክንያት እየሆኑ ያሉ በርካታ ተግዳሮቶች ይጠቀሳሉ። ከነዚህም መካከል የወሰን ማስከበር ፣ የፋይናንስ ችግር ፣ የቁሳቁስ ዋጋን መናር፣ ውጤታማ ያልሆነ የፕሮጀክት ዕቅድ፣ የጊዜ መርሐግብር ወይም የሀብት አስተዳደር፣ ለተጠናቀቁ ሥራዎች በሂደት ክፍያዎች መዘግየት እና በድርጅቶች ውስጥ በግንባታ ማኔጅመንት መስክ የተካኑ ባለሙያዎች አለመኖር እንዲሁም የዲዛይን ችግር ለፕሮጀክቶች መዘግየት እንደምክንያት ተጠቃሽ ናቸው።
በነዚህ ችግሮች ምክንያት በታለመላቸው የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ባለመጀመራቸው ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ከመዳረጓ ባሻገር ህብረተሰቡ ለተለያየ ቅሬታዎችን እንዲያነሳ ምክንያት ሲሆን ይታያል።
በዲዛይን ችግር ምክንያት ከተጓተቱት የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል ያዶት ፕሮጀክት አንዱ ተጠቃሽ ነው። ያዶት የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በመገንባት ላይ ከሚገኙት እና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ ያስገኛል ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው ትላልቅ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች አንዱ ነው።
በባሌ ዞን በዳሎመና ወረዳ በመገንባት ላይ የሚገኘው ይህ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ግንባታው የተጀመረው በ2011 በጀት ዓመት ሲሆን በ2014 በጀት ዓመት በማጠናቀቅ ለአርሶ አደሮች በማስተላለፍ የአካባቢውን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ግብ ተቀምጦ ነበር። በተለይም በአካባቢው የሚመረተውን የሰብል ምርትና ምርታማነት ከፍ እንደሚያደርገው ተስፋ ተጥሎበት እንደነበር ይታወሳል።
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ይህ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ሶስት ሺህ ሄክታር ማሳ ለማልማት የሚያስችል ሲሆን እስከ 12 ሺህ አርሶ አደሮችን የመስኖ ተጠቃሚ በማድረግ አርሶ አደሮችን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ ብሎም በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲያመርቱ የሚያስችል ነው።
ምንም እንኳ በ2014 በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እቅድ የተያዘ ቢሆንም እስከ 2013 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ የተገነባው አስር በመቶ እንኳ እንደማይሞላ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ መረጃ ያሳያል። 255 ሚሊዮን 118 ሺህ ብር በጀት የተያዘለት ይህ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት እስካሁን ድረስ 125 ሚሊዮን 706 ሺህ 173 ብር ክፍያ መፈጸሙንም መረጃው ያመላክታል። በ2014 በጀት ዓመት ፕሮጀክቱን 30 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል።
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ዳባ እንደሚሉት፤ ከኦሮሚያ ክልል በአሁኑ ወቅት ሁለት ትላልቅ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ያዶት ፕሮጀክት ደግሞ በክልሉ ውስጥ በአሁኑ ወቅት በመገንባት ላይ ካሉት ሁለት ትላልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው።
በባሌ ዞን እየተገነባ ያለው ያዶት እና በምስራቅ ሸዋ እየተገነባ ያለው ወለንጪቲ ፕሮጀክቶች በክልሉ በአሁኑ ወቅት በመገንባት ላይ የሚገኙ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ናቸው። ሁለቱ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የክልሉን የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ቁጥር ወደ አራት የሚያሳድጉ ይሆናል።
ያዶት ፕሮጀክት ግን በሁለት ዋና ዋና ችግሮች ምክንያት በታሰበው ፍጥነት እየሄደ አይደለም። እስከ 2013 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ የፕሮጀክቱን 42 ነጥብ 98 በመቶ ማጠናቀቅ ተችሎ እንደነበር የሚያነሱት አቶ ተፈሪ በዲዛይን ችግር ምክንያት ፕሮጀክቱ ዳግም እንዲከለስ ተደርጓል። ፕሮጀክቱ ዳግም ሲከለስ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ወደ 6 በመቶ መውረዱን ነው የጠቆሙት።
ዲዛይኑ እንደገና መከለስ እና መጽደቅ ግድ ስለሆነበት እንደገና ተከልሶ በቅርቡ መጽደቁን ጠቁመዋል። ዲዛይኑ ሲከለስ ወደ 70 በመቶ የሚሆን ተጨማሪ ስራ መምጣቱን የሚናገሩት አቶ ተፈሪ፤ መጽደቅ ነበረበት። ፕሮጀክቱ በመከለሱ ምክንያት ስራው በመጨመሩ ምክንያት ፐርሰንቱ ተመልሶ ወደ ኋላ መምጣቱንም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ተፈሪ ማብራሪያ ከዲዛይን ችግር በተጨማሪ የሲሚንቶ እጥረት የፕሮጀክቱን ግንባታ ሲፈታተን ቆይቷል። በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት ባለፈው ዓመት ይህ ነው የሚባል ስራ መስራት አልተቻለም። በአሁኑ ወቅት የሲሚንቶ ችግር የሚፈቱ እርምጃዎች ተወስደዋል። የዲዛይን ችግርም በክለሳ ተፈቷል። ፕሮጀክቱን ሲያጓትቱ የነበሩ ሁለቱ መሰረታዊ ችግሮች የተፈቱ በመሆናቸው በተያዘው 2014 በጀት ዓመት የፕሮጀክቱን ግንባታ ለማፋጠን ግብ ተቀምጧል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2013