የሴቶች ሙሉ ልብስ- የዲዛይነሯ አዲስ መንገድ

ዲዛይነር ሉሲ ጎይቶም ትባላለች። ለወንዶች፣ ለሴቶችና ለህጻናት የሚሆኑ ሙሉ ልብስ (ሱፍ) ለደንበኞቿ በትእዛዝ ትሠራለች:: በዚህ ሥራም ሁለት ዓመት ቆይታለች:: ወደዚህ ሥራ እንድትገባ ያደረጋት ምክንያት የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ የሙሉ ልብሶችን የመሥራት ፍላጎት ነው። በተለይ ባደረገችው ጥናት በአብዛኛው ሴቶችን ያማከለ የሙሉ ልብስ ሥራ እንደልብ እንደማይገኝ ማረጋገጥ መቻሏ ነው::

‹‹ለራሴ ልብሶችን ስለብስ ድምጻውያን የሚጠቀሙት አይነት ልብስ ነበር የምለብሰው›› የምትለው ዲዛይነሯ፤ በፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ13 ዓመቷ ጀምሮ ስትሳተፍ መቆየቷን ትናገራለች። በልጅነቷ በቴሌቪዥንን በመሳሰሉት ታዳምጣቸው የነበሩ ሙዚቃዎችና ድምጻውያኑ የሚለብሷቸው ልብሶች ይማርኳትም እንደነበርም ትናገራለች::

ትውልድና እድገቷ በዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆንም የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች በቤተሰቦቿ ሥራ ምክንያት በሳዑዲ አረቢያም ኖራለች:: በዚያም የመሰናዶ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ለመከታተል ወደ ሀገሯ ትመለሳለች:: ከዚያም ባህርዳር ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅላለች:: በዩኒቨርሲቲው በኢንጅነሪንግ (ምህንድስና) የትምህርት ክፍል ተመድባ ትምህርቱን በትጀምርም፣ የሉሲ ፍላጎት ወደ ፋሽን ያደላ በመሆኑ መምህራኖቿ ከመጠቆምም አልፈው፣ በዩኒቨርሲቲው የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ክፍል እንድትገባ ሃሳብ አቀረቡላት:: ሉሲም ጥያቄውን ሳታቅማማ ተቀበላ የመግቢያ ፈተናውን አልፋ ትምህርቷን ጀመረች ::

ከአምስት ዓመት በላይ የሚሆነውን እድሜዋን በአረብ ሀገር ያሳለፈችው ሉሲ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለመላመድ ጊዜ ወስዶባት እንደነበርም ታስታውሳለች:: በመሆኑም የባህርዳር ትምህርቷን ሳታጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ የፋሽን ዲዛይን ትምህርትን ለአንድ ዓመት ያህል ተከታተለች:: ይህም መልካም አጋጣሚ ይዞላት መጣ፤ በጊዜው በጅምር ላይ የነበረው የሀብ ኦፍ አፍሪካ የፋሽን ሳምንት ላይ ሥራቸውን የሚያቀርቡ ዲዛይነሮችን በረዳትነት ለማገዝ በበጎፍቃደኝነት እንድትሳተፍ እድሉን ሰጣት:: ይህ አጋጣሚም በይበልጥ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ ዲዛይነሮችን እንድትተዋወቅ ምክንያት ሆናት::

‹‹በኬንያ ስለሚገኝ የፋሽን ትምህርት ቤት ወንድሜ ጥናት አድርጎ ኬንያ ሄጄ ለሁለት ዓመት የፋሽን ዲዛይን ትምህርትን በተሻለ ሁኔታ ለመማር ችያለሁ›› የምትለው ዲዛይነር ሉሲ፣ ለሙያው ያላትን እውቀት ለማዳበር በሀገር ውስጥ ባሉ ትምህርት ቤቶች ብቻ መማር በቂ እንዳልነበር ትገልፃለች:: ይህንን ለማሳካት የቤተሰቦቿ ድጋፍ እንዳልተለያት ትገልፃለች:: በኬንያ ቆይታዋ ስለ ፋሽን ዲዛይን የቀሰመችው እውቀት ተግባር ተኮር እንደነበረና ቶሎ ወደ ሥራ ለመግባት እንደጠቀማትም ገልጻለች::

ዲዛይነር ሉሲ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ወደ ሥራ ለመግባት ጥናት ማድረግ ጀመረች:: በውጤቱም በገበያ ማዕከሎችና የልብስ ዲዛይን ሥራ በብዛት የሚገኝባቸው ቦታዎች ላይ ተዘዋውራ ስትመለከት ለሴቶች ተብሎ የሚዘጋጅ ሙሉ ልብስ እንደሌለ ተረዳች:: ይህንን ክፍተት ለመሙላት በዚህ ዘርፍ ላይ መሠማራትን ምርጫዋ አደረገች።

‹‹በሙሉ ልብስ ዝግጅቱ በይበልጥ ያተኮርነው ሴቶች ላይ ይሁን እንጂ ለወንዶችና ለህጻናትም እንሠራለን›› የምትለው ዲዛይነሯ፤ ገበያው ውስጥ ያለው ክፍተት የሙያ አቅጣጫዋን እንደወሰነው ትገልፃለች። በውጤቱም ለሴቶች ለህጻናትም ሆነ ለወንዶች በጥራትና በዲዛይን አንድ ደረጃ ከፍ ብለው የሚሠሩ ሙሉ ልብሶችን መሥራት ጀመረች::

የዲዛይኗ ስያሜም ‹‹ሉጎቴይለር›› /lugotailor/ የሚል ነው:: ይህ የምርት ስም (Brand) ዲዛይነር ሉሲ የእሷን እና የአባቷን ስም የመጀመርያ ፊደል በመጠቀም ለየት እንዲል በሚል ያወጣችው መሆኑን ትገልጻለች:: በባህሪዋም ያልተለመደ ዲዛይን ያላቸው /ወጣ ያሉ/ አልባሳት አድናቂ ስትሆን ይህንን ፍላጎት የሚያሟላላት ድርጅት ከፍታለች::

‹‹የደንበኞቻችን ፍላጎት አስቀድመን እንጠይቃለን:: ከምንጠቀመው ጨርቅ፣ ቀለም፣ ቁልፍ፣ ዚፕ ገበር እያንዳንዱን ግብዓት እያስረዳናቸው እንዲመርጡ እናደርጋለን›› የምትለው ዲዛይነሯ፣ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ ትገልፃለች:: ሙሉ ልብስ ስፌት ላይ የሰዎችን ምርጫ በእያንዳንዱ ግብዓት ላይ ማስመረጥ ያልተለመደ መሆኑን በማንሳትም በሚገኘው የመጨረሻው ውጤት (የልብሱ ውበትና ጥራት) ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ትገልጻለች::

‹‹በትእዛዝ ሥንሰራ ወንዶች ደንበኞቻችን ደስተኛ ነበሩ:: ነገር ግን ሴቶችን ለማስለመድ ትንሽ ጊዜ ወስዶብናል›› የምትለው ዲዛይነሯ ለሴቶች የሚዘጋጁ ሙሉ ልብሶች በተለያዩ ሁነቶች ላይ፣ የሥራ ቦታዎች፣ ንግግር ለማድረግ በሚዘጋጁበት መድረክ አልያም ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ መልበስ የሚችሏቸው እንደሆኑ ትናገራለች:: በአሁኑ ወቅት በተለያየ የሥራ ዘርፍ ላይ የሚገኙ እንስቶች ደንበኞቿ መሆናቸውን ተናግራለች::

‹‹ደንበኞቼን ከተለመደው ወጣ ያለ ዲዛይን ተጠቅመው እንዲሞክሩት አበረታታቸዋለሁ:: ለሁሉም ደንበኞቻችን አዲስ ዲዛይን አውጥተን እንሠራለን›› የምትለው ዲዛይነሯ፤ ደንበኞች በመረጡት የጨርቅ አይነት እና ዲዛይን ከተስማሙ በኋላ ልኬት ተወስዶ የቀጠሮ ቀን እንደሚሰጣቸው ትናገራለች:: ልብሱ ከመድረሱ በፊት አስቀድመው እንዲለኩት እና ችግር ካለው እንዲስተካከል እንደሚያደርጉም ትናገራለች::

ዲዛይነሯ ሁሉም ጨርቅ ሙሉ ልብስ (ለሱፍ) አይሆንም ትላለች። ከጥጥ የተሠሩ፣ ካሽሚር (ከፍየል ጸጉር የሚሠራ) ጨርቅ፣ ሱፍ /ውል/ ለወንዶች ሱፍ በብዛት የሚውል እና ሌሎች የጨርቅ አይነቶችን ለሥራዋ ውጤታማነት እንደምትጠቀም ታስረዳለች። ግብዓቶቹንም ከተለያዩ ሀገራት በማምጣት ሥራ ላይ ታውለዋለች::

ዲዛይነር ሉሲ በሥራዋ በርካታ ደንበኞችን እንዳገኘች ትናገራለች። በተለይ የረጅም ጊዜ የሀገር ውስጥም የውጭ ዜጋ የሆኑ ደንበኞችን አፍርታለች። በኢትዮጵያ ፍላጎት መሠረት ያደረጉ በሙሉ ልብስ ዲዛይን ላይ ከዚህም በላይ መሥራትና ደንበኞችን ማፍራት እንደሚቻል ትገልጻለች::

‹‹ከደንበኞቿ አብላጫውን ቁጥር የሚወስዱት ወንዶች ቢሆኑም፣ አሁን አሁን በርካታ ሴት ደንበኞች እያፈራሁ ነው›› ትላለች:: ወደፊት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ የምርት ስም (Brand) መገንባት እንደምትፈልግ ገልፃልናለች::

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You