ፒያሳ ሲባል በተለይ ለአዲስ አበቤው እምብርት በመሆኑ የማያውቀው የለም:፡፡ በዘመናችን በአራዳ ክፍለ ከተማ ሥር የታቀፈችው ፒያሳ ፤ አራዳ በሚል ስያሜ ትጠራ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ስምና ዝናዋ የፀናው ግን በፒያሳ አካባቢ ነበር፡፡ በወቅቱ መዲናዋ ስትቆረቆር አደይ አበባ የደራበት የአዲስ ዓመት ወቅት ስለነበር እቴጌይቱ (ጣይቱ) አዲስ አበባ ትባል ብለው ሰየሟት፡፡
ቤተመንግሥታቸውንም ከእንጦጦ ወደ ምኒሊክ ቤተመንግሥት (አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት አሻግረው ተቀመጡ)፤ ይመስለኛል በእንጦጦ ብርድ (የቂጥኝ ሕመም ነበረባቸው) እያዘኑ ስለነበር በፊንፊኔ ፍልውሃ ሊዝናኑና ሊጽናኑ ሽተው ነው፡፡ እቴጌይቱ በፊኒፊኔ ፍል ውሃ በመነከር ጊዜያዊ ማስታገሻ ያገኙ እንደነበር ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ በተደጋጋሚ ከእንጦጦ በመውረዳቸው ምክንያት በህዳር 1878 ዐፄ ምኒልክ ሐረርጌ በዘመቱበት ወቅት አሁን ታላቁ ቤተ መንግሥት በሚገኝበት ቦታ ቤት እንዲሠራና አዲስ ከተማ (ክፍለ ከተማውን አለመሆኑ ይታወቅልንና) እንዲቆረቆር ትእዛዝ ሰጡ፡፡
ዛሬ በአራዳ ክፍለ ከተማ ሥር የምትገኘው ፒያሳ የተመሠረተችው በአምስቱ ዓመት የጣሊያን ወረራ ወቅት ነበር፡፡ ሰነዶች እንደሚያስረዱት ፒያሳ ስትመሠረት ለጣሊያች መኖሪያና መዝናኛ ታስባ ነው። ቀደም ሲል ግን በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን አራዳ የሚል ስያሜ ነበራት፤ የክፍለ/ከተማዋም ብሎም የሀገሪቱ የመጀመሪያው ሆቴል የሆነው የጣይቱ ሆቴል ያለባት ሥፍራ ነች፡፡ ዘንድሮ ምዕት(100) ዓመቱ የተከበረለት የቴአትር መድረክ መሠረቱ በጣይቱ ሆቴል ነበር፡፡
በወቅቱ በ1913 ዓ.ም ፊታውራ ተክለሐዋርያት ተክለ ማርያም የእንስሳት ፋቡላ ወይም የአውሬዎች ኮሜዲ በሚል ለአንድ ቀን ብቻ ታይቶ የተገታ ነበረ፡፡
ፒያሳ በአራዳ ጊዮርጊስ አድርጎ ገዳም ሠፈር ፣ ሰባራ ባቡር፣ ከአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ በኢየሩሳሌም ህንፃ ፣ ካቴድራል ትምህርት ቤት በበኒን መስጊድ፣ ወደ ቸርችል ጎዳናን ተሻግሮ በጣይቱ ሆቴል እና በብሔራዊ ሎተሪ ሕንፃ በኩል ወደ እሪ በከንቱና ሠራተኛ ሰፈር ያሉትን መንገዶች ያጠቃልላል፡፡ ደጎል አደባባይ (በጣም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ እኔን አደባባይ ያድርገኝ ብዬ የማዝንበት ነው፤ ለነገሩ አደባባዩ በተሠራ ዘመን የትራፊክ መጨናነቅ ስላልነበር በርግጥም አደባባይ ነበር) እና ራስ መኮንን ድልድይ ያሉትን አካባቢዎች ያካትታል። ዛሬ ፖሊስ የምንለው ሥራውን የጀመረው በአራዳ ፒያሳ ሲሆን ስሙም የአራዳ ዘበኛ የሚል ነበር። በደጎል አደባባይ ወደ ሠራተኛ ሠፈር ስትወርዱ አስፋልቱ በጣም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ ለጋሪ እንጂ ለተሽከርካሪ የተሠራ አይመስልም፡፡
እዚህ ላይ ግን በኮረና ወረራ ዝናዋንና ሕልውናዋን ያጣችው ነፍሷን ይማራትና አትክልት ተራም (ግን ጎበዝ አትክልት ተራን ብዙ ልጆች በየቦታው ወልዳ እነሱን ለማሳደግ እየተንጎዳጎችና እየተንገዳገደች ከሩቁ አየናት ያሉኝም አሉ)፡፡ በፒያሳ ሥር እንደነበረች ይመዝገብልኝ። በፒያሳ እንደነበረው አትክልት ማከፋፈያ ሁሉ መርካቶም አትክልት ተራ የሚባል ቦታ ከአመዴ ገበያ በታች ነበራት፡፡ ሊዝ መጣና ቦታዋ ህንፃ ተሠርቶበት ዛሬ አትክልት በየዓይነቱ ባይሆንም አልባሳት በያይነቱ ይሸጥበታል፡፡
ጣልያን ፒያሳን ለዘናጮች ነጮች የታጨች መንደር አድርጓት ለአምስት ዓመት ከረመባት ፤መርካቶ ደግሞ ለሀበሾች የተሠራች የመዝናኛ እና የመገናኛ መንደር አድርጎ አጠረ፡፡ እናም ማንኛውም ጥቁር ፒያሳ ከሄደ ደንብ በመተላለፍ ይታሰር እና ይቀጣ ነበረ፡፡ ስለ ፒያሳ ስናስብ ዝነኛው ሀገር ፍቅር ቲያትርን እናስታውሳለን ሲኒማ አምፒርም እንዲሁ፡፡ በተለይ አገር ፍቅር ትያትር ቤት ከጣሊያን ወረራ በኋላ ፈር ቀዳጅ የስነጥበብና ሙዚቃ አድባር የሚዘራበት ቦታ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ዝነኛ ድምጻውያን የወጡት ከሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ነው። በማዘጋጃ ቤት የነበረው በእድሳት የተዘጋው የአዲስ አበባ ትያትርና ባህል አዳራሽም ሳይዘነጋ፡፡
በኢትዮጵያ የከተሞች ርቀት የሚለካው ፒያሳ አራዳ ጊዮርስ እና ማዘጋጃ ቤት አጠገብ ከሚገኘው ከዳግማዊ ምኒሊክ አደባባይ ዞር ተብሎ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የማዘጋጃ ቤት ህንፃ የሚገርም ስልትና ውበት የሚታይበት ህንፃ ነው፤ ንጉሥ ኃይለሥላሴን እናደንቃለን፤ በዘመናችን አዲስ አበባ ውስጥ የሚሠሩት አብዛኞቹ ህንፃዎች በአንድ ወቅት አንድ ጸሐፊ እንደገጹት የበርሜል ቅርጽ አልያም የቁም ሳጥን ቅርጽ ያላቸው ናቸው ያሉት ይታወሰኛል፡፡ የማዘጋጃ ቤት ህንፃ የከተማው ትልቁ ውበት ነው፡፡ አራተኛ ፎቅ ላይ ወጥታችሁ 75 በመቶ የሚሆነውን የከተማውን አካባቢና አጎራባች ቦታዎችን (በአራዳ ጊዮርጊስ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ካልሆነ በስተቀር) የሚያሳይ ስትራቴጂክ የሆነ ቦታ ላይ የተሠራ ነው፡፡
ፒያሳ የአዲስ አበባ አስተዳደር ማዕከል ወይም የማዘጋጃ ቤት ህንፃ የከንቲባ (Mayor) ባለቤት ነች። በነገራችን ላይ ከንቲባ የሚለው ቃል ግእዝ ሲሆን ‹ካንተ ዘንድ ይባዕ› የሚለው ቃል ተጨምቆ የወጣ ነው፡፡ ካንተ ይባዕ ማለት ካንተ ይግባ ማለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ከንቲባ ቢትወደድ ወልጻዲቅ ጐሹ ነበሩ፣ ወሰኔ ዛማኔል፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፣ ደጃች. ታከለ ወ/ሐዋርያት (ከጣሊያን ወረራ በፊትና በኋላ) ደጃች.ዘውዴ ገብረሥላሴ፣ ዘውዴ ገብረሕይወት፣ አርከበ ዕቁባይ የሚጠቀሱ ነበሩ፤ በዘመናችን ሸገርን በምክትል ከንቲባ እየመሩ ያሉት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ይጠቀሳሉ፡፡
የአዲስ አበባን ምስረታን ለማወቅና የቁሳዊና ባህላዊ ታሪክ ቅርስ ቅሪቱ ያለው ፒያሳ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በጣልያን ዘመን የተሠሩ ባለ አንድ ሁለት ፎቅ ህንፃዎች መኖሪያ ቤቶች ንግድ ቤቶች ሆቴሎች ይታያሉ፡፡ በተለይ ከራስ መኮንን ድልድይ ወደ ኤሌክትሪክ ህንፃ ግራ እና ቀኝ ያሉት ህንፃዎች በማየት መቃኘት ይቻላል፡፡ በሥፍራው እስከ ደጎል አደባባይ የወርቅና ብር ቤቶች መሸጫዎች ይታያሉ ምግብ ቤቶችን ልብስ መሸጫ መደብሮችም እንዲሁ ፡፡ ሠራተኛ ሰፈርና ዶሮ ማነቂያም አስፋልት ዳር የሚታዩ ቤቶች የእድሳት ያለህ የሚሉ በእንጨት የተሠሩ ባለ አንድ ፎቅ ቤቶች ሲሆኑ የምድር ቤቱ በአብዛኛው ለንግድ ፤ ፎቁ ደግሞ ለመኖሪያ የሚያገለግል ነው፡፡ ኬክ ቤቱ ቡና ቤቱ ሬስቶራንቱ በየቦታው ፈሶ ታያላችሁ፡፡
ሠራተኛ ሠፈር ከደጎል አደባባይ ወረድ ብሎ የሚገኘው ጠባብ አስፋልት ያለበት ነው፡፡ በሠፈሩ ብዙ ጥንታዊ ቤቶች ይታያሉ፤ በአካባቢው የተሠራው ኮንዶሚኒየም ሳይቀር የአሠራር ስልቱ ከአካባቢው ሕንፃዎች ጋር የሚዛመድ ነው፡፡ ጎስቆልቆል ያለ የህንድ ትምህርት ቤትም አለ፡፡ ህንዶች ያድሱታል ብለን እንጠብቃለን፡፡
በምኒሊክ ዘመን የአራዳ ዘበኞች (ፒያሳ) አካባቢን ይጠብቁ ነበር፡፡ በሠራተኛ ሠፈር ከጀርባው ደግሞ የእሪ በከንቱ ሠፈር አለ፡፡ ጫካና በርከት ያለ ሴተኛ አዳሪ ነበረበት፡፡ መሸት ሲል ዘረፋ ይፋፋም ስለነበር ማጅራት መቺዎች በጫካዎች ይገኙበት ነበር፡፡ አላፊ አግዳሚውን ይዘርፉታል፤ ሴተኛ አዳሪ የገባውም ሲወጣ ከሴቶቹ በገንዘብ ይጋጭ ስለነበር ፤ ጎረቤት ሴተኛ አዳሪዎች ተባብረው ዱላና ዘነዘና ይዘው ሊደበድቡት ይነሱ ነበር፤ ዘራፊዎች አጋጣሚውን አይተው ሰውየው ፈርቶ ሲሄድ ይዘርፉታል ቢጮኽም የሚደርስለትም ስለሌለ (የአራዳ ዘበኛም ቢመጣ አያስጥልም ለራሱም ይፈራል የሚሉ ሰዎች አጋጥመውኛል፤ ‹‹ የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም›› እንበለው) እሪ በከንቱ ተባለ። በቦታው ፒያሳ ዳና ናፖሊ ሬስቶራንት በአማርኛ የጣሊያን ምግብ ቤት የሚል ጽሁፍ ያለበት ህንፃ ይታያል፡፡ በአካባቢው የተሠራ ባለአምስት ፎቅ ህንፃ የዛኔውን ዘመን ህንፃዎች ስልትና ስሪት የሚያሳይና ውበት ያለው እናት ህንፃ አለ።በአጠቃላይ በፒያሳ የጣሊያኖች የህንዶች የአርመኖች የየመኖች አሻራ አሁንም ይታያል፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2014