ይቤ ከደጃች. ውቤ
ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት ይባላል። ዞረን ዞረን የምንመለስበትን ቤት መቼም እንደነገሩ አናረገውም። ማረፊያችን ፣ገበናችን ነውና ብዙ አውጥተን እናሰማምረዋለን። አዎን እረፍት ጥሩ ስፍራን ይሻልና የምናርፍበት ቦታ ጥሩ መሆን አለበት። ጥሩ ማድረግ ይኖርብናል ።
እንደዚያም ሁሉ ሌላ የማንቀርበት ስፍራ አለ። ይህ ስፍራ የቀብር ስፍራ ነው፤ …ኖሮ ኖሮ ከመሬት .. የሚባለው። ሰውዬ! ምን ነካህ ስለምን ቀብር ነው በአገር አማን የምታወራው ትሉኝ ይሆናል። ጎበዝ የቀብር ስፍራ ባናስበውም እንድናስበው ያረገናል።
ይህ ጉዳይ ግን አባቶችንና እናቶችን በእጅጉ ሲያሳስባቸው ኖሯል። መቃብር ቤት አስቀድመው ያዘጋጃሉ። አሁን በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች እንደሚስተዋለው ከቀብር ቦታ ጥበት የተነሳ ራቅ ባለ ስፍራ ላለመቀበር በሚል በአካባቢው በሚገኝ የእምነት ተቋም አቅራቢያ አስቀድሞ የቀብር ቦታ ማዘጋጀት ተለምዷል። ሰዎች ተሰባስበው በርካታ ኪስ ቀብር ያሉት ህንጻ መስራት ውስጥም ገብተዋል።
አንዳንዶች ደግሞ የቀብር ስፍራ ማዘጋጀትን የንግድ ስራ አርገውታል። አንድ ኪስ ዛሬ 40 እና 50 ሺ ብር እየተሸጠ ነው ይባላል። ይህ ላለው ነው፤ አፈሯን ለሚፈልጉት ግን ነገሮች አስቸጋሪ እየሆኑ ይገኛሉ።
መቼም ቀብር ወጥቼ አላውቅም እንዳትሉኝ ። ከሰው ተፈጥሮ ከቀብር ስፍራ አይቀርም። ስፍራው ለህጻናት ብቻ ነው የማይሆነው። እዚህ ላይ ህጻን ነኝ ትሉ ይሆናል። አይቻልም። እድር ውስጥ ባትኖሩም ጎረቤት፣ ዘመድ፣ ጓደኛ ሞት ወይም የቅርብ ሰው ሞቶባችሁ ሳትሄዱ አትቀሩም። ስለቀብር ስፍራ ምንም አላውቅም አትሉኝም።
እኔ ግን ጉዳዬ ወዲህ ነው ። በተለያዩ የቀብር ስፍራዎች ተገኝቼ አውቃለሁ። ስለቀብር ስፍራዎች እና የቀብር ስርአት ብዙ ማለት ቢቻልም፣ እኔን አሁን በእጅጉ ያሳሰበኝ የቀብር ስፍራዎች ጽዳት ጉድለት ነው። ትንሽም ቢሆን በመንግሰት የሚተዳደሩ የቀብር ስፍራዎች በጥሩ ሁኔታ የተያዙ ይመስለኛል። ሀውልት ብሎ ነገር ቀርቷል፤ ምልክት ነው የሚኖረው፤ በተረፈ አካባቢውን አረንጓዴ ለማድረግም እየተሞከረ ነው ፤ መግቢያ መውጫውም እንዲሁ ተለይቷል። ሌሎች ተመሳሳይ የቀብር ስፍራዎችም አሉ። ከጎናችን የተለየንን ሰው በእነዚህ አይነቶቹ ክቡር ስፍራዎች አሳርፈን ፣እኛም በእነዚህ የተከበሩ ስፍራዎች ቆይታ አርገን ብንመለስ መልካም ነበር።
በሌሎች የቀብር ስፍራዎች የሚታየው ግን ከዚህ በእጅጉ ይለያል። ወደ እነዚህ አይነቶቹ የቀብር ስፍራዎች አማራጭ ስለሌና ከቦታው ስለማይቀር እንጂ ተደግሞ የሚኬድባቸውም አይደሉም። እዚህ እዚህ ቦታ አልላችሁም። እነዚህ የቀብር ስፍራዎች በቅርበትም በርቀትም ሲታዩ በጣም ያሳፍራሉ። ሁሉም ማለት ይቻላል ዳዋ ለብሰዋል። በጨጎጎት እና እሾህ ተሞልተዋል፣ ሳሩ ቅጠሉ ቅጥ የለውም። አንዳንዶቹ የቀብር ስፍራዎች የለየላቸው ጫካ ናቸው። ጅብ በብዛት እንደሚገኝባቸውም ይነገራል።
ከፍተኛ የጽዳት ጉድለት ይታያል ። የመጸዳጃ ስፍራ ተደርገዋል። የቀብር ስፍራ መጥፎ ጠረን ሊኖረው ቢችልም የእነዚህ አካባቢዎች መጥፎ ሽታ መጸዳጃ ከመደረጋቸው ጋር በቅጡ ይያያዛል። መተላለፊያ የለም፤ በፈራረሱ ሀውልቶች፣ በመቃብር ላይ እየተረማመዱ ነው ወደ ትኩሱ የቀብር ስፍራ የሚደረሰው።
በመሰረቱ የቀብር ስፍራዎች በተለይ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ አስከሬን ማረፊያ ከመሆን አልፈው፣ በሕይወት ያሉ ሰዎችም በጽሞና አረፍ የሚሉባቸው በአረንጓዴ ልምላሜ የተዋቡ መሆን ነበረባቸው። በዚህ ዘመን ዘላቂ ማረፊያ ነው የተባሉት መሰለኝ። ጥሩ ስያሜ ነው የወጣለቸው።
ወዳጆቼ አብዛኞቹ የቀብር ስፍራዎቻችን ማረፊያ ከመሆን ይልቅ ማፈሪያ እየሆኑብን ነው። ዮሴፍ ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚገኘው የባሃኢ አማኞች መካነመቃብር እና የዊንጌት የካቶሊክ ቅዱስ ጴጥሮስ መካነ መቃብር ስፍራዎችን ከውጪ ሆኜ እንዳየሁዋቸው ከሆነ የተሻሉ ናቸው። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት መንግስት የሚያስተዳድራቸው የቀጨኔ፣ የመካኒሳ ፣ የዮሴፍ የቀብር ስፍራዎችም በእርግጥም የሙታን ማረፊያ ናቸው።
የተቀሩት በእምነት ተቋማት የሚተዳደሩት የቀብር ስፍራዎች ግን በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ናቸው። በቅድሚያ እነዚህ የቀብር ስፍራዎች እየተመናመኑ ይገኛሉ። አጽም እየወጣ ህንጻ እየተገነባባቸው ለሌላ አገልግሎት እንዲውሉ እየተደረገ ነው። አንዳንዶቹም እንደ ጋራዥ ላሉት አገልግሎቶች ተከራይተዋል። ጥቂት የማይባሉ ቦታዎችም ቢሆኑ በማህበር የተሰባሰቡ ሰዎች ኪስ የቀብር ስፍራዎችንና ሌሎች ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ህንጻዎች እየገነቡባቸው ነው።
የተቀሩት ስፍራዎች ለአፈር የቀብር ስፍራ የተተው ቢሆንም፣ ሰው ለአፍታም የሚቆይባቸው አይነት አይደሉም። እንደ እውነቱ ከሆነ ተቋም የሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች አይመስሉም። ዳዋ ለብሰዋል። መጸዳጃ ተደርገዋል። የቀብር ስፍራዎቹን የሚያስተዳድሩ የእምነት ተቋማት ይህን እየተመለከቱ ለምን ዝም እንደሚሉ አይገባኝም። ለቀብር ስፍራ ክፍያ እንደሚፈጸም ይታወቃል። ከዚህ ክፍያ ውስጥ ለቆፋሪዎችና ለመሳሰሉት ክፍያ ሊፈጸም ይችላል። አካባቢውን ለማጽዳትስ ለምን አይተኮርበትም። እንደሚገባኝ ብዙ ብር ይሰበሰባል። ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ለጽዳት ስራ መመደብ ያስፈልጋል። የገንዘብ እጥረት ካለ በዚህ ላይ ተወያይቶ የሚቀረፍበትን ሁኔታ ማበጀት ያስፈልጋል።
ከአንዳንዶቹ የቀብር ስፍራዎች የሚወጣው መጥፎ ጠረን የእምነት ተቋማቱ ቅጥር ገቢ ድረስ የሚደርስበት ሁኔታ ይስተዋላል። አካባቢውን ማጽዳት የእምነት ተቋማቱን ማጽዳትም ጭምር መሆኑ ለምን ተዘነጋ? መጸዳጃ ቤቶችን በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀትና እያስከፈሉ አገልግሎት መስጠትም ይቻላል።
ዳዋውን በየጊዜው መመንጠር ያስፈልጋል። አካባቢው በሚገባ ተስተካክሎ ለቀባሪ መረማመጃ ምቹ ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል። አጥር ግቢ የሌላቸው የቀብር ስፍራዎች ካሉም በአጥር በመከለል መጸዳጃ ሊሆኑ የሚችሉበትን እድል ለማጥበብ ይረዳል። የቀብር ስፍራውም መልክ መልክ መያዝ ይኖርበታል።
በቀብር ስፍራ ላይ ከህጻናት በስተቀር የማይመጣ የማህበረሰብ ክፍል የለም። ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ወዘተ. ሊመጡ ይችላሉ ተብሎ መታሰብ ነበረበት። እነዚህ ሰዎች ይህን ጉድ ሲመለከቱ ምን ሊሉ እንደሚችሉ መገመት ያስፈልጋል።
የእምነት ተቋማት በተለይ የአዲስ አበባዎቹ ይህን ስፍራ ማጽዳት አይደለም ሌላም መስራት የሚያስችል እቅም እንዳላቸው ይታወቃል። ማጽዳት ሲገባቸው ታቅፈው መቀመጣቸውና እዩልኝ ማለታቸው ትዝብት ውስጥ እንደሚጥላቸው ተረድተው ከዚህ በሁላ ለስፍራዎቹ ጽዳትና ንጽህና ትኩረት መስጠት አለባቸው።
ከመንግስትና ከአንዳንድ የእምነት ተቀማት የቀብር ስፍራዎች ጽዳትና ስርአት አያያዝ ተሞክሮ መውሰድ ይገባል። በጽዳት ጉድለትና ውብ አለመሆን ሳቢያ ቀባሪዎች ያንን ስፍራ እንዳይጠሉት ማድረግ ይገባል። ስፍራው በተቀባሪም ሆነ በቀባሪነት የማይቀርበት ነውና በሚገባ አልምቶ ጥሩ የማረፊያ ስፍራ ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም