ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ በአሜሪካ የመጀመሪያውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸውን ሊያደርጉ ነው

የዓረብ ኢምሬትስ ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህንያን በአሜሪካ የመጀመሪያቸው የሆነውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሊያደጉር ነው።

ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ በአሜሪካ የሚያደርጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት የፊታችን ሰኞ መስከረም 12 እንደሚጀምሩም ከዓረብ ኢምሬትስ የዜና አገልግሎት ዋም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህንያን የዓረብ ኢምሬትስ ፕሬዚዳንት ሆነው ሥልጣን ከያዙ በኋላ በአሜሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው እንደሆነም ተነግሯል።

ፕሬዚዳንቱ በአሜሪካ ነጩ ቤተ መንግሥት ዋይት ኃውስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይፋዊ አቀባበል እንደሚደረግላቸውም ተነግሯል።

ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ በአሜሪካ ቆይታቸውም ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር እንዲሁም ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።

ከዋነኛ የውይይት አጀንዳዎቻው ውስጥም ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የአሜሪካ እና የዓረብ ኢምሬትስ ስትራቴጂካዊ አጋርነትን የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚያተኩር ተነግሯል።

በተለይም በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና የህዋ ምርምር እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ እና በታዳሽ ኃይል ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።

ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ እና ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር በዓለም አቀፋዊ እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩም የሚጠበቅ ሲሆን፤ የጋዛው ጦርነት እና የሱዳን ጦርነትን በውይይታቸው ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል ናቸው።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከሁለት ዓመት በፊት በመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከዓረብ ኢምሬትስ ፕሬዚዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ጋር ተገናኝተው መምከራቸው ይታወሳል።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከፕሬዚዳንት ሼህ መሐመድ ቢን ዛይድ ጋር ባደረጉት ውይይትም ከዓረብ ኢምሬትስ ጋር ያለውን ግንኙነት በሚጠናከርበት ዙሪያ መምከራቸው ይታወሳል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You