የአፍሪካ ቀንድ በጥቅሉም ምሥራቅ አፍሪካ ዘርፈ ብዙ የትኩረት ቀጣና ነው፡፡ ቀጣናው ከፍ ያለ ተፈጥሯዊ ሀብት ባለቤት ነው፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑ ሀገራት ቀጣናም ነው፡፡ በአንጻሩ ከባሕርነት ያለፈ ከፍ ያለ የፖለቲካ አጀንዳነትን የተሸከመው የቀይ ባሕር ጉዳይም ቀዳሚ አጀንዳቸው ያደረጉ ሀገራት ትኩረት ያሉበት አካባቢ ነው፡፡
በእነዚህ እና ሌሎችም ከፍ ያለ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ማንጸሪያነት የሚቃኘው ቀጣናው፤ ለዘመናት ከዕድገትና ሥልጣኔ ተቆራርጦ፤ ከሠላምና መረጋጋት ተራርቆ፤ ከመተባበርና መደጋገፍ እሳቤ ተፋትቶ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቢሆን ከዚህን መሰል ችግር የተላቀቀ አይደለም፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ቀድማ ነቅታ ቀጣናውን ለማንቃት እየተጋች የምትገኝ ሀገር የመሆኗን ያህል፤ የእሷን ሕልምና መንገድ የተረዱ ጥቂቶችም ሊያግዟት፣ ሊከተሏትና የጋራ ዕድገትና ብልፅግናቸውን ለማረጋገጥ የሚታትሩ አልጠፉም፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ሶማሌ ላንድ አንዷ ናት፡፡
የዚህ ዐቢይ ማሳያው ደግሞ፣ ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሠላምና መረጋጋት እውን ለማድረግ ከምታደርገው ጥረት በተጓዳኝ፤ ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር እያደረገች ባለው ጥረት አቅም የመደመር ጥረቷን እና ይሄን ጥረቷን ተረድቶ የማገዝ ጅምርን መመልከት ተችሏልና፡፡
ኢትዮጵያ ቀጣናውን በመሠረተ ልማት፣ በኃይልና በሌላም ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶች በማስተሳሰር፤ የቀጣናው ሀገራት እና ሕዝቦች ያሏቸውን አቅሞች አሰባስበውና ደምረው ማልማት እንዲችሉ፤ አልምተውም በጋራ መጠቀምም፣ በጋራ መበልፀግም እንዲችሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ስታከናውን ቆይታለች፡፡ የዓባይ ግድብ ደግሞ የዚህ አንዱና ቀዳሚው ሥራዋ ነው፡፡
ሌላኛው እና ከፍ ያለ ትርጉምም፣ ፋይዳም ያለው የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት እና ጥያቄ ነው፡፡ ይሄ የባሕር በር ፍላጎትና ጥያቄ ደግሞ ያለምክንያት የመጣ አይደለም፡፡ ይልቁንም በቀጣናው ያለውን ነገር ግን ጥቅም ላይ ሳይውል እየባከነ ያለውን እምቅ አቅም አውጥቶና አልምቶ በጋራ ከመጠቀም፤ እንደ ሀገርም ያለውን ከፍ ያለ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት፤ የቀይ ባሕር ጉዳይም የኢትዮጵያም ጉዳይ ከመሆኑ እና ሌሎች የበዙ ምክንያቶች ጋር ይያያዛል፡፡
ይሄ በብዙ አሳማኝ ምክንያቶች ታጅቦ የመጣ ፍላጎትም ይሁን የቀረበ ጥያቄ ታዲያ፤ ለሁሉም የጎረቤት ሀገራት የቀረበ “ሀብትና አቅማችንን ደምረን በማልማት በጋራ እንበልፅግ” የሚል ጥያቄ ቢሆንም፤ ይሄን ጥያቄ በልኩ ተገንዝቦ ቀና መልስ በመስጠት ረገድ እስካሁን ሶማሌ ላንድ ቀዳሚም ብቸኛም ሀገር ናት፡፡
ይሄ የሶማሌ ላንድ የኢትዮጵያን ጥያቄ በበጎ ተመልክቶ አዎንታዊ ምላሽ ከመስጠት ጀምሮ ጉዳዩን በስምምነት እስከመቋጨት የዘለቀው ርምጃ ታዲያ፤ ለኢትዮጵያ ከመራራት ወይም ደግ ለመሆን ሲባል ብቻ የሆነ አይደለም፡፡ ይልቁንም፣ ለሶማሌ ላንድ ሕዝቦች ዘርፈ ብዙ ጥቅም እና ለሶማሌ ላንድም ሁሉን አቀፍ ብልፅግና እጅጉን ወሳኝ አጀንዳ መሆኑን በመገንዘብ ነው፡፡
ይሄን አይነት መገንዘብ የሚመነጨው ደግሞ ከግል ጥቅምና ፍላጎት በፊት ለሀገርና ለሕዝብ ቅድሚያ ከመስጠት ይመነጫል፡፡ ከአምባገነናዊና አፋኝ እሳቤ ይልቅ ከዴሞክራት አዕምሮ ይመነጫል፡፡ ከእኔ ብቻ ብሂል ይልቅ፣ ከእኛ በእኛ ለእኛ በሚል የወል ተሳትፎና ተጠቃሚነት መርሕ ይቀዳል፡፡ የሶማሌ ላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ መስጠትም ከእነዚህ የእሳቤ ልዕልናዎች የመነጨ መሆኑ እሙን ነው፡፡
ይሄን አይነት እሳቤ ደግሞ አንድም እንደ ሀገር ለሚደረግ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ አቅም ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሶማሌ ላንድ እንደ ሀገር (ራስ ገዝ ሆና በዘለቀችባቸው ሦስት አስርት ዓመታት በላይ) ዜጎቿን ከዴሞክራሲ ጋር እያስተዋወቀች፤ ለበርካቶች ምሳሌ ስለመሆናቸው ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ጭምር እየመሰከሩላቸው ያለፉ በርካታ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎችን እያደረገች እና መሪዎቿንም፣ እንደራሴዎቿንም በዴሞክራሲያዊ መንገድ እየመረጠች መዝለቅ ችላለች፡፡
ዘንድሮም ከሰሞኑ መሰል ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ማካሄድ የቻለች ሲሆን፤ የራሷ ምክር ቤት እና መንግሥት፣ ገንዘብ፣ ማዕከላዊ ባንክ፣ ጦር ሠራዊት ላላት ሶማሌላንድ፤ ይሄን መሰሉ በየአምስት ዓመቱ የሚደረግ እና በአፍሪካ በምሳሌነት የሚጠቀስ ምርጫ ማከናወኗ ከፍ ያለ ሕልም እና ተስፋ ያላት ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡
ይሄ ከፍ ያለ ሀገራዊ ሕልም ደግሞ ብቻ ተቆሞ የሚሳካ አይደለም፡፡ እናም ይሄንን እሳቤ እና አቅም ደምራ ወደ ቀጣናው አቅም ሆና ብቅ ብላለች፡፡ የዚህ መውጣቷ አብነትም ከኢትዮጵያ ጋር የገባቸው የትብብርና አብሮነት ውል፤ የባሕር በር ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ በዴሞክራቶች መካከል የተፈጸመ ትብብር፤ ከሀገራቱ ባለፈ ለቀጣናው ሁሉን አቀፍ ሽግግር ያለው አበርክቶ ጉልህ ነው፡፡
እናም ዛሬ ላይ ሶማሌላንድ ይሄን መሰል ከየብቻ ሕልም ወደ ሁለትዮሽ ትልም፤ ከሁለትዮሽ ትልምም ወደ ባለብዙ እና ቀጣናዊ የጋራ አጀንዳና ግብ የሚሸጋገር ጉዳይን የሚገዛ ሕዝብ ባለቤት ሆናለች፡፡ ይሄ ደግሞ እንድትሆን ከምትፈልገው ባሻገር፤ ቀጣናው ላይ እንዲመጣ ለሚፈለገው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ተደማሪ አቅም ሆና እንድትወጣ የሚያደርጋት ነው!
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም