ሩሲያ በዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማት ላይ ከባድ የሚሳዬል ጥቃት ፈጸመች

ሩሲያ ከነሐሴ ወዲህ በፈጸመችው መጠነ ሰፊ የሚሳይል ጥቃት የዩክሬን የኃይል መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ማድረጓን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

ዩክሬን ችግር ውስጥ በገባው የኃይል መሠረተ ልማቷ ላይ የሚደርሰው ለሳምንታት የቆየው ጥቃት ለረጅም ጊዜ የኃይል መቋረጥ እና ወሳኝ በሆነ ሰዓት የሥነ ልቦና ጫና ያስከትላል የሚል ስጋት አድሮባታል።

“ሌላኛው በኃይል መሠረተ ልማት ላይ ያነጣጠረ ግዙፍ ጥቃት እየተካሄደ ነው። ጠላት በመላው ዩክሬን የኃይል ማመንጫዎችን እና የማስተላለፊያ መስመሮችን እያጠቃ ነው” ሲሉ የዩክሬን የኢነርጂ ሚኒስትር ጀርመን ጋሉሽቸንኮ ተናግረዋል።

ትናንትና ሌሊት የአየር ኃይሉ በኪዬቭ ከተማ ድሮኖችን ለማክሸፍ ሲተኩስ እና ከፍተኛ ፍንዳታ ሲሰማ ነበር ተብሏል። ሆኖም የደረሰው የጉዳት መጠን ምን ያህል እንደሆነ አልታወቀም።

ባለሥልጣናት ጉዳት ለመቀነስ በሚል በኪዬቭ እና በዙሪያዋ ያሉ ግዛቶች ጨምሮ በበርካታ ከተሞች ያሉ የኃይል አቅርቦቶችን አቋርጠዋል። የሰሜን ምሥራቅ ዩክሬን ቮልይን ግዛት ባለሥልጣናት እንደገለጹት በኃይል መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ደርሷል።

ባለሥልጣናቱ በጦርነቱ ምክንያት የኃይል መሠረተ ልማቱ ያለበትን ሁኔታ ግልጽ ማድረግ አይፈልጉም።

በደቡብ ማይኮላይቭ ግዛት ደግሞ ትናንትና ሌሊት በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። ሮይተርስ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው በደቡባዊቷ የዛፖሮዥያ ግዛት እና በጥቁር ባሕሯ የወደብ ከተማ ከፍተኛ ፍንዳታዎች ተከስተዋል።

“ሩሲያ ከባድ የተባለ የአየር ጥቃት ፈጽማለች። ድሮን እና ሚሳይሎች በሠላማዊ ከተሞች፣ በንፁሓን እና በኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት አድርሰዋል” ብለዋል የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሂያ።

ሚኒስትሩ ጥቃቱን ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ንግግር ላደረጉት ኦላፍ ሾልዝ መልስ ነው ሲሉ ገልጸውታል። የኔቶ አባል የሆነችው ፖላንድ ሩሲያ የምታስወነጭፋቸው ክሩዝ ሚሳይሎች ጥቃት እንዳያደርሱባት ለጥንቃቄ በአየር ክልሏ ውስጥ የጦር ጀት አሠማርታ እንደነበር ገልጻለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You