ሁለቱ የሞት ሰርጓጆች

በአንድ ሳምንት፣ በአንድ ቀን ልዩነት፣ በአንድ ዓይነት ሁኔታ፣ ሁለት የሕይወት ጀልባዎች ከአንድ የሞት ባሕር ሰርጉደዋል። በሁለት ተከታታይ ቀናት ሁለት የሀገራችን ዝነኞች በድንገት ሰጥመው ቀሩ። ቅዳሜና እሁድ፣ ሁለቱ የእረፍት ቀናት ሁለቱን በሞት ወለል ላይ አሳረፉ። ልብ ሰበር ዜናዎች አንድ አንድ እያሉ በየቀናቱ ማለዳ ደርሰው የመርዶ ነጋሪታቸውን ጎስመዋል።

የመጀመሪያው ሰርጓጅ፣ የሁለተኛው ቀን የሞት ተጓዥ ኩራባቸው ደነቅ (ኩራ) ያሉት ኩሩ ነበር። ሁለተኛው ቢሆንም እንደ ወግ ባሕላችን እናስቀድመው። ጠዋት ላይ እኮ ደህና ነበር። ከእንቅልፉ በሰላም ነቅቶ የእሁድ ማለዳን ብርሃን ጮራ ተመልክቶ ነበር። በዛሬ ተስፋ ቆሞ ነገን እየተመለከተ ለአፍታ ፈገግ ብሎ ነበር እኮ…ግን ቅጽበቶች በቅጽበት ተሻሩ። የቆመባት የሕይወት ጀልባ ድንገት በማዕበሉ ተናወጠች። ሞት ፈጥኖ ታንኳዋን ጨበጠው። ከባሕሩ መሐል ቁልቁል ወደማትመለስበት ስምጥ አሰረጎዳት። ከዚያ ቅጽበት አስቀድሞ ኩራባቸው ከእንቅልፉ እንደተነሳ ቁርሱን መብላት ይፈልግ ነበር። በሕይወት ጉዞ ውስጥ መኖርን ተስፋ ስላደረገ ስንቁን በሆዱ መቋጠርን ፈለገ። ከአልጋው ብድግ እንዳለ ከዚያው ከቤቱ ምግቡን አዞ ተመለሰ። ሞት ግን ቁርሱን ቀድሞት ደረሰ። ከፊት ለፊት ቆሞ ሾተላዩን ጨብጦ ለመሰቅሰቅ የተዘጋጀው ሞት ሰውን ያያል እንጂ፤ ሰው ግን ፊቱ የቆመውን ሞት አይመለከትም። ከሚሰረጉደው ጀልባ ላይ ያለውን ኩራባቸው ደነቀን ድንገት ሞት አንገቱን አንቆ እስትንፋሱን እንደ ውሀው ፉት አደረጋት። ለሕመም እንኳን ፋታ ያላገኘው ኩራባቸው በዚያው አሸለበ።

ኩራባቸው ደነቀ፣ ምስኪኑ የሞት ባሕር ሰርጓጅ ዛሬ እንደምናወራለት ከሞት በፊት ምንም አላልንለትም ነበር። ከሞት ኋላ እንደሆነው ዓይነት ዝነኛም አልነበረም። ለመሆን የማይችል፣ ለዚህም የሚያበቃ ሥራ ስላልሠራ ግን አልነበረም። ምናልባት ሳይመስለን ቀርቶ ወይንም ጊዜ ታጥቶ ይሆናል። ምናልባትም ደግሞ በኪነ ጥበባዊ ተጋድሎው ከፊት አርበኝነቱ ይልቅ የኋላ ደጀንነቱና የውስጥ አርበኝነቱ ስለሚጎላ ይሆናል። በአደባባይ ከሠራው ይልቅ በጓዳው፣ እላይ ከሠራውም እታች ያደረገው ይበልጣል። እሱ ማለት እናቱን አብዝቶ እንደሚወድና ለአፍታም ቢሆን ሊለያት እንደማይችል ሕጻን ልጅ ነበር። ከልጅነቱ ጀምሮ የጥበብ ቀሚሷን ጫፍ እንደያዘ በሄደችበትና በዞረችበት ሁሉ ኩስ! ኩስ! እያለ እስከ ዕለተሞቱ ድረስ ሲከተላት ኖሯል።

የሐረር ከተማ ኩራባቸውን ያህሉን ትልቅ ሰው ወልዳለች። ከጀጎል ግንብ ፊት ፎለል ብላ ከተቀመጠችው የሽንኮር መንደር ውስጥ በ1957 ዓ.ም ተወልዶ ከአስታራቂው መንገድ ላይ፤ ከአቻዎቹ ጋር ውስጥ ውስጡን በአኩኩሉና በአባሮሽ ሲሯሯጥ ደርሶ ከትምህርት ቤቱ ገባ። ነገር ግን በፍጥነት የሚመታው ልቡ እንኳን ሳይረጋ ከቤተሰቡ ጋር አብሮ ወደ አሰበ ተፈሪ አቀና። የአስኳላን ሀሁም ሆነ የሕይወት ኤቢሲዲውን የተማረውም ከዚህ ነበር። ጥለቱ በኅብራዊ የቀስተደመና ቀለማት ያጌጠውን የጥበብ ቀሚስ መያዝ የጀመረውም ከዚሁ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ነበር። በነጋ በጠባ ቁጥር ከትምህርት ቤቱ የሚኒ ሚዲያ ክፍል ውስጥ ኩራባቸውን ማግኘት የተለመደ ነገር ነበር። ቢያቀርብም ባያቀርብም ሁሌም ከዚያ ቦታ አይጠፋም። እዚያ ቦታ ላይ ብቻ ሳይሆን አንዳች ጥበብ ጥበብ የሚሸት ነገር ካለበት ሁሉ ድንኳን ሰባሪ ነው። ያለው ጉጉትና ፍላጎት ከእርሱ አልፎ የሚመለከተውንም የሚቀሰቅስ ዓይነት ነበር።

በ1970 ዓ.ም አካባቢ የቀበሌው የኪነት ቡድን ሲቋቋም በዚያው በሰማበት ቅጽበት ሲገሰግስ ደርሶ የመጀመሪያው ተመዝጋቢ አባል ለመሆን የቀደመው አልነበረም። ጥበብን እንጂ ጥሪውን ለይቶ ባለማወቁም እንዲሁ በደመነብስ ወደ ውዝዋዜና ድምፃዊነቱ ተቀላቀለ። ብዙ ሳምንት፣ ወራት አልፈው ግን ከልቡ ውስጥ የሚያቃጭለው የጥበብ ጥሪ የትወና ድምፅ መሆኑን ተረዳ። ወደዚያ ሲያማትር ግን በትወናው ውስጥ ያሉት ከፍ ከፍ ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና መምህራን ብቻ ነበሩ። እንዴት ብሎ በየት ሾልኮ ሊገባ እንደሚችል ሲያስብና ሲያውጠነጥን ቢቆይም ከውስጥ ለሚንፈራገጠው ልቡ ግን ምላሹን ሊያገኝ አልቻለም። ተስፋ እንደሌለው አምኖ ላለማሰብ ቢሞክርም ሁል ጊዜም ቢሆን ግን የቲያትርና ድራማ ልምምድ ከሚያደርጉበት አዳራሽ ቀርቶ ግን አያውቅም። ከአንዱ ጥግ ቁጭ እንዳለ ሲለማመዱ በልጅነት ጉጉቱ ተመልክቶ ይመለሳል።

ከአንደኛ ደረጃ እያለ ሁለተኛ አልፎም በ1975 ዓ.ም ወደ ትልቁ የአስኳላ ቤት፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ ገባ። እዚያ እስኪደርስ ድረስ የጥበብን ቀሚስ እንደያዘ ቢሆንም ደርሶ በዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ ምን እንደሚማር ግን አላወቀም አልወሰነም ነበር። የተቀበሉት የሀገሩ ልጆች ግን ድሮውኑ ከተሰጠበት የቲያትር ጥበባት ውጭ ማየት እንደሌለበት አስረግጠው ነገሩት። ነቅቶ ትዝ ያለው ገና የዚያኔ ነበር። የዩኒቨርሲቲው የባሕልና ኪነት ቡድን አባልም ሆኖ በትወናው ብዙ ሠርቷል። ትምህርቱን አጠናቆ ከወጣ በኋላም በ1980 ዓ.ም በባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር በዘመቻ መምሪያ ተመድቦ ወደ ጋሞ ጎፋ ክፍለ ሀገር ሄደ። በአርባ ምንጭ ቅርንጫፍም ጀማሪ የቲያትር ኤክስፐርት ሆኖ ተቀጠረ። ነብስያው የቲያትሩን መድረክ እየተጠማች በዚያ ሁለት ዓመት ሲቆይ፤ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ ከተማው ባሉ ክበባት ውስጥ ስለቲያትር እያሠለጠነ ያፈራው ትውልድ አይረሳም። አንድ የጥበብ ፍንጭ የተመለከታቸውን ወጣቶች እያነፈነፈ ቀርቦ ተሰጥዖዋቸውን ያወጣዋል። የቲያትር ጠረን እየናፈቀው በአንድ ዓመት ውስጥ ሰበብ እየፈለገ አሥር ጊዜ ወደ አዲስ አበባ መመላለሱም ይነገራል። የመመረቂያ ጽሑፉን በሕጻናት ቲያትር ዙሪያ ጽፎ የነበረው ኩራባቸውም በስተመጨረሻ አዲስ ወደ ተከፈተው የሕጻናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት ጎራ በማለት በ1982 ዓ.ም ተቀጥሮ አዲስ አበባ የመግባቱን ዕድል አገኘ።

በሕጻናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት ውስጥ በመደበኛነት እየሠራ በጎን ግን ከትልልቅ የቲያትር ባለሙያዎች ጋር ግንኙነትና ጥምረት እየፈጠረ የቲያትር ጥሙን ያረካ ጀመረ። ኋላም ሳይቆይ ከእነ ኃይሉ ፀጋዬ፣ ስንዱ አበበና ሌሎችም ጋር በመሆን “ቅርጫው” የተሰኘውን ቲያትር በጋራ ሠርተው በራስ ቲያትር አቅርበዋል። በዚህ ጥምረት የተማረከው ተፈሪ ዓለሙም ሥራዎችን ያመጣላቸው ነበር። በሕጻናትና ወጣቶች ሁለት ዓመታትን ከሰነበተ በኋላ ኩራባቸው አንጋፋውን ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ተገናኘ። በሀገር ፍቅር ውስጥ ከመድረክ ተዋናይነት አንስቶ እስከ መሪነት ወንበር ድረስ ተቀምጦበታል። ቢሆንም ግን ልቡ ለጥበብ በቃኝ አይልምና ከአንድ ሀገር ፍቅር ውስጥ ሆኖ የማይደርስባቸው ቲያትር ቤቶች አልነበሩም። በሬዲዮና ቴሌቪዥን ድራማዎች ውስጥ ሳይቀር የትወና ብቃቱን ሲያስመሰክር ነበር። ከዚህ ባሻገርም ራሱ እያዘጋጀና ዳይሬክት እያደረገ አይረሴ ሥራዎቹን ከማይረሱ መድረኮች ፊት አቅርቧል።

ስለኩራባቸው ታላቅነት ከሚያነሱ ሰዎች አንደኛው ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ አንዱ ነው። ከወራት በፊት “የሚሳም ተራራ” የተሰኘውን መጽሐፍ ሲያስመርቅ መድረኩ ላይ ቆሞ እንዲህ ሲል ሰማሁት “….የዚያን ጊዜ ኩራባቸው ያን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍሎ እኔን አፈላልጎ ባያገኘኝና በዚያች ብጣሽ ወረቀት በሰፈረች ጽሑፌ እንደምችል ነግሮ ብርታት ባይሆነኝ ኖሮ ምናልባትም ደራሲ ባልሆንኩ ነበር” አለ። ይህ የሆነው ኩራባቸው ጋሞ ጎፋ በነበረበት ሰዓት ነበር። ፍቅረ ማርቆስ ለአንድ ውድድር የሚሆነውን ጽሑፍ ልኮ እርሱ ግን አንዴም ብቅ ሳይል በዚያው የውሀ ሽታ ሆኖ ቀረ። ጽሑፉን አንብቦ በጣም የተደሰተው ኩራባቸውም በእግር በፈረስ አፈላልጎ በመጨረሻ ፍቅረ ማርቆስን አገኘው።

የ59 ዓመታት የወርቃማ ዕድሜ ባለቤቱና ከያኒው ኩራባቸው ደነቀ ለቲያትር ጥበብ እንደኳተነ ነሐሴ 19 ቀን 2016 ዓ.ም አረፈ። ነሐሴ 21 ቀን በቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ከአፀዱ አፈር ለበሰ።

“አባዬ” አለ ልጅ። “አባቴ” ሲል አባት የልጁን ቀጣይ ንግግር ተጠባበቀ። “ባለፈው እኔ የሠራሁበት ፊልም ዛሬ ይመረቃልና አብረኸኝ ብትሄድ ደስ ይለኛል” በማለት ዓይኖቹን እያቁለጨለጨ በዓይኖቹ ተማጸነው። አባትም በዕለቱ ሌላ ለእንጀራቸው የሚውሉበት ሥራ ቢኖራቸውም ከልጄ ደስታ አይበልጥም በማለት ወደ ፊልም ምረቃው ለመሄድ ተስማሙ። ከሰዓታት በኋላም አባትና ልጅ በአዳራሹ ውስጥ ጎን ለጎን ተቀምጠው መመልከት ጀመሩ። አባት በልጃቸው ኩራት እየተሰማቸው ደርበብ ብለው ከወንበሩ ላይ እንደተቀመጡ ከአሁን አሁን ልጄን ልመለከተው ነው እያሉ በጉጉት ብዙ ቅጽበቶችን እንደተጠባበቁ ፊልሙ ተጀምሮ አለቀ። ግራ የተጋቡት አባት ወደ ልጅ ዞር ብለው “ቆይ በፊልሙ ውስጥ ሠርቻለሁ አላልከኝም ታዲያ የት አለ?” ሲሉ በንዴት ታፍኖ በደከመ ድምፅ ጠየቁት። “እንዴ አባዬ ቅድም ወንበሩ ላይ ቆሜ ሁለቴ ያሳልኩት እኮ እኔ ነበርኩኝ” በማለት መለሰ። ከዚህ በኋላ አባት ምንም አልተናገሩትም። በልባቸው የሥራህን ይስጥህ እንዳሉት አንዳችም ሳይተነፍሱ እቤት ደረሱ። ይህ የጌታቸው እጅጉ (ባቡጂ) መጀመሪያ ነበር። ከዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ተነስቶ 60 ያህል ፊልሞችን ለመሥራት በቃ። ቢሆንም ሕይወቱ ግን እንኳንስ ስድሳ ቀርቶ ሁለት ፊልም የሠራ ያህል አነበረም።

ጌታቸው ፊልም ሠርቶ አይደለም እንዲሁ ገና ሲመለከቱት በሰው ስሜት ውስጥ ሳቅና ፈገግታን የመፍጠር አቅም አለው። ስድሳ ፊልሞችን ቢሠራም ካለው አቅም አንጻር ግን ለፊልሙም ሆነ ለኑሮው አልተጠቀመበትም። ቁጥሩ ዝነኛ ቢያደርገውም ከዝናው ለመጠቀም ያልቻለ ምስኪን ነው። ለተጠራበት ጥበብ እንጂ እንደ አብዛኛዎቹ ዝነኞች ለራሱ አላወቀበትም። ከበርካታ የፊልም ቁጥሮቹ መካከል ቤንጃሚን፣ ያረፈደ ፍቅር፣ ጉራ ብቻ፣ የእናቴ ሠርግ፣ እሱና እሷ፣ መጣ በፈረስ፣ ወደልጅነት እና በቅርቡ ደግሞ እንዳትረሳው በሚሉት ፊልሞች ውስጥ እንደ ኦሪዮን ኮከብ ነበር። ከሠራቸው ፊልሞች ሁሉ አብልጦ የሚወደው ደግሞ “መባ” የተሰኘውን ፊልም ነው። ለምን በልዩነት ወደድከው ሲባል “እንዳለ በምሠራቸው ሥራዎች ውስጥ የሚሰጡኝ ገፀ ባህሪያት የሚያስቁና የኮሜዲ ዘውግ ያላቸው ናቸው። መባ ላይ ግን ወጣ ያለና ከቀልድ የራቀ ገፀ ባሕሪን ነበር የተጫወትኩት” በማለት ምክንያቱን ያስረዳል።

የሞት ሰርጓጁ ባቡጂ በውዝግብ አሰርጓጅ ማንነት የነበረው ወጣት ነበር። በተገኘበት ሁሉ በሳቅ ጥርስ የማያስከድን ብቻም ሳይሆን በአስገራሚነቱ በልብ ዥዋዥዌ የሚያጫወት ዓይነት ነው። ለዚህም ነበር ከህልፈቱ ቀደም ብለው በነበሩት ጊዜያት አጀብ ለሚወደው የማኅበራዊ ሚዲያ ሰለባ መሆኑ። ሰለባ ሆኗል ለማለታችን…የዚህ ማንነቱ መጨረሻ ለማኅበራዊ ሚዲያው ቆማሪዎች እንጂ ለእርሱ ሕይወት አንዳችም ጠብ ያደረገለት ባለመኖሩ ነው። በእርሱ ዝነኝነት ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ሲበሉ የነበሩ ሁሉ ከካሜራው በስተጀርባ በነበረው የሕይወት ምስቅልቅሉ ውስጥ አንድም ቀን አነበሩም። የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ “14 ሺህ መጽሐፍትን ያነበበው አርቲስት…” ከሚለው ሐረግ ላይ ልዩ ልዩ ቃላትን እየቀጣጠሉና የሚወደውን የመጠጥ ብርጭቆ አስጨብጠው በየማኅበራዊ ሚዲያው ሲያቀጣጥሉት ለሳምንት ያህል ተፋፋመ። ፍልስፍና የሚወደው ጌታቸው ካነበባቸው መካከል በብዕር ስሙ የተረጎማቸው እንዳሉም ይነገርለታል።

ባቡጂን በሁለት በተለያዩ አጋጣሚዎች አግኝቼው አውቃለሁ። ለሁለተኛ ጊዜ ሳገኘው በእርግጠኝነት ዓመት ከመንፈቅ ይሆናል። ከጦር ኃይሎች አልፎ ቀራኒዮ አደባባይ ፊት ለፊት፣ ከአንድ ሬስቶራንት ደጅ ላይ ካለ የጀበና ቡና ቁጭ ብዬ ዓይኖቼን ጎዳናው ላይ ተክዬ እንዳፈጠጥኩ ነበር። ያ በየፊልሙ ላይ እርሱን ብዙ ከመመልከቴ የተነሳ ፊቱን የራሴ ያህል የማውቀው ጌታቸው እጅጉ (ባቡጂ) እያነከሰ ቅዝዝ ባለ አረማመድ ከፊት ሲመጣ ተመለከትኩት። መጥቶም አጠገቤ ከነበረው ሦስተኛ ወንበር ላይ ቁጭ አለ። በየት በኩል እንዳዘዛት ባላውቅም አስተናጋጇ አንድ ሊትር ውሃና የቡና ሲኒ አምጥታ ፊቱ ከነበረው ወንበር ላይ አኖረችለት። ደግሞ ውስጤ ሌላ አንድ ጥርጣሬ ገባ። ፊልሞቹ ላይ ሁሉ ስመለከተው ሾጠጥ ካለው አስቂኝ ፊቱ ጋር የነበረው ነብሰ ቀጭን ሰውነቱ… አሁን ግን ከለበሰው ሙሉ ፒጃማ ስር ተነፋፍቷል። ከፊቱ ላይ ቅላት ፈሶ ኩፍ ስላለ ሲነኩት ስርጉድ የሚል ያህል ድንቡሽቡሽ ሆኖ ይታይ ነበር። ከማንከሱ ጋር ተደማምሮ ይህ ሁሉ የጤና እንዳልሆነ ግን ለማንም በግልጽ የሚታይ ነበር። “ጌች!” አልኩት። በመጀመሪያ ዞሮ በጥርጣሬ ”አማን ነው…” ካለኝ በኋላ እንደማንተዋወቅ እርግጠኛ ሲሆን “በቃ ስማችን የተጻፈው ፊታችን ላይ ነው አይደል…” ብሎ እየቀለደ የዓይን ሰላምታውን ከቀልዱ ጋር አደረሰ። ቆይቶም… ሁኔታው ሁሉ እዚያ ፊልሙ ላይ ከነበረው የተለየ ምንም አልነበረውም። በመጀመሪያ ስለ እግሩ ነበር የጠየቅኩት። “…አለ አይደል..” ሲል ቀለል አድርጎ ጊዜያዊ ነገር እንደሆነ ነገረኝ። ልጁ ከማንም በላይ ዝነኛ ነው። የፊልም ተመልካች ቢሆኑም ባይሆኑም በተለይ በወጣቱ ዘንድ በሁሉም ታዋቂ ነው። ግን አንድ ነገር ግር ስላለኝ ልጠይቀው ስል በመሐል ሌላ አንድ ወጣት የአስፋልት ዳር ብረቱን እንደተደገፈ “ጃ!” ሲል ባቡጂ እጁን ከፍ አድርጎ ካወለበለበለት በኋላ “አሁን እንሂድ ወይንስ?” ሲል ጠየቀው። በጣም እንደሚቀራረቡ ያስታውቃል። ስለበኋላው ቀጠሯቸው በሦስት ቃላት ብቻ ተግባብተው ልጁ መንገዱን ቀጠለ። “ግን የዚህ ሰፈር ልጅ ነህ?” ስል ጠየቅኩት። “ከልደታ መርካቶና እዚህ የሺ ደበሌ ሁሉም ሰፈሬና ጓደኞቼ ናቸው…” አለኝ። ልደታ ተወልዶ ያደገባት ሰፈሩና የዘለዓለም ሙክራቡ ነበረች። አንተ ዝነኛ ነህ ግን እንዲህ ሰፈር ውስጥ ግን ዓይን አይበዛብህም? አልኩት እንደቀልድ። “ምን አሁንማ እኮ በቃ አብሬያቸው ስውል ሁሉም የቆሎ ጓደኛቸው አድርገውኝ አረፉት…” ሲል ቀለደ።

ያን ሁሉ ፊልም እንደሠራ ሰው ለዝነኝነቱ ቁብ ሰጥቶ ምንም ዓይነት የኩራት መንፈስ የሚታይበት አይደለም። ከሠራቸው 60 ፊልሞች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑትን ልክ እንደዚሁ ያላቸውን ተካፍለው ከሚበሉ የአዲስ አበባ መንደሮች ውስጥ የወጣና የሚኖር የሕዝብ ልጅ ሆኖ ነው የሚሠራው። ጌታቸው (ባቡጂ) በየፊልሙ ውስጥ እየተወነ ሳይሆን የራሱን ኑሮ እየኖረ እንደነበር የገባኝ ከዚያን ጊዜ በኋላ ነበር። በድጋሚ አግኝቼው ባላውቅም ፊልም በሠራ ቁጥር ሁሉ ይበልጥ እንድወደው አደረገኝ። ከሞቱ በኋላም አንድ ጓደኛው “ጌች ትምህርት ቤት አብረን የተማርን ጓደኞቹን ፍለጋ… ከዓመታት በኋላ ናፍቃችሁኛል እንገናኝ ሲል ከልደታ እስከ ጦር ኃይሎች በእግሩ እየዞረ ወረቀት በትኗል። ነገር ግን ካለንበት ሁኔታ አንጻር አብዛኛዎቻችን ትኩረት አልሰጠነውም ነበር..” ሲል ተናገረ። ጌታቸው ምን ያህል ሰው እንደተራበና እንዴት በሰው ፍቅር ልቡ እንደተናጠ ማሳያ ነበር። እንዲህ በሰው ራብ ሲቃትት የእውነትም በምግብ ረሀብ ሞቶ ከሆነ የምናውቅ ሁሉ ሕሊናችን በጸጸት ባሕር መሰርጎድ አለበት። ጦር ባንወረውርም ሳናውቅ የገደልነው ግን ብዙዎች ነን። በመብል እጦትና በመጠጥ ብዛት ባይሞትም አስቀድመን በፍቅር ረሀብ ገድለነዋል። ከገባን ይህ ዛሬም የሕይወት ትምህርት ነው።

ወጣቱ የባለ 60 ቀለማት የፊልም ዝናር ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም እስትንፋሱ ከባሩድ ጋር ፀጥ አለች። በነሐሴ 20 ቀን ደግሞ ግብዓተ መሬቱን በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ተፈጸመ።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You