ኢራን የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለፀጋ ኤለን መስክ እና በመንግሥታቱ ድርጅት የሀገሪቱ አምባሳደር አሚር ሳይድ ኢራቫኒ በምስጢር ተገናኝተው ተወያይተዋል መባሉን አስተባበለች።
ኒውዮርክ ታይምስን ጨምሮ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ቢሊየነሩ መስክ እና በተመድ የኢራን አምባሳደር በምስጢር መወያየታቸው ምንጮቻቸውን ዋቢ አድርገው መዘገባቸው ይታወሳል።
ኒውዮርክ ታይምስ በተለይም የኢራን ባለሥልጣናት ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው በኒውዮርክ የተካሄደው ምክክር ከአንድ ሰዓት በላይ የቆየ ነበር።
ምክክሩ የአሜሪካ እና ኢራንን የሻከረ ግንኙነት ለማስተካከል ያለመ እንደነበርም ነው ዘገባው የጠቀሰው።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫው፣ ቢሊየነሩ መስክ እና በተመድ የኢራን አምባሳደር መካከል ሚስጢራዊ ውይይት ተደርጎ ነበር መባሉን በጽኑ አስተባብሏል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፣ በኢራን የተመድ አምባሳደር እና የተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የቅርብ አማካሪ በሆኑት ኤለን መስክ እና በኢራን የተመድ አምባሳደር መካከል ተደርጓል የተባለው ውይይት ፍጹም ሐሰት ነው በማለት አስተባብለዋል።
ይህ የአሜሪካ ሚዲያዎች የፈጠራ ወሬ ነው፣ ከጀርባው ምን አይነት ተልዕኮ እንዳለውም ግልጽ ነው፤ የፈጠራ ወሬ ነው ብለውታል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ በመግለጫቸው።
የኢራን አመራሮች በተመድ የሀገሪቱ ተወካይ ለሆኑት አምባሳደር አሚር ሳይድ የውይይት ፈቃድ እንዳልሰጠም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
“በአሁኑ ወቅት አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር በኢራን ላይ የሚያራምደውን ፖሊሲ ግልጽ እስከሚያደርግ እየጠበቅን ነው፣ የባይደን መንግሥት ፖሊሲ ላይ በመመሥረት የራሳችንን ፖሊሲ እናስተካክላለን፣ ለውይይት አሁን ጊዜው አይደለም” ብለዋል ሚኒስትሩ።
የትራምፕ ዳግም መመረጥ በኢራን ላይ “ከባድ ግፊት” ይፈጥራል ተብሎ ተሰግቷል።
የሪፐብሊካኑን ተመራጭ ፕሬዚዳንት የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን የሚያወሱ ተንታኞች ግን ትራምፕ በኢራን ላይ አዲስ ፖሊሲ የሚከተሉ አይመስልም ይላሉ።
አሜሪካን ከ2015ቱ የኢራን የኒዩክሌር ስምምነት በ2018 ያስወጡት ትራምፕ ቴህራን በስምምነቱ ተነስተውላት የነበሩ ማዕቀቦች ዳግም እንዲተገበሩ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ኢራንም የዩራኒየም ማበልፀግ ሂደቷን ከማፋጠን ባሻገር የነዳጅ የወጪ ንግዷን በእጅጉ ጨምራለች።
በመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የምታደርገውን ድጋፍ ማጠናከሯም ለአሜሪካ ዋነኛ አጋር እስራኤል ከፍተኛ ስጋት ደቅኖ እርስ በርስ ኃይላቸውን እስከመለካካት ደርሰዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም