ፍሬህይወት አወቀ
የኢትዮጵያ ከተሞች የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር መሰረታዊ ችግሮች እያደር እየተባባሰባቸው የመጡ ስለመሆናቸው እማኝ መጥቀስ አያሻቸውም። የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም የከተሞቹን መሰረታዊ ችግር ለማቃለል ‹‹አደጋን የሚቋቋም፤ አረንጓዴና ተደራሽ የከተሞች ልማት›› የሚል በመንግስት የጸደቀ ፖሊሲን በ2005 ዓ.ም ሥራ ላይ አውሏል። ይሁንና በፖሊሲው ችግሩን ለመፍታት ከተደረገው ጥረት በላይ የከተሞቹ ችግር በእጥፍ እየጨመረ ዛሬ ላይ ደርሷል።
በተለይም የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሀገሪቱ ጤናማ ያልሆነ የከተማነት ትራንስፎርሜሽን ስለመኖሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለዚህም ከተሞች በቂ የመሰረተ ልማት የሌላቸው፣ ጥራትና ስፋት ያለው የማህበራዊ አገልግሎት አለማግኘታቸው፣ ሰፊ የሆነ የመኖሪያ ቤት እጥረት ፣ የመዝናኛ ቦታና የአካባቢ ብክለት መኖሩ እንዲሁም የከተሞች አከታተም ከገጠር ጋር የጠነከረ ትስስር ያልነበረው መሆኑን በማሳያነት ያቀርባሉ።
ከተሜነት ማለት በራሱ ምን ማለት ነው? ከከተሞች አከታታም ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሔው ምን ይሆን? በማለት ላነሳንላቸው ጥያቄ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ፕላን ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ፍሬው መንግስቱ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።
የከተማነት ትራንስፎርሜሽን በአግባቡ መመራት ካልቻለ አሁን የሚታዩት ችግሮች ከዚህ የከፉ እንዳይሆኑ ያላቸውን ስጋት በመግለጽ፤ የከተሜነት ባህሪ ውስብስብና ፈታኝ የሆኑ ችግሮች አሉት ይላሉ። ‹‹ከተማ ማለት በህግ በተሰጠው አግባብ ማዘጋጃ ቤት የተቋቋመለት፣ ሰፊ ቁጥር ያለው ህዝብ የሚኖርበትና 50 በመቶ የሚሆነው የማህበረሰብ ክፍል ከግብርና ውጭ በሆኑ ማለትም በንግድ፣ በአገልግሎት፣ በኢንቨስትመንትና በመሳሰሉት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ የተሰማራ ህዝብ ያለበት ስብስብ ነው።›› ይህ ትርጉም ከተማነትን ከሌሎች ትርጓሜዎች በተሻለ ሁኔታ ማስረዳት ይችላል በማለት ዶክተር ፍሬው ሀሳባቸውን ይቀጥላሉ።
የከተማነትን ባህሪ የሚገልጹ ሁለት መመዘኛዎች አሉ። አንደኛው የከተማነት መጠናችን ሲሆን፤ ሁለተኛው የከተማነት የዕድገት ፍጥነት ምጣኔ ነው። እነዚህ ሁለቱ በከተማ ትራንስፎርሜሽን ቁልፍ ጉዳዮች በመሆናቸው ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ። በአሁን ወቅት የሀገሪቷ የከተማነት መጠን ሲለካ ብዙዎች 25 በመቶ ላይ ነው ቢሉም በአማካኝ ከ20 እስከ 22 በመቶ እንደሚሆን ይገመታል። ይህ ማለት ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ መካከል 20 በመቶው የሚሆነው ህዝብ በከተማነት ይኖራል እንደማለት ነው። ለአብነትም 100 ሚሊዮን ህዝብ ቢኖር 20 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ ብቻ በከተማ ውስጥ ይኖራል ማለት ነው።
የከተማነት የዕድገት ፍጥነቱን በተመለከተም ላለፉት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ የከተማነት ዕድገት በየአመቱ የአራት ነጥብ ሶስት በመቶ እድገት ያሳይ ነበር። አሁን ግን በየዓመቱ አምስት ነጥብ ሁለትና አምስት ነጥብ አራት በመቶ እያደገ ይገኛል። ይህ ቁጥር እጅግ በጣም አስደንጋጭ ነው። ምክንያቱም ኢኮኖሚው ሳይሻሻል ሁሉም ነገር ባለበት ሆኖ ከተሜነቱ ግን እየሰፋ መጥቷል። የአፍሪካ የከተማነት እድገት በአማካኝ በዓመት 40 በመቶ ነው። እኛ ሀገር ላይ ግን ገና 20 በመቶ ማለትም ዝቅተኛ የከተማነት መጠን ላይ እያለን የዕድገት ምጣኔው ደግሞ ፈጣን ነው።
የከተማ ህዝብ እያደገ የሚሄደው በአራት ሁኔታዎች መሆኑን የሚያነሱት ዶክተር ፍሬው፤ አንደኛው በተፈጥሮ ወይም ከሚሞተው የሚወለደው ቁጥር ሲጨምር ነው፣ ከዚህ ውጭ የከተማ ህዝብ የሚጨምረው በዋናነት የገጠር ከተማ ፍልሰት ነው። ይህ የገጠር ከተማ ፍልሰት ደግሞ በሀገሪቱ እጅግ እየፈጠነ ይገኛል። ለዚህም አሁን ላይ መፍትሔ ካልተሰጠ ነገ ከነገ ወዲያ ችግሩ የከፋ ይሆናል።
ሌላው መሰረታዊ ችግር የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ወይም የእድገት ደረጃ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ ነው። ዝቅተኛ በሆነ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ የሆነ ቁጥር ከገጠር ወደ ከተማ ይፈልሳል። ፈልሰው ለሚመጡ ሰዎች ደግሞ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ደካማ በመሆኑ በቂ የሆነ መሰረተ ልማት አይቀርብላቸውም። ስለዚህ ከህዝቡ ቁጥር ጋር ኢኮኖሚው አብሮ አያድግም። ስለዚህ ሰዎች ሳይወዱ በግድ በኢመደበኛ እንቅስቃሴ ውስጥ ለማለፍ ይገደዳሉ። ይህም በሀገሪቱ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑ ይታመናል።
የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከገጠር ወደ ከተማ ፈልሰው ለሚመጡ ዜጎች በቂ አገልግሎት፣ የስራ ዕድልና መሰረተ ልማቶችን ማቅረብ ካልቻለ ዜጎች የሚያዋጣቸውን መንገድ ይመርጣሉ። ምክንያቱም ሰዎች በፈቃደኝነት መሞት የሚችሉ ፍጡሮች አይደሉም የሚሉት ዶክተር ፍሬው፤ የተለያዩ የኢመደበኛ እንቅስቃሴ አይነቶችን በማሳያነት አቅርበዋል። ለአብነትም በርካቶች መጠለያ ሲያጡ ጨረቃ ቤት ሰርተው መኖር፣ በጉልበትና በሌሎች ህገወጥ ንግድ መተዳደር፣ ጎዳና ተዳዳሪ መሆንና ሌላም ሌላም ማሳያዎችን አንስተዋል። በአሁን ወቅት ታድያ በሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ የኢመደበኛነት እንቅስቃሴ ተንሰራፍቶ መታየቱም ከመንግስት መቅረብ የሚገባቸው መሰረታዊ ግልጋሎቶች ካለመቅረባቸው ጋር ተያይዞ መሆኑን ይናገራሉ።
በውጭው ዓለም ከተሜነት እና የኢንዱስትሪ ስብስብ አንድ ላይ የተገናኘ ነው። ይህም ማለት ከተሞች ሲስፋፉ ኢንዱስትሪውም አብሮ ተስፋፍቷል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ከተሜነቱ ከኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ጋር አንድ ላይ አልተሳሰረም። ከተሞች እየታጨቁ ያሉትም ከገጠር ወይም ከግብርናው ተላቅቀው ወደ ከተማ በሚመጡ ዜጎች ነው። እነዚህ ከገጠር ወደ ከተማ የሚመጡት ዜጎች ደግሞ የተማሩ ያልተማሩ በመሆናቸው ባሉት ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረው መስራት አይችሉም ። ስለዚህ ወደ ኢመደበኛ እንቅስቃሴ ሊገቡ የግድ በመሆኑ የሀገሪቱ የከተማነት ትራንስፎርሜሽን መገለጫ ዋና ባህሪያት ሆነዋል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ እየተባባሰ የመጣውን ፍልሰት ማቆም አይቻልም፤ ነገር ግን በአግባቡ መምራት ያስፈልጋል። ለዚህም ጊዜው አሁን በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ። ከገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት እየተመራ ያለበት መንገድ አሳሳቢነቱን በማንሳት እስካሁን ከአጠቃላይ የሀገሪቷ ህዝብ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ 30 በመቶ ድርሻ ነበረው። ይሁንና አሁን ግን የክልል ከተሞች እያደጉ ስለመጡ ቁጥሩ ሊቀንስ ይችል ይሆናል። ሆኖም የህዝቡ ብዛት ዕለት ተዕለት እየጨመረ የሚሄድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በከተሞች የሚስተዋለው ችግር እየጎላ ነው።
የከተማ ጥናት ባለሙያዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ 50 በሚደርሱ የዓለም ሀገራት ላይ የከተማነት ባህሪን አጥንተዋል። ያገኙት ውጤትም የገጠር ከተማ ፍልሰት የሚቆመው የሀገሪቱ ህዝብ 80 በመቶ ከተሜ መሆን ሲችል እንደሆነ አመላክቷል። ይህ ማለት ደግሞ 80 በመቶ የሚሆነው የከተማ ህዝብ 20 በመቶ የሚሆነውን አርሶአደር ይመግባል ማለት ነው። በቁጥር ጥቂት የሆነው አርሶ አደር ሰፊውን ከተሜ መመገብ እንዴት ይችላል ተብሎ አይጠየቅም ምክንያቱም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ነው።
ይህ የከተማነት መጠን 80 በመቶ ሲደርስ የሚቆም ከሆነ ሀገሪቷ አሁን ካለችበት 20 በመቶ ከተሜነት 80 በመቶ ለመድረስ መስራት ያለብንን የቤት ሥራ ዛሬ ላይ ሆነን ማዘጋጀት አለብን የሚሉት ዶክተር ፍሬው፤ ያ ካልሆነ ግን ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እንደሚሆኑና አስፈሪ እንደሆነም ይናገራሉ። የተለያዩ ሀገራት የከተማነትን መስፋፋት ለማቆም ሞክረዋል ነገር ግን ከተማነትን ማቆም አይቻልም። ምክንያቱም የሰዎችን የእርካታና የደስታ መሻት መገደብ አይቻልም። ሰዎች ሁልጊዜ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሱትም በገጠሩ ያጡት ነገር በመኖሩና የተሻለ ነገር አገኛለሁ በማለታቸው እንዲሁም ተፈጥሯዊ መብት በመሆኑም ጭምር ነው።
የከተሞች ጤነኛ እድገትና መስፋፋት ለግብርናውም መሰረት መሆን ይችላል። ነገር ግን ገበሬው ማትጊያ የለውም። አሁን ባለው ሁኔታ የአንድ ከተማን ህዝብ እየቀለቡ ያሉት አራት ገበሬዎች መሆናቸውን የሚያነሱት ዶክተር ፍሬው፤ ይህ ቁጥር ቢዘዋወር ደግሞ አንድ ገበሬ አራት ከተሞችን ይመግባል እንደማለት ነው። አንዱ ገበሬ አራት ከተሞችን ለመመገብ በባህላዊ ዘዴ አይችለውምና መትጋት እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የግድ ይለዋል። ስለዚህ ጤናማ የከተሞች እድገት ካለና በጤናማ መንገድ የከተማ እድገት ከተመራ ለግብርናው ልማት ወሳኝ ነው።
ሌላው ከተሞች የብሔር የሀይማኖትና የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችን ተከትለው የሚነሱ ግጭቶችን ማብረድ የሚችሉ እንደሆኑ ያነሱት ዶክተር ፍሬው፤ በከተሞች በስፋት የሚደረገው እንቅስቃሴ ንግድ፣ አገልግሎትንና ኢንዱስትሪዎች ላይ ነው። ውድድሩና ፉክክሩ በአብዛኛው ሥራና ሥራን ብቻ ማዕከል ያደረገ ነው። ምክንያቱም የተለያየ ብሔር፣ ሀይማኖትና አመለካከት ያላቸው በርካታ ሰዎች በጋራ የሚኖሩት በከተሞች አካባቢ ነው። እነዚህ ሰዎችም ስለሚሰሩት ሥራ እንጂ ሀይማኖት፣ ብሄርና ሌሎች የሚያለያዩ ጉዳዮች ላይ ሲያተኩሩ አይታዩም። በዚህም ከተሞች ውጥረትን ያበርዳሉ። በተለይም እንደ አኛ ሀገር ያሉ ከተሞችን ማሳደግ አሁን የሚታዩ ግጭቶችን ለማብረድ ይጠቅማል በማለት ያስረዱት ዶክተር ፍሬው፤ መርካቶ ውስጥ ያለውን የንግድ ትስስር እና የራጉኤል ቤተክርስቲያንና የአንዋር መስጊድ ትልቅ ምሳሌዎች መሆናቸውን አንስተዋል።
ይሁንና የገጠር ከተማ ትራንስፎርሜሽን እየተመራ ያለበት መንገድ ጤናማ ካለመሆኑ የተነሳ በአሁን ወቅት በተለይም አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች መታየት ጀምረዋል። ስለዚህ ከሀገሪቱ የመልማት ጥያቄ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለውን የገጠር ከተማ ትራንስፎርሜሽን በአግባቡ መምራት የሚያስፈልግ መሆኑንና እየተመራ ያለበትን መንገድም ማጤን አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ ።
በከተሞች የሚታየውን የመሰረተ ልማት እጥረት በማሟላት የስራ ዕድል መፍጠር ዋናው ቁልፍ ጉዳይ ነው ። ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር የሚችለው ኢንዱስትሪ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ መፈተሽም ይገባል። መንግስት ከኢንዱስትሪዎች አስቀድሞ ሲደግፋቸው የነበሩ አነስተኛና ጥቃቅን ላይ የሚሰራው ስራና አካሄዱ ጤናማ ነው ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። አብዛኞቹ በገበያ የማትጊያ ህግ ሲሰሩ አይታዩም፤ ኪራይ ሰብሳቢ እየሆኑ ቀርተዋል። የተሰጣቸውን ሱቅ ከዓላማው ውጭ በሆነ መንገድ በውድ ዋጋ አከራይተው ተቀምጠዋል። እንደዚህ አይነት ችግሮች መታረም አለባቸው። ይህ ካልሆነ የከተሞችን ኢኮኖሚ አሳድጎ ለሚፈልሰው ህዝብ መሰረተ ልማት ማሟላት አይቻልም።
የገጠሩ ወጣት ወደ ከተማ የሚፈልሰው መሰረታዊ በሆኑ ችግሮች ምክንያት በመሆኑ ከተሞች ዝግጁ ሆነው መጠበቅ እንጂ አትድረስብኝ ማለት አያዋጣም። ስለዚህ አዲስ አበባ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከአቅሟ በላይ የሆኑ ውስብስብ ችግሮች ታጭቀውባት ይታያል። ይሁንና የገጠር ከተማ ትራንስፎርሜሽኑ ያለበትን ችግር በመለየት መፍትሔ ሰጥቶ በአግባቡ መመራት እንዳለበት ዶክተር ፍሬው አበክረው ይገልጻሉ።
ከተሞች ለማስፋፊያ የሚጠቀሙት የገበሬውን መሬት ብቻ ነው። ነገር ግን የገበሬውን መሬት ብቻ መጠቀም ሳይሆን ልጆቹንም ወደ ኢኮኖሚው ማምጣት ያስፈልጋል። ይህን ለመተግበር ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የግድ ቢሆንም ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት የገበሬው ልጅ ቢያንስ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርለት ማድረግ ያስፈልጋል። የሥራ ዕድል መፍጠር ደግሞ የከተሞች ዕድገት መገለጫ ዋናውና ቁልፉ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም