ኑ! ጎመን ‘እናጠንዛ’

ከብሂሎቻችን መካከል ብስጭት የሚያደርገኝ ‘ሴት በዛ፣ ጎመን ጠነዛ’ የሚለው ነው። ሴቶች ሰብሰብ ሲሉ ጨዋታና ወግ ያበዛሉ ነው ነገሩ። ምንአልባት ያኔ…ማለቴ ይህ ብሂል ‘በተፈለሰፈበት’ ዘመን ሰብሰብ ብሎ ሃሳብን የመግለጥና የማውራት ልማድ ጥቅሙ አልታወቀም ነበር መሰለኝ።

ዛሬ ላይ እንደ አሸን የፈሉ የሚመስሉን አነቃቂ ንግግር አድራጊዎችና አበረታቾች እንደሚሉት ከሆነ፥ እንደቀደመው ዘመን ሰዎች በተለይም በወሬ የምንታማ ሴቶች ቁጭ ብለን የልብ የልባችንን ማውራት ትተናል። ቡና ተጠራርቶ መጠጣት እየቀረ ይመስላል። በእርግጥ ነገሩ በጥናት የተረጋገጠ አይደለም፣ አሁንም ተጠራርተው ቡና የሚጠጡ አሉ። ምንአልባት ቦታውና ሁኔታው ተቀይሯል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙዎቻችን ‘ጊዜ የለንም’ የምንል ነን።

ግን ጥቅሙ ቀላል አይደለም። አሁን ላይ ዓለምን የሚዘውረው ፖለቲካ እንዲህ ሰላም ያጣው ጎመን ማጠንዛት ለሚችል ደቂቃ ቁጭ ብሎ መነጋገር ስላልቻለ ነው። ጊዜ የቆጠብን እየመሰለን በጋራ ቁጭ ብለን የምናሳልፋቸውን ጊዜዎች ቸል ብለናቸዋል፣ ንቀናቸዋል። እውነት ነው! ዝም ብሎ ጊዜን በዋዛ ፈዛዛ ማባከን ተገቢ አይደለም። ግን ደግሞ ሰብሰብ ብሎ ከጨዋታ ጋር ቁም ነገርን፣ የሆድ የሆድን፣ ገጠመኝን፣ ችግርን፣ ብሶት መከፋትን፣ ቁጭትን ማውሪያ፣ መተንፈሻ ጊዜ ያስፈልገናል።

“ከተገናኙ ቁጭ ብለው ሲያወሩ ነው የሚውሉት” የሚባልልን ሴቶች፥ ድሮ ድሮ እንዲህ እንደ ቡና መጠጣት፣ ማኅበርና እድል ከመሳሰለው የመሰባሰብ አጋጣሚ አንዳች መፍትሔ እናገኝ ነበር። ያገኙም ጥቂት አይደሉም። ለምሳሌ ቀደም ብለው ትዳር የመሠረቱ እህቶች ለአዲሷ ሙሽራ ሃሳብ ያካፍሏታል። ልጇን ስታሳድግ ምን ብታደርግ ጥሩ እንደሆነ፣ ሥራዋንና ቤቷን እንዴት አድርጋ ማስኬድ እንደምትችል፣ ውበቷን መጠበቂያ መንገዶች ምን እንደሆኑ…ብቻ እንደየአውዱ ሃሳብ ይከፋፈላሉ።

ይህን ስል እንከን አልባ ነው እያልኩኝ አይደለም። የሚለዋወጡት ሃሳብ፣ የሚሰጡት ምክር፣ የሚያካፍሉት ልምድ ከሚያውቁት ከኖሩበት ነውና እሱን አንሞግትም። ግን በማንኛውም አጋጣሚ የሰዎች ሰብሰብ ብሎ ለመደማመጥ ተዘጋጅቶ መቀመጥ መቻል መልካም እድል ነው ብዬ አምናለሁና ነው። እናም ሴቶች ሰብሰብ ብለው መምከራቸው ለምን ተተረተበት የሚለው ነበር እንዳልኳችሁ ‘ሴት በዛ ጎመን ጠነዛ’ የሚለውን ብሂል እንድጠላው ያደረገኝ።

አሁን ግን ሳስበው፣ እንደውም ይጠንዛ! ከሆድ በላይ፣ ከጎመን የሚበልጥ የመኖር ጉዳይ እያለ፣ ስናወራ ውለን ብናድርስ! እስቲ እናውራ! በተለይ ጾታን መሠረት አድርጎ ስለሚደርስ ጥቃት! ምን እናድርግ? እንዴት እናድርግ? ከየት እንጀምር? ምን ይሻለናል? ብለን አብረን ጠይቀን አብረን መፍትሔውን እንፈልግ።

በሴት ልጅ ላይ ጾታዊ ጥቃት ያደረሰ ሰው የሞት ፍርድ ተፈርዶበት፥ በፍርዱም ተፈጻሚ የሆነባቸውና እንዲህ ያሉ ወንጀለኞችን በስቅላት የቀጡና የሚቀጡ ሀገራትን አይተናል፣ እያየንም ነው። እንደው የሚደረገው ግራ ሲገባ እንጂ፥ ሞትማ ጥቃት ደርሶባት የተገደለች ሴትስ ያለጥፋቷ አይደል የ’ሞት ፍርድ’ የተፈረደባት፣ ያውም ያለገላጋይ ያለጠበቃ፣ ያለይግባኝ ያለ አቤቱታ።

ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን ለማስቆም እንዲህ ያለ መንገድን የተጠቀሙ ሀገራት፥ ቅጣቱ አስተማሪና ሴቶችን ከጥቃት የሚከላከል ይሆናል ብለው በማመን ነው። ምን ያህል ውጤታማ ነው የሚለውን በተመለከተ ግን ምንም የተባለ ነገር የለም። ጉዳዩም አሁን ድረስ አነጋጋሪና ቁርጡ የታወቀ መስማማት ያልተደረሰበት ሆኖ ዘልቋል። ያም ሆነ ይህ ግን ፍትሐዊ ርምጃ የግድ ይላል። ፍትሕ ማኅበረሰብን አስተሳስሮ በሰላም የሚያቆይ ቁልፍ እሴት ነው።

ከዚህ ባለፈ ፍትሕ ተጓደለ ብዬ የማስበው፥ ጥቃት ያደረሰ ሰው በአግባቡ ቅጣት ሳይጣልበት ሲቀር ብቻ አይደለም። የተዛነፈ የልጅ አስተዳደግ ራሱ ፍትሕን ያጓድላል። ሴት ልጁን ‘ሴት ነሽ፣ አንገትሽን ዝቅ አድርጊ’ ብሎ እያሳደገ፥ ወንዱን ‘ቀና በል እንጂ ወንድ አይደለህ!’ የሚለው ገና በጠዋቱ ፍትሕን አጓድሏል። እህቱን ‘ኮስተር በይበት! ራስሽ ስቀሽለት ነዋ!’ እያለ፥ በዛ በኩል ወዳጁን ‘ወንድ አይደለህ! ለሴት ልጅ የምን ፊት ማሳየት ነው’ የሚለው ፍትሕን አዛንፏል።

እነዚህ ‘ቻይው’ የተባለች ሴትና ‘በርታ’ የተባለ ወንድ፣ ኑሮና ሕይወት በተባለው ሜዳ አንድ ላይ ይሠማራሉ። የተሠሩበት መንገድ ደግሞ አንዱን ጭምት ሌላውን ጥቃት ለመፈጸም የተዘጋጀ አድርጎታል። እንግዲህ ከዚህ በላይ ፍትሕን ማጓደል ከወዴት አለ? ይህ ራሳችን የሠራናቸው በጎችና ራሳችን የፈጠርናቸውን ተኩላዎች በአንድ ሜዳ ማሠማራት ብንለው ትክክል አይደለም?

እስቲ ኑ! ጎመኑ ይጠንዛ! እንነጋገር! ወንድ ልጆቻችን እንዴት ነው አስተዳደጋቸው? ወንድሞቻችን ጠባያቸው ምንድን ነው? አንድ “ሥርዓት አለው” የምንለውን ወንድ ልጅ ያሳደገ ቤተሰብ ምን መንገድ ተጠቀመ?

ሴት ልጅን በሥርዓትን በሕግ፣ በደንብና በመመሪያ ውስጥ ለማሳደግና ለማኖር ብዙ ጊዜ ሰጥተናል። ይህም የሆነው ይመስለኛል በሴቷ ጠንቃቃነት ብቻ ደኅንነቷ ይጠበቃል ብሎ በማመን ነው። እስቲ ወዲህ መለስ እንበል ደግሞ። ወንድ ልጆችን እንዴት እናሳድግ፣ ምን ይሻላል ብለን ጎመን የሚያጠነዛ ምክክር እናድርግ፣ ጊዜ እንስጠው። ዛሬ ከፍርድና ፍትሕ ተቋማት የምንጠይቀውን ፍርድና ብይን፣ ነገም ልጆቻችን ከዛው ተቋም ብቻ እየጠበቁ እንዲኖሩ አንፍረድባቸው። ቢያንስ ለቀጣዩ ትውልድ ደግሞ እየመከርን እንሞክር።

ሂላርያ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You