እስራኤል በኔታንያሁ ላይ ያነጣጥር የነበረ የግድያ ሴራን አከሸፍኩ አለች

እሥራኤል በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ ሊቃጣ የነበረ የግድያ ሙከራን ማክሸፏን አስታወቀች።

የሀገሪቱ ፖሊስና የደኅንነት መሥሪያ ቤት (ሺን ቤት) በጋራ ባወጡት መግለጫ፥ በኢራን በሚደገፈው የግድያ ሴራ ሲሳተፍ ነበር የተባለ እሥራኤላዊ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።

ተጠርጣሪው ኔታንያሁ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት እና የሀገር ውስጥ የደኅንነት ተቋሙ ኃላፊ የሚገደሉበትን መንገድ በተመለከተ በተደረጉ ውይይቶች ተሳትፏል ይላል መግለጫው።

በቁጥጥር ስር የዋለውን ተጠርጣሪ ስም መግለጫው ባይጠቅስም የእሥራኤል መገናኛ ብዙኃን የ73 አመቱ የአሽኬሎን ከተማ ነዋሪ ሞቲ ማማን መሆኑን ዘግበዋል።

ለቢዝነስ ጉዳይ ለመምከር በቱርክ አድርጎ ወደ ኢራን እንደገባ ከቴህራን መውጣት እንደማይችል የተነገረው ተጠርጣሪው ከኢራን የደኅንነት ባለሥልጣናት ጋር እንዲገናኝ ተደርጎ ተልዕኮዎች እንደተሰጡት ነው ሺን ቤት የገለጸው።

ለቴህራን ገንዘብና መሣሪያዎችን ማዘዋወር፣ በእሥራኤል ሰዎች በብዛት የሚገኙባቸውን አካባቢዎች ፎቶግራፍ አንስቶ መላክና ሌሎች ተልዕኮዎች ተሰጥቶት ወደ እሥራኤል ቢገባም የተባለውን ሳያደርግ ዳግም ወደ ኢራን መመለሱንም ጠቅሷል።

በነሐሴ ወር ወደ ኢራን ሲመለስ የሽብር ጥቃት እንዲፈጽም አልያም የእሥራኤል ባለሥልጣናትን እንዲገድል ጥያቄ ቀርቦለት 1 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈለው ጠይቆ የቴህራን ባለሥልጣናት ጥያቄውን ሳይቀበሉት መቅረቱንም ነው መግለጫው ያብራራው። በግድያ ሴራ ስብሰባዎቹ በመሳተፉ ግን 5 ሺህ 570 ዶላር እንደተከፈለውም በመጥቀስ።

እሥራኤል፥ በኢራን የሀገሪቱን ዜጎች ጭምር በመመልመል የስለላ ሥራ የማከናወን የረጅም ጊዜ ልምድ አላት። በሐምሌ ወር የሃማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ በቴህራን መግደሏም የዚህ ማሳያ ተደርጎ ይነሳል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You