የታላቁ ሩጫ ታላላቅ ባለድሎች

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ትናንት ለ24ኛ ጊዜ ሲካሄድ በወንዶች አትሌት ቢንያም መሐሪ በሴቶች ደግሞ አትሌት አሳየች አይቸው አሸናፊ ሆነዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ የ”ሌብል” ስያሜ ከተሰጠው በኋላ ”የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ሕጻናት” በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄድ፣ ትልቅ ስም ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ኬንያውያንና ዩጋንዳውያን አትሌቶችን አፎካክሯል።

በወንዶች መካከል በተካሄደው ፉክክር የአምናው የመድረኩ ባለድል አትሌት ቢኒያም መሐሪ ዳግም ባለድል የሆነበትን ውጤት አስመዝግቧል። ሠላሳ ያህል አትሌቶች እስከ ውድድሩ መጨረሻ እልህ አስጨራሽ ፉክክር ሲያደርጉ ወጣቱና ተስፋ የተጣለበት አትሌት ቢንያም በድንቅ ብቃት ለሁለተኛ ጊዜ አሸንፏል። አትሌት ቢንያም በታላቁ ሩጫ ዳግም ከማሸነፉም በላይ ከወራት በፊት በዓለም ከ20 ዓመት በታች 1500 ሜትር ክብረወሰን በእጁ እንዳስገባ ይታወቃል። አትሌት ይስማው ድሉና አዲሱ ነጋሽ እስከ ውድድሩ መጨረሻ ድንቅ ፉክክር ያደረጉ ወጣቶች ናቸው። አዲሱ ነጋሽ ከቢንያም መሐሪ ጋር አስደናቂ ፉክክርን አሳይቶ 2ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። አትሌት ይስማው ድሉ በበኩሉ ልምዱን በመጠቀም ፉክክሩን በሦስተኝነት ጨርሷል።

በሴቶች መካከል በተደረገው አስደናቂ ፉክክር አትሌት አሳየች አይቸው ከአምናዋ የውድድሩ አሸናፊ መልክናት ውዱና ሌሎች ድንቅ አትሌቶች ጋር ተፋልማ በግሩም አጨራረስ ለድል በቅታለች። አትሌት አሳየች አምና በሰርቢያ ቤልግሬድ ከ20 ዓመት በታች የዓለም ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና በግል የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በቡድን ወርቅ ማጥለቋ ይታወቃል። አትሌት የኔዋ ንብረት በፉክክሩ ለጥቂት ተቀድማ በሁለተኝነት ጨርሳለች። አትሌት ቦሰና ሙላቴ ጠንካራ ፉክክር አድርጋ ሦስተኛ ሆና አጠናቃለች።

ውድድሩ ፈታኝና ጠንካራ ከመሆኑ ባሻገር ትልቅ ደረጃ የሚሰጠው መሆኑን ባለድሉ አትሌት ቢንያም ተናግሯል። ውድድሩ ጥሩ ፉክክር እንደታየበትና ከአምናው በተሻለ አቋም ማሸነፉን የገለፀው አትሌት ቢኒያም፣ ሰፊ ዝግጅት ማድረጉንና የውድድሩ ስፍራ ዳገትና ቁልቁለቱ እንዲሁም ቅዝቃዜ ፈታኝ እንደነበረ አስረድቷል። እንደዚህ ዓይነት ትልቅ ውድድር መኖሩ ለታዳጊ አትሌቶች ተነሳሽነት እንደሚፈጥርም ገልጿል። በቀጣይም ጠንክሮ በመሥራት በዓለም መድረኮች ሀገሩን ወክሎ ማሸነፍ እንደሚፈልግ ጠቁሟል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ1993 ዓ.ም ከተጀመረ ወዲህ በየዓመቱ የሚከናወነው ዓለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር በርካታ ታላላቅ አትሌቶች አሸንፈውበታል።

የውድደሩ ዋና መሥራች ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ የውድድሩ አሸናፊ ከሆኑ ኮከቦች አንዱ ነው። አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት፣ በሪሁ አረጋዊና አቤ ጋሻው ሦስት ሦስት ጊዜ ያሸነፉ ሲሆን በሴቶች ያለምዘርፍ የኋላው ሁለት ጊዜ አሸንፋለች። የዘንድሮው ባለድል አትሌት ቢንያም መሐሪ ከአምናው ጋር ውድድሩን ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ከነዚህ ታላላቅ አትሌቶች ጋር ታሪክ መጋራት ችሏል። ባለፈው ዓመት በተከናወነው የ23ኛው ዙር የታላቁ ሩጫ ውድድር በወንዶች ቢንያም መሐሪ በሴቶች ደግሞ መልክናት ውዱ ማሸነፋቸው ይታወሳል። የውድድሩ ክብረ ወሰን በሴቶች አትሌት ያለምዘርፍ የኋላ 31:15:51 የተመዘገበ ሰዓት ሲሆን በወንዶች አትሌት ድሪባ መርጋ ያስመዘገበው 28፡18:61 ነው።

ውድድሩ በርካታ ዓለም አቀፍ የጤና ሯጮችንም ማሳተፍ የቻለ ሲሆን፣ ከ20 በላይ የተለያዩ ሃገራት የመጡ ከ500 በላይ የጤና ሯጮችም ተሳትፈዋል። ውድድሩን ያሸነፉ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ 1ኛ ደረጃ 250 ሺ ብር፣ 2ኛ 150 ሺ ብር እና 3ኛ 100 ሺ ብር ተበርክቷል።

በትናንቱ ውድድር ትልልቅ ስም ያላቸውን አትሌቶችን ጨምሮ ከ50 ሺ በላይ ሰዎችን ሲያሳትፍ ይህም ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሉሲ(ድንቅነሽ) ቅሪተ አካል የተገኘበት 50ኛ ዓመትን በማስመልከት መሆኑ ተገልጿል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You