“ደረሰኝ ሳይቀበሉ ሂሳብዎን አይክፈሉ!”

አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ነገሮችን ደጋግመን በዓይናችን እናያቸውና ምንም እንዳልሆኑ አድርገን እንቆጥራቸዋለን። በየገባንበት የንግድ ማዕከል፣ በየመዝናኛ ስፍራው፣ በገበያ ቦታ፣ በየሆቴሉ፣ በየቁርጡ ቤት …ማሳሰቢያ ይሁኑ የግድግዳ ማስዋቢያ ጥያቄ እስኪፈጥሩብን ድረስ እንዘነጋቸዋለን። ምንም እንዳልሆኑ ምንም እንደማያስከትሉ አድርገን እንለምዳቸዋለን። “ደረሰኝ ሳይቀበሉ ሂሳብዎን አይክፈሉ!” የሚለው መልዕክት በእዚህ እሳቤ ውስጥ ከሚታዩት ትዕዛዝ አዘል ማሳሰቢያዎች መካከል አንዱ ነው።

ማንኛውም ማስታወቂያ በየትኛውም ቦታ ላይ ከተለጠፈ ወይም ከተሰቀለ መልዕክቱ መተግበር አለበት። በማስታወቂያው ግርጌ ላይ የሚቀመጡ የስልክ ቁጥሮችም የራሳቸው ዋጋ አላቸው። ‹‹ያጋጠመህን ችግር በስልክ ቁጥሮቹ ደውልና አሳውቀን። ቅሬታው በትክክልም ጥፋት ሆኖ ከተገኘ አጥፊውን ወይም ሕግ የጣሰውን በሕግ ተጠያቂ እናደርጋለን›› የሚል ውስጠ ምስጢር ያዘለ ይመስለኛል።

በተሰጠው ስልክ ቁጥር የደወለው አካል ባገኘው አገልግሎት ረክቶና ተደስቶ ለማመስገን ከሆነም ሙሉ መረጃውን ይዞ ለተገቢው አካል ተገቢውን ግብረ መልስ ለመስጠት እንጠቀምበታለን የሚል ይመስለኛል። ይህ የሚሆነው ትክክለኛ ያልነውን መንገድ የተከተልን እንደሆነ ነው። ‹‹አሁንስ?›› ካልን የአንዳንድ ማስታወቂያዎችና በግርጌያቸው የሚገኙ ስልክ ቁጥሮች ከጌጥነት ያለፈ ፋይዳ ያላቸው አይመስሉም። ምክንያቱም ስልክ ቁጥሮቹ የቢሮ ናቸው፤ የቢሮ ሥራና ሰዓት ደግሞ ይታወቃል። ስለዚህ ማንም ሠራተኛ ወይም ኃላፊ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል ብሎ የሚያስብ ሰው አይኖርም። ምክንያቱም የብዙ ነገር አገልግሎት ልውውጥ የሚኖረው ከሥራ ሰዓት ውጪ በበዓላት ቀንና በምሽት ጭምር በመሆኑ የቢሮ ስልክ የሚያነሳና ቅሬታውንም ሆነ ምስጋናውን የሚቀበል አለ?

“ደረሰኝ ሳይቀበሉ ሂሳብዎን አይክፈሉ!” የሚለውን መልዕክት የምናገኘው ከዋናው ከተማ እስከ ገጠር ድረስ ነው። በእያንዳንዱ ንግድ ቤት ውስጥ በጉልህ ተጽፎ ይነበባል። ኧረ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከአንድ በላይ ማስታወቂያ በየግድግዳው ሁሉ ተለጥፎ ይታያል። ሆኖም ግን ማስታወቂያው ከማስታወቂያነት ባለፈ ሂሳቡ ተከፍሎም ደረሰኙን ማግኘት እጅግ ከባድ የሚሆንበት ሁኔታ አለ። ይሄ አገልግሎት ባገኘውም አገልግሎት በሰጠውም አካል ክፍተት ወይም ድክመት የሚመነጭ ነው።

አንዳንድ ሰው ላገኘው አገልግሎት ክፍያ ለመፈጸም “ሂሳብ አምጡልኝ ” ብሎ ሲጠይቅ አስተናጋጁ ደረሰኙን ይዞ ብቅ ከማለት ይልቅ እጁን ወደ ኋላ አድርጎ የሂሳቡን መጠን ይናገራል። “ደረሰኝ አምጣ እንጂ” የሚል ጎበዝ የገጠመው እንደሆነ ፈጠን ብሎ፣ ‹‹መብራት ጠፍቶ ነው›› ወይም ‹‹ደረሰኝ አትጠይቁን›› የሚሉ ገፍታሪ መልሶችን ይደረድራል። ኧረ “መብራት ሲመጣ ኑ” የሚሉም አልጠፉም። “ዛሬ እንኳን እንሥራበት! ላሽ በል” የሚልም አራዳ መሳይ አጭበርባሪ ያጋጥማል። የተገልጋዩን ሂሳብ ከኪሱ አስወጥቶ የመንግሥትን ድርሻ ወደ ካዝናው የሚያደርግ ሰው አራዳ መሆኑ ነው? አንዳንዱ ደግሞ ለማያውቀው (ድንገት ለተከሰተ ደንበኛ) ብቻ ነው ደረሰኝ የሚቆርጠው። ሌሎች ‹‹ቤተሰብ›› ናቸው። በዚህ ሰበብ የመንግሥት ገቢ የግለሰቦችን ኪስ ያሞቃል። እዚህ ላይ ወንጀለኛው ሁለቱም አካል መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።

ዛሬ ላይ ደረሰኝ ስጡኝ አትስጡኝ ለሚለው ንትርክ የዳረገን ለታክስና ግብር ያለው የተዛባ አመለካከት ነው። “ያለደረሰኝ አትሽጡ፣ ትክክለኛ ገቢያችሁን አሳውቁ፣ ኮንትሮባንድ ንግድ አቁሙ፤ ወደ ቫት ሥርዓት ግቡ፣ ንግድ ፈቃድ የሌላችሁ ንግድ ፍቃድ አውጡ፣ ደረሰኝ መቁረጥ ደረጃ የደረሱ ነጋዴዎች ደረሰኝ አስፈቅደው ያሳትሙ፣ በአጠቃላይ የንግድና የግብይት ሥርዓቱ ሕጋዊ መስመር የተከተለ ይሁን” የሚል ጠበቅ ያለ እንቅስቃሴ በመንግሥት በኩል በመጀመሩ ነው። ይሁን እንጂ ሕገወጥነት እንዲጠፋ የማይፈልጉ አካላት ኅብረተሰቡን የሚያውኩና ለአመፅ የሚቀሰቅሱ ወሬዎችን አስቀድመው ይነዛሉ። ወከባ ይፈጥራሉ፤ ግርግር ያስነሳሉ።

ሰሞኑን በመርካቶ አካባቢ ያየነው ግርምትን ያጫረብን ጉዳይ ነው። በእርግጥ ሁሉንም የንግዱ ማኅበረሰብ አጭበርባሪ፣ አወናባጅ፣ ሕገወጥ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። በጣም ምስጉን የሆኑ፣ ሕግና ሥርዓት ተከትለው የሚሠሩ በሥነምግባር የሚታወቁ ብዙ ስመጥሩ ነጋዴዎች አሉ። አንቱ የተባሉና ከዘመን ዘመን ከነስምና ክብራቸው የዘለቁ አሉ። በሐቀኛ ግብር ከፋይነት የተመሰከረላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ እውቅና እስከማግኘት የደረሱ ‹‹የቄሳርን ለቄሳር የእግዜሩን ለእግዜር›› ብለው በሐቅ የሚሠሩ ብዙ የንግድ ማኅበረሰቦች አሉ። እነዚህን ጨምሮ የንግዱ ማኅበረሰብ ብሎ በጅምላ መውቀስ አይቻልም። እነዚህን ሐቀኛ የሕዝብ አገልጋዮችን ሽፋን አድርጎ የሚሠሩትን ግን መቼም ቢሆን መውቀስና ማውገዝ ይገባል።

‹‹ሕጋዊ ሥርዓት ይዘርጋ፣ ሰው የልፋቱን፣ የላቡን ያግኝ›› ሲባል “ሱቅ ሊዘጉ ነው፤ ንብረት ሊወርሱ ነው” የሚል ሽብር መንዛት ተገቢነት የለውም። ሱቅን መዝጋትና መሸሽም መፍትሔ አያመጣም። ሐቀኛ ነጋዴ ማንም ይምጣ ምንም ይምጣ ለሚጠየቀው ሁሉ የሚሰጠው መልስ በልበ ሙሉነት በተሟላ መረጃና ማስረጃ መሆን ይኖርበታል። ለዚህም በሩን ክፍት ማድረግ ነው የሚጠበቅበት። ከተቆጣጣሪ አካል ጋር ድርድር፣ ንብረት ማሸሽ የመሳሰሉት ውስጥ መግባት የትም አያደርስም። ምክንያቱም በየትኛውም ዓለም ለሀገር ዕድገት አንዱ የገቢ ምንጭ ታክስ፣ ግብር፣ ቫት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ምንም ማጭበርበር የሌለበት ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር የሚቻለው የመንግሥት ሠራተኛው የሚከፍለውን ታክስ ነው። የመንግሥት ሠራተኛው የሚጠበቅበትን ታክስ ገቢ የሚያደርገው ከዋናው ደመወዙ ፔሮል ላይ ተቆርጦ ነው፤ ስለዚህ በማንም ሰው እጅ ላይ የሚገባ ገንዘብ ባለመኖሩ ሳይቆረጥ የሚቀር ወይም የሚጭበረበር ታክስ አይኖርም። ለዚህም ነው የመንግሥት ሠራተኛው ሳያጭበረብር ታክስ ይከፍላል የምንለው።

በከተማዋ በርካታ ነጋዴዎች በግብር ከፋይነት ተመዝግበው ደረሰኝ የማይሰጡ በመሆናቸው እና ችግሩም በጣም እየሰፋ በመሆኑ ወጥነት ባለው መንገድ ሕጉን እንዲያከብሩ እና ወደሥርዓት እንዲገቡ የማድረግ እንቅስቃሴ በከተማ አስተዳደሩ ተጀምሯል። ይህ ይበል የሚያሰኝ ጅምር ነው። በነገራችን ላይ አንድን ጉዳይ ሕግና ሥርዓት ለማስያዝ ሲሠራ፣ የችግሩ አስኳል የሚገኘው በሌላ ቦታ ሌላ አካል ላይ ሊሆን እንደሚችል መገመትና ሰንኮፉን ለይቶ ለማውጣት መሥራት ይገባል። አስመጪዎችና ጅምላ አከፋፋዮች አካባቢ ያለውንም በነካ እጃችሁ ማለት ያስፈልጋል ። በቸርቻሪነት ሥራ ላይ ያሉትንም አለብን የሚሉትን ችግር በደንብ ማድመጥና መፍትሔ መስጠት ይገባል። ይሄ ሲሆን ነው ፍትሐዊ ውድድር የሚሰፍነው፤ ሕግና ሥርዓት የሚከበረው፤ ደረሰኝ ስጠኝ ከሚለው ሙግትም የሚወጣው።

ሕግና ሥርዓት በከተማችን ብሎም በሀገራችን ሲሰፍን ‹‹ደረሰኝ ሳይቀበሉ ሂሳብዎን አይክፈሉ›› የሚለው ማሳሰቢያ መሳይ ማስታወቂያ ከጌጥነት ያለፈ ሚና ይኖረዋል።

(አዶኒስ (ከሲኤምሲ)

አዲስ ዘመን ኅዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You