ኢትዮጵያ እና የጤና ዲፕሎማሲ

የሰው ልጅ በዚህ ምድር መኖር ከጀመረ ጀምሮ እስካአሁን አንድ መቶ ስምንት ቢሊየን ሰዎች የኖሩበት እንደሆነ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በእርጅና፣ በተፈጥሮ አደጋ፣ በጦርነት፣ በረሀብ፣ በተለያዩ የበሽታ ዓይነቶችና ወዘተ ምክንያቶች አንድ መቶ ቢሊየን ሰዎች ሞተዋል፤ ቀሪው ስምንት ቢሊየን ሕዝብ አሁን በሕይወት ይገኛል፡፡ ከአንድ ምዕተ ዓመት በኋላ ደግሞ ጥቂት ታሪክ ተናጋሪዎች ብቻ ሲቀሩ አሁን በሕይወት ያሉት ሰዎች አልፈው በሌሎች አዲስ ትውልዶች ይተካሉ፡፡ ይህ የተፈጥሮ ግዴታና እውነታ ነው፡፡

ቶማስ ሮበርት ማልተስ የሚባል ሰው (እ.ኤ.አ 1766-1834 የኖረ) የዓለምን ሕዝብ በተመለከተ በፃፈው ጥናትና ንድፈ ሃሳብ (ቲዩሪ) የዓለም ሕዝብ ከሚመገበው የምግብና ሌሎች ሪሶርስ አንፃር ብዛቱ ካልተመጣጠነ በዓለም ላይ ከፍተኛ ችግር ይፈጠራል ይላል፡፡ በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱት የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች መኖርና የሕዝብ ቁጥር መቀነሱ አስፈላጊ ነው ይላል፡፡ ይህ ሃሳብ ደጋፊም ተቃዋሚም ያለው ነው፡፡

ለመንደርደሪያ ያክል ይህንን ካነሳን የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ሲኖር በጤና እንዲኖር ሀገራት የራሳቸው ፖሊሲና ሕግ ቀርፀው ይሰራሉ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም የጤና ድርጅቶች ተቋቁመው በሥራ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሀገራችንም ኢትዮጵያ የዜጎችን ጤንነት በተመለከተ በሕገ መንግሥት አንቀጽ 90 ላይ እንደደነገገችው የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጤና አገልግሎት እንዲኖረው ይደረጋል ይላል፡፡

በዚህ መሠረት በሀገራችን ላይ ያለው የጤና ሽፋን እየተስፋፋ ቢሆንም በቂ ግን አይደለም። ብዙ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ሰፋ ያለ ሥራ ከሌሎች ሀገሮችና ዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት በዲፕሎማሲ ማጠናከር ተገቢ ነው፡፡ ይህም ተግባር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የጤና ሚኒስቴር የጋራ ሥራ ይሆናል ማለት ነው፡፡

የዚህም ጽሑፍ ዋና አላማ የጤና ዲፕሎማሲ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን ሀገራችን ከአላት ሀብት በተጨማሪ የሌሎችን ድጋፍና ትኩረት በመሳብ ከጤና ጋር ያለብንን ችግሮች ለመቅረፍ ሲሆን፤ እንደአስፈላጊነቱም ኢትዮጵያ ያላትን ውስን ሀብት ለሌሎች ሀገሮች የምታካፍልበትንም ለመጠቆም ነው፡፡ ከርዕሱ ለመረዳት እንደሚቻለው የጤና ዲፕሎማሲ የሚለው ሃሳብ የጤና ሥራ እና የዲፕሎማሲ ሥራ ተናበውና ተቀናጅተው መሥራትን ያመለክታል፡፡

የሀገራችንን የጤና ዲፕሎማሲ ታሪካችንን በተመለ ከተ የውጭ ሀገር ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ መድኃኒቶችን እንዲያመጡና የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረግ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የቀድሞ ነገሥታትም የውጭ ሀገር የህክምና ባለሙያዎችን በማስመጣት የግል ሐኪሞች በማድረግ ይጠቀሙ ነበር፡፡ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ የባሕል መድኃኒቶችን ከበሽታ ለመፈውስ ይጠቀም ነበር፡፡

ጣልያን በወረረችን ጊዜ በርካታ ሀገሮች የገንዘብ፣ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሰረተው ሆስፒታል የዳግማዊ አጼ ምኒልክ መታሰቢያ ሆስፒታል ሲሆን በ1901 ዓ.ም ነበር የተመሰረተው፡፡ ይህም ሆስፒታል መመስረት አሁን ለደረሰንበት የህክምና ሥራ ጥሩ መሰረት ሆኗል፡፡

ከዲፕሎማሲ አንፃር በሀገራችን የተመሰረቱ ሆስፒታሎችን ስንመለከት ደግሞ የጋንዲ ሆስፒታል እ.አ.አ በ1958 ዓ.ም በህንድ የተመሰረተ፤ የዓድዋ ጦርነት ጀግና በሆኑት የደጃዝማች ባልቻ ስም እ.ኤ.አ 1947 በሩስያ ቀይ መስቀል የተመሰረተ ሆስፒታል፤ እ.ኤ.አ 2008 የቤጂንግ-ቻይና ኦሎምፒክ ሁለት ወርቅ በአመጣችው የጥሩነሽ ዲባባ ስም የተሰየመው ሆስፒታል በቻይና ተገንብቶ ወደ ሥራ ገብቷል።

በኮሪያ ጦርነት ያደረግነውን ድጋፍ ታሳቢ ያደረገ በቅርብ ዓመታት ውስጥ አዲስ አበባ ላይ የተሰራው የኮሪያ ሆስፒታል እንዲሁም በርካታ የጤና ተቋማትና በውጭ ሀገራት ድጋፍ ተቋቁመው በሥራ ላይ እናገኛቸዋለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO)እና የበርካታ የጤና ተቋማት አባል በመሆኗ የጤና ድጋፎችን እያገኘች ነው፡፡ ይህ ተግባር በሀገራችን ያለውን የሀብት ውስንነት በመቅረፍ የጤና ሽፋን አሁን ከአለው በተሻለ ደረጃ ለማድረስ ያግዛል፡፡

ዲፕሎማሲ ማለት ሰጥቶ መቀበል መርህን የሚከተል እንደመሆኑ ከጤና ዲፕሎማሲ ሥራ ኢትዮጵያ የምትቀበለውን ድጋፍ ብቻ ትኩረት ማድረግ ሳይሆን ለሌሎችም መስጠት የምትችለውን የሚመለከት ነው። ለአብነት ያክል የኢቦላ ወረርሽኝ በምዕራብ አፍሪካ ሲስፋፋ ኢትዮጵያ ሁለት መቶ(200) የሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎችን እና የገንዘብ ድጋፍ በመላክ የጤና አጋርነቷን አሳይታለች፡፡

በተመሳሳይም የኮቪድ ወረርሺኝ ዓለምን ባስጨነቀበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የህክምና እና የበሽታ መከላከያ ቁሳቁሶችን በመውሰድ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 ኢትዮጵያ ሰላሳ አምስት ዶክተሮችን ወደ ኤርትራ በመላክ የበጎ ፈቃደኛ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጋለች፡፡

የጎረቤት ሀገራትን ከመደገፍ አንጻርም ኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራት የህክምና ዶክተሮች በሀገራችን እንዲማሩ አድርጋለች፡፡ ለአብነት ያክል አንድ መቶ አርባ አምስት(145) የደቡብ ሱዳን ወጣቶች የህክምና ትምህርት(ዶክትሬት) በሀገራችን እንዲያገኙ ስኮላርሺፕ ሰጥታለች፡፡ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኔዘርላንድ ለደረሰባት የተፈጥሮ አደጋ ኢትዮጵያ ድጋፍ የሰጠች መሆኑ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

የጤና ዲፕሎማሲ ማከናወን በርካታ ጥቅሞችን የሚያመጣ ሲሆን አቅም በፈቀደ መጠን ለተቸገሩ ስንደርስ የጋር ኃይልን (soft power) ለማስፋት የሚያግዝ ሲሆን፤ አቅማቸው ከፍ ያሉ ሀገራት ጋር በሚኖረን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ደግሞ ያሉብንን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያግዝ ድጋፍ እናገኝበታለን፡፡ የጤና ዲፕሎማሲ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ውስጥ በዋናነት የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

የጤና ጋር የተያያዙ መዋዕለ ነዋይ (ኢንቨስትመንት) ከውጭ ለመሳብ

በሀገራችን የሚገኙ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ስንመለከት በዋናነት ምርት ላይ ያተኮሩ ናቸው (manufacture)፡፡ በጤና ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ የውጭ ባለሀብቶች ግን እጅግ አነስተኛ ናቸው፡፡ ጤና ዙሪያ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉ ባለሀብቶች ወደ ሀገራችን መጥተው እንዲሰሩ ማድረጉ የተሻለ ህክምና ለማግኘት ወደ ውጭ ሀገር እየሄዱ የሚታከሙ ዜጎችን በሀገራቸው እንዲታከሙ ማድረግ የሚያስችልና አዋጭ መሆኑን ለባለሀብቶች ማሳየት ተገቢ ነው፡፡

በጤና ዘርፍ ኢንቨስት የሚያደርጉ የዲያስፖራ አባላት ወይም የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለአብነት ያክል በቻይና ኢንቨስት የተደረገው Silk Road General Hospital መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ ሆስፒታል በኢትዮጵያ እንዲመሰረት ለማድረግ የተቻለው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ተሰርቶ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም የጤና ሽፋንን ለማስፋት የጤና ዲፕሎማሲ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል፡፡

የእውቀት ሽግግር ለማከናወን

በጤና ዲፕሎማሲ ከሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ ከጤና ጋር የተያያዙ ከአደጉ ሀገሮች የሚፈስ እውቀት አንዱ ነው፡፡ ጤናን በተመለከተ አዳዲስ ፈጠራዎች ወደ ሀገራችን እንዲገቡ በማድረግ የህክምና አገልግሎትን ጥራት መጨመር ይቻላል፡፡ የእኛም የጤና ዲፕሎማሲ በሥራ ላይ ለሚገኙ የህክምና ዶክተሮችና ባለሙያዎች የስኮላርሺፕ በማመቻቸት አዳዲስ የህክምና መሣሪያዎች ወደ ሀገራችን እንዲገቡ በማድረግ፣ በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞችን (Volunteer) ወደ ሀገራችን መጥተው የተለየ እውቀታቸውን የሚያስተላልፉበትና ወዘተ ሥራዎችን መሥራት ያስችላል፡፡

ፋይናንስ ለማፈላለግ

በሀገር ደረጃ ያለውን የጤና ፍላጎት ለማሟላት የመንግሥት በጀት ብቻውን ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለአላት ሀገር በቂ እንዳልሆነ ይታወቃል።በመሆኑም በጤና ዲፕሎማሲ ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በመገናኘትና የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት ለሀገራችን የጤና ሥራ የሚያገለግል ፋይናንስ ማግኘት ይቻላል፡፡ በተለይ ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎችን ለማከም የሚደረገውን ፍላጎትና ተግባር ለማገዝ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ የጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ ተቋማት ጋር በአጋርነት እየሰራ እንደሚገኝ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድህረ-ገፅ ያሳያል፡፡ ይህንን ማስፋት የሚቻለውም በጤና ዲፕሎማሲ ነው፡፡

ጤና የሚጎዱ ምርቶች ከውጭ እንዳይገቡ ለማገድ

ዲፕሎማቶች ከተመደቡበት ሀገር እና ከሌሎች ሀገሮች ወደ ሀገራችን የሚገቡ ምርቶች ጥራት ላይ መረጃዎችን በማሰባሰብ መንግሥትን የሚመክሩበትና አላስፈላጊ ምርቶች ሰርገው ገብተው የጤና ችግር እንዳይፈጥሩ የማድረግ ሥራን ሊያግዙ ይችላሉ፡፡ በተለይ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዘኑ እና ደረጃቸውን ያልጠበቁ መድኃኒቶች ከውጭ እንዳይገቡ ለማድረግ ያስችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት መድኃኒቶች ሁለት ጉዳቶችን ያመጣል፡፡ አንዱና ዋናው ጉዳት የታመሙ ሰዎች መድኃኒቱን ተጠቅመው መዳን አይችሉም፤ የጎንዮሽ ችግርም ሊያመጣባቸው ይችላል። ሁለተኛው ችግር ደግሞ ማዳን የማይችል መድኃኒት ለመግዛትና ለማጓጓዝ የውጭ ምንዛሪ መውጣቱ ነው፡፡ የጤና ዲፕሎማሲ ይህንን የመሰል ዘርፈ ብዙ ኪሳራ ሊታደግ ይችላል፤፤

በዓለም ላይ የሚከሰቱ ወረርሽኞች ወደ ሀገር እንዳይገቡ የጥንቃቄ ሥራ ለማከናወን

በተለያዩ ጊዜያት በዓለማችን ላይ ወረርሽኞች ይነሳሉ፡፡ ከአንዱ ሀገር ወደሌላው በመዛመት ሕዝብ ይጨርሳሉ፡፡ የቅርቡን ኮቪድ 19 እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህን መሰል ወረርሽኝ ሲነሳ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ለማድረግና የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ያስችላል። በተለያዩ ሀገራት የተመደቡ ዲፕሎማቶች ስለተመደቡበት ሀገር የጤና ሁኔታ ላይ መረጃ ለማግኘት ብዙም አይቸገሩም፡፡ ይህ መረጃ ግን ለሀገራችን የጤና ሥራ በጣም ጠቃሚ ነው። በሽታ እንዳያስተላልፉ እንደአስፈላጊነቱ ወደ ሀገራችን ሰዎች እንዳይገቡ ቪዛ እስከ መከልከልም የሚያደርስ ውሳኔ ሊያስከትል ይችላል፡፡

ከጤና ጋር የተያያዙ ድርድሮችን ለማከናወን

ሀገራት የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የሚያከናውኑ ሲሆን በዚህ ሂደት ውስጥ የድርድር ክህሎት ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ክህሎት በዋናነት በዲፕሎማቶች አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የድርድር ተግባራትን የማገዝ እና የብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ሥራ ለማከናወን ያግዛል፡፡ ከድርድር በፊት የሚከናወኑ ቅድመ ዝግጅቶች ላይም ዲፕሎማቶች የተለያዩ ሥራዎችን ሊሰሩ ይችላሉ። በተለይ ድርድሩ በውጭ ሀገር የሚደረግ ከሆነ ዲፕሎማቶች ቅድመ ድርድር ላይ ዝግጅትን ያግዛሉ፡፡ የድርድሩ ውጤት አተገባበር ላይም የጤና ዲፕሎማሲ መሥራት ያስችላል፡፡

ሀገራችን የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አተገባበር መከታተል

በዓለማችን ላይ ከጤና ጋር የተያያዙ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያም የፈረመቻቸው በርካታ ናቸው፡፡ ለአብነት ያክል በ1927 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር አባል ሆናለች። የእነዚህ ስምምነቶች አፈፃፀም ላይ በጤና ሚኒስቴር የሚቀርቡ ሪፖርቶች አቀራረብ ላይ በዲፕሎማሲ ሥራ ማገዝ ያስችላል፡፡ የሚቀርቡ ሪፖርቶች ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም እንዲደርስ ያግዛል፡፡

ዲያስፖራ ማህበረሰብን በጤና ዘርፍ ማሳተፍ

በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የሆነ የእውቀት፣ የማቴሪያል እና የገንዘብ ሀብት ባለቤቶች ሆነው ይገኛሉ። እነዚህ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ወደ ሀገራቸው ገብተው በጤና ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ፣ የህክምና መሳሪያ እና መድኃኒት እንዲያበረክቱ ማድረግ ይቻላል፡፡ በተለይ የህክምና ትምህርትና የሥራ ተሞክሮ ያላቸው የዲያስፖራ አባላት በሀገራችን ያለውን የጤና ክፍተት እንዲሞሉ በማስተባበር በርካታ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ ዲያስፖራዎች ሀብትና እውቀታቸውን አሰባስበው ሆስፒታል በአዲስ አበባም የከፈቱ አሉ፡፡ ይህንን መሰል ሥራ ለማከናወን የጤና ዲፕሎማሲ ሥራ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

ዓለም አቀፍ የጤና ኮንፍረንሶችን ለማከናወን

የጤና ዲፕሎማሲ ተግባር ውስጥ አንዱ የሆነው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶችን በሀገራችን እንዲከናወን የሎቢ(Lobby) ሥራ መሥራት ነው፡፡ ይህ ተግባር ስለጤና የሚከናወነው ኮንፍረንስ ከሚሰጠው እውቀት በተጨማሪ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ለማከናወንም ያግዛል፡፡ የሀገራችንም የህክምና ባለሙያዎች የጥናትና ምርምር ውጤቶቻቸውን የሚያቀርቡበትን እድል ይፈጥራል፡፡ በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች በውጭ ሀገር ሲከናወኑ የሀገራችን ምሁራን የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በጤና ዲፕሎማሲ አማካኝነት ድጋፍ እንዲኖር ያስችላል፡፡

የምርምር ውጤቶች በታዋቂ ጆርናሎች እንዲታተሙ ማገዝ

የጤና ሥራ እና ምርምር በእጅጉ የተያያዙ ናቸው፡፡ የሀገራችን የህክምና ዶክተሮችና ባለሙያዎች የሚፅፏቸው የምርምር ውጤቶች በውጭ ሀገር ታዋቂ ጆርናሎች ላይ ሲታተሙ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንን መሰል የምርምር ሕትመቶች እንዲወጡ የዲፕሎማቶች ድጋፍ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በተለያዩ ሀገራት ተመድበው የሚሰሩ ዲፕሎማቶች የትኛው ጆርናል ስመጥርና ተነባቢ ነው የሚለውን መረጃ በቀላሉ ማግኘት ስለሚችሉ የሀገር ውስጥ የህክምና ባለሙያዎችን ሊያግዙ ይችላሉ፡፡

የሌሎችን ሀገሮች ፖሊሲ ለመረዳትና ለመጠቀም

የጤና ዲፕሎማሲ ሥራ ትኩረት ከሚሰጣቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ የሌሎች ወሳኝ ሀገራትና አህጉራትን የጤና ፖሊሲ የመረዳትና ከዚያ ፖሊሲ በመነሳት የሀገር ጥቅምን ማፈላለግ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የአውሮፓ ህብረት የዓለም አቀፍ የጤና ስትራቴጂ(European Union Global Health Strategy) አለው፡፡ በተመሳሳይም አሜሪካና ሌሎች ኃያላን ሀገራት ይህንን መሰል ስትራቴጂዎች አሏቸው፡፡ ቻይናም ተመሳሳይ የጤና ስትራቴጂ (Health Silk Road) አላት፡፡ እነዚህ ስትራቴጂዎች ሲተገበሩ ለሀገራችን ሊያበረክቱ የሚችሉት ጥቅም ምን እንደሆነ በማጥናትና በዲፕሎማሲ ጥበብ በመታገዝ ብሔራዊ ጥቅም ላይ መሥራት ያስችላል፡፡

የሀገራችን የመድኃኒት ፋብሪካ ገበያ ማፈላለግ

በሀገራችን የተለያዩ የመድኃኒት ፋብሪካዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ጥቂት ፋብሪካዎች የሚያመርቷቸው መድኃኒቶች ከሀገር ፍላጎት በላይ ሲሆኑ የውጭ ገበያ የሚያስፈልጋቸው በመሆናቸው የጤና ዲፕሎማሲ ሥራ ይህንን ተግባር በማከናወን ፋብሪካዎች እየተጠናከሩና እየተስፋፉ እንዲሄዱ ያስችላል፡፡ ልክ ለቡና እና ለቅባት እህሎች ምርቶቻችን ዲፕሎማቶች ገበያ እንደሚያፈላልጉ ሁሉ ለመድኃኒት ምርቶቻችንም ገበያ ማፈላለግ ያስችላል።

የጤና ምርምር ተቋማትን የማገናኘት

የጤና ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ በመሆኑ የተለያዩ ሀገራት ከጤና ጋር የተያያዙ የጥናትና ምርምር ተቋማትን የማቋቋም ሥራ ያከናውናሉ፡፡ በእኛም ሀገር የጤና የምርምር ተቋማት የሚገኙ ሲሆን ውጪ ከሚገኙ መሰል ተቋማት ጋር በጋራ እንዲሰሩ ለማስቻል የጤና ዲፕሎማሲ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የምርምር ተቋማት በጋራ ጥናትና ምርምር እንዲያከናውኑ፣ ተሞክሮ እንዲቀያየሩ፣ የውይይት መድረክ በጋራ እንዲያዘጋጁ፣ ሥልጠናዎችን አንዱ ለአንዱ እንዲሰጥ እና የመሳሰሉት ሥራዎችን ሊሰሩ ይችላሉ፡፡

ለማጠቃለል ያክል የጤና ዲፕሎማሲ ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ለሀገራችን እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ ሥራ ፍጹም ያልተሰራ ነው ለማለት ሳይሆን አስፍቶና አጠናክሮ መሥራት ወቅቱ የሚጠይቀው ነው ለማለት ነው፡፡ ይህን ተግባር በተለያዩ የአሰራር ሥርዓት ሊተገበር ይችላል፡፡ አንዳንድ ሀገሮች የወታደር፣ የባሕል፣ የጤና አታሼ በኤምባሲዎች በመመደብ በየዘርፉ የዲፕሎማሲ ሥራ ያከናውናሉ፡፡ እኛም በተመረጡ ጥቂት ሀገሮች ውስጥ የጤና አታሼ እንዲመደቡ ወይም የጤና ትምህርት ያላቸው ዲፕሎማቶች በዘርፉ ላይ ተመድበው እንዲሰሩ ማድረጉ ጠቃሚ መሆኑን የግል አስተያየቴን እያቀረብኩ ጽሑፌን በዚሁ እቋጫለሁ፡፡

ከመላኩ ሙሉዓለም ቀ.

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የሥልጠና ዳይሬክተር ጄኔራል

melakumulu@yahoo.com

 አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You