የወንጀል ሕግ ምንነት

የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ዋናው /አጋፋሪው/ ሕግ የወንጀል ሕግ ነው:: የወንጀል ሕግ እንደ ፍትሕብሔር ወይም የንግድ ሕግ ስለ ግለሰቦች ሳይሆን በዋናነት ስለ ሕብረተሰብ ሰላም እና ደህንነት ሲባል የሚወጣ እጅግ መሠረታዊ ሕግ ነው:: በእርግጥ በሕግ ታሪክ ጥናት ውስጥም ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን የሜሶፖታሚያ፣ የግሪክ ወይን የሮም ጥንታዊ የሕግ ሥርዓቶችን ብናጠና ሥርዓቱ የተመሠረተበት ዋና ሕግ የወንጀል ሕግ ሆኖ እናገኘዋለን::

ታዲያ የወንጀል ሕግ ስንል የትኛውን ሕግ ማለታችን ነው ብለን ስንጠይቅ የወንጀል ሕግ ሲባል በዋናነት የሚያመለክተው የሀገራት የወንጀል ኮድን ነው:: ሀገራት የትኛውንም የሕግ ሥርዓት ቢከተሉም፤ በይዘቱ እና አቀራረፁ ልዩነት ከሌለ በቀር የወንጀል ኮድ የሌለው ሀገር ግን የለም:: በኢትዮጵያም በተለያየ ጊዜ የተለያዩ የወንጀል ኮዶች እየተቀረፁ እና እየተሻሻሉ ሥራ ላይ ውለዋል::

አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ የ1996 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ ተብሎ የሚጠቀሰው 865 አንቀፅችን በተለያዩ ክፍሎች እና ምዕራፎች ይዞ የሚገኘው ኮድ ነው:: እንደ ማንኛውም መሠረታዊ ሕግ ይህ ሕግ አቀራረፁ ከመርሆዎች ጀምሮ ከከባድ ወደ ቀላል ወንጀሎችን በቅደም ተከተል ድርደራ በማድረግ እና በመጨረሻም የደንብ መተላለፍ ጥፋቶችን እና ቅጣቶችን የሚደነግግ ነው::

ይህ ማለት ግን የወንጀል ድንጋጌ/ይዘት ያላቸው ሌሎች ሕግጋት የሉም ማለት አይደለም:: “በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት” ውስጥ ከ125 በላይ የሆኑ የወንጀል ድንጋጌ ይዘት ያላቸው ሌሎች አዋጆች አሉ:: ከእነዚህ አዋጆች መካከል አንዳንደቹ ራሳቸውን ችለው ስለ አንድ የተለየ ልዩ ወንጀል ለመደንገግ የወጡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007፣ በወንጀል የተገኘ ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ተያያዥ ወንጀሎችን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 ወይም በሰዎች መነገድን እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/2012 ለአብነት ልናነሳ እንችላለን:: ሎሌቹ አዋጆች ደግሞ ዋና መሠረታዊ ጉዳያቸው ሌላ ሆኖ ነገር ግን ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ የወንጀል ድንጋጌዎችን የሚይዙ ናቸው:: ለአብነትም የባንክ ሥራ አዋጅ፣ የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ወይም የብሔራዊ መዝሙር አዋጅን ልንመለከት እንችላለን::

የዚህ ፅሑፍ ዋና ትኩረት ግን የወንጀል ኮድ በመሆኑ ይህንኑ የተመለከቱ የተወሰኑ ጉዳዮችን እንደሚከተለው እናነሳለን:: ይህ የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ በዋናነት ሀገርን ለመጠበቅ፣ የሰዎችን ሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከመንግሥትም ይሁን ከሌሎች ሰዎች ጥሰት ለመከላከል የወጣ ሕግ ነው:: ይህ ሕግ የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት ለመጠበቅ እና ሰዎች በጋራ ሲኖሩ አንዱ የሌላውን ሕይወት እንዳያጠፋ ሰው መግደልን ከባድ ወንጀል አድርጎ ያስቀምጣል፣ የሰዎችን ክብር ለመጠበቅ ሰዎችን መሳደብ፣ ካለፍቃድ መንካት/መምታት ወይም አካል ጉዳት ማድረስን..ወዘተ ወንጀል አድርጎ ያስቀምጣል::

የሰዎችን የንብረት መብት ለመጠበቅ ስርቆትን፣ ውንብድናን፣ ማታለልን..ወዘተ ወንጀል አድርጎ ያስቀምጣል:: የሰዎችን ነፃነት ለመጠበቅ ሰውን መጥለፍ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የሰዎችን ጊቢ መድፈር.. ወዘተ ወንጀል አድርጎ ያስቀምጣል:: በእንዲህ መልኩ ማህበረሰብን እና የማህበረሰብ መሠረት የሆኑትን ግለሰቦች መሠረታዊ መብቶችን በዝርዝር ለመከላከል ይሠራል:: በሕጉ አፈፃፀም ላይ እንከኖች እስከሌሉ ድረስ የወንጀል ሕግ በጋራ ለመኖር የማይታይ ዋስትና ሆኖ ያገለግላል::

የወንጀል ሕግ በሚቀረፅበት ጊዜ የማይናወጡ መሠረታዊ መርሆዎች አሉት:: ከእነዚህ መርሆዎች መካከል አንዱ የሕጋዊነት መርህ ይባላል:: ይህ መርህ የሚያረጋግጠው የወንጀል ሕግ አስቀድሞ ተፅፎ መዘጋጀት እንዳለበትና የወንጀል ድርጊት ነው ተብሎ በግልፅ ባልተጠቀሰ ተግባር ሰውን መክሰስም ይሁን መቅጣት በሕግ ፊት ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ነው:: በሀገራችን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 2 ስር ይኸው መርህ ተቀምጧል::

ይህ ድንጋጌ “ፍርድ ቤት ሕገወጥነቱ በሕግ ያልተደነገን ድርጊት ወይም ግድፈት እንደ ወንጀል ሊቆጥረው እና ቅጣት ሊወስንበት አይችልም” ይላል:: ይህም ማለት በአጭሩ ሲገለፅ አስቀድሞ ካልተፃፈ በስተቀር ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ አስፈፃሚ አካል ወይም ፍርድ-ቤት ወንጀል ሊፈጥር አይችልም ማለት ነው:: ይህም መርህ በዜጎች ወይም በሰዎች መካከል መተማመንን ይፈጥራል:: ይህ መርህ በግለሰቦች መብት እና በማህበረሰብ ሰላምና ደህንነት መካከል ያለውን አጥር አስቀድሞ በፅሑፍ እንደማዘጋጀት ማለት ነው::

አንድ ግለሰብ በወንጀል ሕግ ወይም በሌሎች የወንጀል ድንጋጌን በያዙ አዋጆች የወንጀል ድርጊት ነው ያልተባለን ያልተገባ ወይም ኢ-ሞራሊያዊ ድርጊት ቢፈፅም እንኳን የሞራል ቅጣት ከህብረተሰቡ ያጋጥመው ካልሆነ በቀር አስቀድሞ ባልተፃፈ ጉዳይ በወንጀል ሊጠየቅ፣ በፖሊስ ሊያዝ እና ሊመረመር፣ በዐ/ሕግ ክስ ሊቀርብበት ወይም በፍርድ-ቤት ቅጣት ሊያርፍበት አይችልም ማለት ነው::

ነገር ግን የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ደረቅ ወንጀል ወይም ማህበራዊ ወንጀል ብለን ከምንጠራቸው ወንጀሎች ባለፈ ከህብረተሰብ ሞራል የሚቃረኑ፤ ለመልካም ባህርይ ተቃራኒ የሆኑ እንደ ግብረሰዶም እና ለንፅህና ክብር ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች፣ አመንዝራነት፣ በአደባባይ ፆታዊ ድርጊት መፈፀም…ወዘተ የመሳሰሉ ድርጊቶችን ሁሉ አስቀድሞ የወንጀል ድርጊት በማለት ይደነግጋል:: ይህም ሕጉ ለህብረተሰብ ባህል እና እሴት ከፍተኛ ዋጋ የሰጠ መሆኑን የሚያመላክት ነው::

እነዚህን እና ሌሎችን አስቀድሞ የተፃፉትን የወንጀል ድርጊቶች ሁሉ ማወቅ ደግሞ ግዴታ ነው:: ምክንያቱም ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት ስለማያድን እና ሌላኛው መርህም ይኸው በመሆኑ ነው:: በወንጀል ክርክር “ይህ ድርጊት ወንጀል መሆኑን አላውቅም ነበር” በማለት ከቅጣት ነፃ መሆን ፈፅሞ አይቻልም:: በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ በባህሪያቸው መብት የሚመስሉ ነገር ግን ወንጀል የሆኑ ጥቂት ጉዳዮች ያሉ ሲሆን እንዲህ አይነት ጉዳዮች ባጋጠሙ ጊዜ የወንጀል ሕግ ዋና ዓላማ ወንጀል የሚያስብን አእምሮ/ሃሳብ መቅጣት በመሆኑ ፍርድ ቤቱን ቅጣቱን በመሰለው ሊያቀል ይችላል::

ለምሳሌ አንድ ለጓደኛው 1000/አንድ ሺህ ብር/ ብድር ያበደረ ሰው ጓደኛው ብድሩን ባለመመለሱ ተናዶ ጥሩ ዱላ ይዞ እና አስፈራርቶ ገንዘቡን ቢቀበለው በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 436/ሐ ስር የተመለከተውን መብትን በሕገ-ወጥ መንገድ የማስከበር ወንጀል ፈፅሟልና በወንጀል ይጠየቃል:: ሆኖም ፍርድ-ቤቱ ይህ ሰው ይህንን ማድረጉ በእርግጥ መብቱ እንደሆነ ሙሉ ለሙሉ አምኖበት ነው የሚለውን በተለያዩ መስፈርቶች መዝኖ ካረጋገጠ ቅጣቱን በመሰለው መልኩ ሊያቀልለት ይችል ይሆናል::

ነገር ግን አንድ ሰው ሌላውን ሰው ሰርቆ የሰረቅኩት መስረቅ ወንጀል መሆኑን ስለማላውቅ ነው ወይም መስረቅ መብቴ መስሎኝ ነው በማለት ፍርድ-ቤት ቢናገር ዳኛውን ፈገግ ካላደረጋቸው በቀር በቅጣቱ ላይ አንዳችምለውጥ አያመጣም:: ምክንያቱም በየትኛውም ወንጀል ወንጀልን አለማወቅ መከላከያ ሊሆን ካለመቻሉም በላይ አብዛኞቹ የወንጀል ድርጊቶች መብት ከመሆን ጋር ግንኙነት የሌላቸው በመሆኑ ነው::

ሌላው መርህ የእኩልነት እና የቅጣት ግለሰባዊነት መርህ ነው:: ወንጀል የፈፀመ ግለሰብ ሁሉ ዘሩ፣ ጾታው፣ ፖለቲካ አመለካከቱ፣ ቀለሙ…ወዘተ ሳይታይ ሕግ ፊት መቅረብ እና መዳኘት አለበት:: አንድ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ጠንካራ ወይም ደካማ ሊባል የሚችልበት አንዱ መስፈርትም ይኽው ነው:: ይህንን የእኩልነት መርህ በየትኛውም የሕግ ሥርዓት ፍፁም በሆነ መንገድ መቶ በመቶ ይተገበራል ባይባል እንኳን ሂደቱ ወደ ፍፀምነት እያደገ ካልመጣ የሕግ ሥርዓቱ ውጤታማ ነው ለማለት አይቻልም:: ሁሉም ሰው በሕግ ፊት አኩል ነው:: ወንጀል ካልሠራ ነፃ ነው:: ወንጀል ከሠራ ደግሞ በወንጀል ፍትህ አስተዳደር አደደባባይ መቆም ይገባዋል:: ይህ ሲሆን ከሰውነት ውጭ ሌላ ሚዛን ሊኖር አይገባም:: የወንጀል ሕጋችን አንቀፅ 4 የሚለውም ይህንኑ ነው::

የእኩልነት መርህ በእንዲህ መልኩ የሚፈፀም ሆኖ ሳለ የወንጀል ቅጣት ሲጣል ግን የግለሰባዊነት መርህን ተከትሎ ነው:: ይህ መርህ በሕግ ሳይንስ (“ጁሪስፕሩደንስ”) ሁለት ትርጉም አለው:: የመጀመሪያው የወንጀል ቅጣት ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የማይተላለፍ መሆኑ እና ግለሰባዊ መሆኑ ነው:: በፍትሐብሔር ሕግ ልጅ ባጠፋው አባት፣ ሹፌር ባጠፋው ባለመኪና፣ ሠራተኛ ባጠፋው ድርጅት ክስ ሊቀርብበት እና ሊፈረድበት ይችላል:: በወንጀል ሕግ ግን ይህንን ማድረግ ክልክል ነው::

አባት በፈፀመው ወንጀል ልጅ ወይም ልጅ በፈፀመው ወንጀል አባት አይቀጣም:: ይህ መርህ በዘመናዊ የወንጀል ሕግጋት መሠረታዊ መርህ ሆኖ የቀረበ ሲሆን በቀደሙ ጊዜያት የነበረውን ኢ-ፍትሐዊ የወንጀል ቅጣት ትልልፍ ያስቀረ መርህ ነው:: በጥንት ሜሶፖታሚያ አንድ መሃንዲስ የተበላሸ ወይም ጥራት የሌለው ህንፃ ከገነባ ቅጣቱ የሚፈፀመው በልጆቹ ላይ ነበር:: ይህም ማለት አባት ባጠፋው ጥፋት ልጅን መቅጣት ሲሆን ይህ የቅጣት አሠራር በዘመናዊ የሕግ ሥርዓቶች ቀርቷል::

ሌላው የቅጣት ግለሰባዊነት መገለጫው ሁለት ሰዎች ተመሳሳይ ወንጀል በተመሳሳይ ሁኔታ ቢፈፅሙ ወይም ሁለት ሰዎች በጋራ ሆነው አንድ ወንጀል ቢፈፅሙ የሚጣለው ቅጣት ግን እንደ ግለሰቡ የአእምሮ ሁኔታ፣ የትምህርት ሁኔታ፣ የቤተሰብ ሁኔታ፣ የእድሜ ሁኔታ…ወዘተ ሊለያይ የሚችል መሆኑ እና ግለሰባዊ መሆኑ ነው:: በዚህ መነሻ ተመሳሳይ ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች አንዱ 5 አመት ሲቀጣ አንዱ ደግሞ 4 ዓመት ሊቀጣ ይችላል::

ይህንን የግለሰባዊነት መርህ ባለመገንዘብ አንዳንድ ጊዜ በአንድ ወንጀል በጋራ የተከሰሱ ሰዎች በወንጀል ይግባኝ ችሎት ክርክሮች ከእኔ ጋር ያለውን ሰው 5 ዓመት ቀጥቶ እኔን 6 ዓመት ቀጥቶኛል፤ የስር ፍርድ-ቤት ፍትሐዊ ውሳኔ አልሰጠም….ወዘተ የሚሉ ክርክሮችን ሲያቀርቡ ይሰማል:: ይህ ግን በሕግ መሠረት ተሠርቶበት ከሆነ የቅጣት ግለሰባዊነት መርህ ያመጣው ልዩነት እንጂ አድሎአዊነት አይደለም::

ሌላው የወንጀል ሕግ መሠረታዊ መርህ የወንጀል ሕግ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ ተመልሶ የማይሠራ መሆኑ ነው:: ለምሳሌ አሁን ባለው የወንጀል ሕጋችን አንቀፅ 648 መሠረት ማንም ሰው ከ18 ዓመት በታች የሆናትን ሴት ቢያገባ በወንጀል ይጠየቃል:: ነገር ግን ይህ ሕግ በሌለበት ጊዜ 14 ወይም 15 ዓመት የሆናትን ሴት አግብተው ትዳር መሥርተው የቆዩ ሰዎችን ወደ ኋላ ተመልሶ በወንጀል መጠየቅ የማይቻል መሆኑን ይህ መርህ የሚያፀና ሲሆን መርሁም ከህጋዊነት መርህ ጋር አብሮ የሚናበብ ነው::

የወንጀል ሕግ በእንዲህ ያሉ እና ሌሎች መሠረታዊ መርሆዎች የሚመሠረት ሲሆን እንደ ፀሐፊው ዕይታ የዚህ ሕግ አንድ ልዩ ጥቅሙ ሕጉ በአግባቡ ቢሰርፅ እና ቢተገበር የሀገር ባህልን በመጠበቅ እና በሰዎች መካከል መተሳሰብን በመፍጠር ሰዎች በሰላም እንዲኖሩ ከማድረግ ባለፈ የሰዎችን አስተሳሰብ ወደ ልዕልና የመውሰድ አቅም እንዳለው ነው:: የወንጀል ሕጉን አንቀፆች አንድ በአንድ ስንመረምራቸው የሕጉ ፍላጎት በሰዎች ላይ የአስተሳሰብ ልዕልና መፍጠር፣ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ መፍጠር፣ የሌላን ሰው መብት የሚጠብቅ ዜጋ መፍጠር…ወዘተ ሆኖ እናገኘዋለን::

ይግረማቸው ከፈለኝ ወግደረስ (LLB, LLM) ጠበቃ፣ የሕግ አማካሪ እና በወንጀል ፍትህ አስተዳደር አሠልጣኝ 0910037554/yigremachewk@gmail.com

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You