መስከረም ሲጠባ ኢትዮጵያውያን በልዩ መንገድ ገጽታቸው ይፈካል፤ አለባበሳቸው ይደምቃል። የነሐሴ ጨለማ የጳጉሜን ካፊያ ለበጋው ወራት ተራቸውን ለመልቀቅ ዳር ዳር ይላሉ። የክረምቱ ማብቂያ መስከረም የኢትዮጵያውያንን ገፅታ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያንንም መልከዓ ምድር ያፈካዋል። ሜዳው ሸንተረሩ፣ ደጋው ወይና ደጋው አረንጓዴ ይለብሳል፤ ሰብል ደረስኩ ደረስኩ ይላል። ይህ ወቅት የመላው ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት የሚገባበት፣ ያለ ልዩነት ሁሉም በአንድነት ለመጪው ዓመት የሚዘጋጅበትም ነው።
ሜዳ ተራራው በአደይ አበባ ይደምቃል፤ ቢጫ ይሆናል፡፡ ቢጫ ቀለም ተስፋ እንደሆነው ሁሉ አደዩም የሀገሪቱን መልከዓ ምድር ቢጫ ቀለም በማልበስ ይህን ተስፋ ያስተጋባል፡፡
በመስከረም ወቅት ልክ ሜዳው ሸንተረሩ በአንድ አደይ አበባ እንደሚደምቀው ሁሉ ኢትዮጵያውያንም ይዋባሉ። ዘመድ፤ ወዳጅ፣ ቤተሰብ ይጠያየቃል። በየአቅጣጫው እንቅስቃሴዎች ይበዛሉ፡፡
ተማሪዎች እውቀትን ለመገበየት የሚናፍቁበት ወር ነው፤ ወርሀ መስከረም። በመስከረም ሰው ብቻ ሳይሆን የቤት እንስሳቱ ይጠግባሉ፤ ከብቶች ለግጦሽ በተዘጋጀ ሜዳ ላይ ይቦርቃሉ። ምን አለፋችሁ መስከረም ለመላው ኢትዮጵያውያን የአዲስ ተሰፋ፣ የአዲስ እሳቤ፤ የአዲስ ዓመት መግቢያ ወር ነው።
በወርሀ መስከረም በሁሉም ዋልታ ለኢትዮጵ ያውያን በዓል ነው። ለዛሬ ግን እኛ ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሉ ጉራጌ ብሔረሰብ ዞኖች ለመሄድ ወደናል። የጉራጌ ብሔረሰብ ልክ እንደ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በቱባ እውቀት፣ ባሕልና እሴቶች ባለጸጋ ነው። በአንድ ጊዜ ‹‹እንዲህ ናቸው›› ተብለው ተነግረው የማያልቁ ተወዳጅና አስደናቂ እውቀቶች ባለቤት ነው።
የጉራጌ ብሔረሰብ የሚኖርባቸው የአሁኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሁለቱ የጉራጌ ዞኖች/ ቀደም ሲል ዞኑ አንድ ነበር/ በመስከረም ከሚደምቁ፣ በፍቅርና በደስታ ከሚያብቡ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ቀዳሚዎቹ ናቸው። ‹‹መስከረም ሲጠባ በመስቀል በዓል በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ጭር ይላል›› እስከ መባል መድረሱም ይታወቃል። በከተማዋ የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች የመስቀል በዓልን ለማክበር፣ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ፣ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ስለሚተሙ ነው ይህ መባሉ።
በተለይ መስከረም 17 ቀን ለሚከበረው የመስቀል በዓል የጉራጌ ብሔረሰብ በሚኖርባቸው የክልሉ ዞኖች ልዩ የበዓል ዝግጅት ይደረጋል። ማህበረሰቡ መስቀልን በዋዜማው እንዲሁም በእለቱ ብቻ አይደለም የሚያከብረው፡፡ ሰሞኑን ሁሉ በበዓላቱ ይደምቃሉ፡፡
በዓሉን ለማክበር ዓመቱን ሙሉ ነው ዝግጅት ይደረጋል። ይህም የማህበረሰቡን ብልሀት እንዲሁም ጥብቅ እሴት ያመለክታል። የጉራጌ ብሔረሰብ ለበዓል የሚያደርጋቸው ዝግጅቶች በባሕላዊ ሥነ ሥርዓቶች የታጀቡ ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር የእለት ተእለት ማህበራዊ ሕይወቱን የሚያከናውንባቸው ሀገር በቀል እውቀቶችና እሴቶችም ሞልተውታል። ለዛሬ ከእነዚህ እሴቶች መካከል ጥቂቱን ይዘን ቀርበናል፡፡
ያጋ ቃዋ – የጉራጌ ማህበረሰብ የቡና ሥነ ሥርዓት
የጉራጌ ማህበረሰብ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ከሚያቀራርቡላቸው ወይም ከሚያጠነክሩላቸው መልካም እሴቶች መካከል ‹‹ያጋ ቃዋ›› የሚሉት የቡና አጠጣጥ ሥነ ሥርዓት አንዱ ስለመሆኑ ከጉራጌ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ የቡና አፈላል ሥርዓት በመስከረም ወር በተለይ በመስቀል በዓል ወቅት ደምቆ ይታያል፤ በልዩ ሁኔታ ይካሄዳል።
መረጃው እንዳመለከተው፤ የጉራጌ ማህበረሰብ ካለበት ቀዬ አቅራቢያ ከሚገኙ ጎረቤቶቹ ከሶስት እስከ ስድስት አባላት በመሆን ቃዋ (ቡና) ይጠጣል። የቡና አፈላል ሂደቱ የሚከናወነው ተራ በተራ ነው፡ ፡ ዛሬ በአንዱ አባ ወራ ቤት ከተፈላ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተራውን ጠብቆ በሌላኛው አባወራ ቤት ይፈላል፡፡ ይህ ዓይነቱ የቡና አጠጣጥ ሥነ ሥርዓት ያጋ ቃዋ በመባል ይታወቃል፡፡ ጠዋት ላይ የሚካሄደው የቡና አጠጣጥ ሥነ ሥርዓት ያጋ ቃዋ ሲባል መሸት ሲል ተጠራርተው የሚጠጡት ቡና ደግም ዮጔር ቃዋ (ሸንጎ ቡና) ተብሎ እንደሚጠራ ያስረዳል፡፡
‹‹ያጋ ቃዋ›› እጅግ በጣም ተወዳጅ የሆነ የቡና አጠጣጥ ሥነ ሥርዓት ነው። ሰዎችን እርስ በርስ የሚገናኝና የሚያዋድድ፣ የሚያፋቅርና የሚያስተሳስብ ስለሆነ ጉራጌዎች ለያጋ ቃዋ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡት መረጃው ይጠቁማል፡፡ ባለተራዋ እማወራ ሌሊት ወፎች ከመንጫጫታቸው በፊት አስቀድማ በመነሳት ‹‹ቦሄ ያትየደርሄ ጌታ ቦሄ አወሬ›› (ሰላም ያሳደርከኝ አምላክ ሰላም አውለኝ) በማለት ለአምላኳ ምስጋና ካቀረበች በኋላ ተጣጥባ ቡና የማፍላት ዝግጅቷን እንደምትጀምር አመልክቶ፣ ሥርዓቱ በደማቅ ማህበራዊ ትስስር እንደሚቀጥል ጠቁሟል።
ጀፎር- የብሔረሰቡ የመንገድ ምህንድስና ጥበብ
መረጃው እንዳብራራው፤ ብሔረሰቡ የራሱ የሆነ የመንገድ ምህንድስና ጥበብም አለው፡፡ ከጉራጌ ማህበረሰብ እሴቶችና ሀገር በቀል እውቀቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ይህ የምህንድስና ጥበብ ‹‹ጀፎር›› በመባል ይታወቃል፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለዚህ ሀገር በቀል እውቀት አንስተው በኢትዮጵያ የሚገነቡ መንገዶች ከጉራጌ ማህበረሰብ ሀገር በቀል እውቀት ብዙ ሊጋሩ እንደሚገባቸው መናገራቸው ይታወሳል።
የመንደር አመሰራረቱና ‹‹ጀፎር›› የተሰኘው የባሕላዊ የአውራ መንገድ ቅየሳ ወይም የምህንድስና ጥበብ አንዱ የብሔረሰቡ ሀገር በቀል እውቀት መሆኑን መረጃው ይጠቁማል። “ጀፎር” ማለት የጉራጌኛ ቃል ሲሆን አውራ መንገድ ማለት ነው፡፡ ታዲያ ይህ የ”ጀፎር” ፍልስፍና በጉራጌዎች መንደር የተጀመረው ገና ሀገራችን ባለ አራት እግር የሞተር ተሽከርካሪዎች ሳይገቡና የመኪና ስሙ እንኳን በማይታወቅበት ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት እንደነበረ የጉራጌ አባቶች እንደሚያስረዱ መምሪያው ይጠቁማል።
የጀፎር የጎኑ ስፋት ከ60-100 ሜትር እንደሚወስድ የሚገለጽ ሲሆን፣ ርዝመቱ ግን አውራ መንገድ (ጀፎር) በሚያቋርጥባቸው አቅጣጫዎች ወንዝ፣ ደንና ትልልቅ ሸለቆዎች እስካላጋጠመው ድረስ ቅያሱ ይቀጥላል፡፡ የመንገዱ ስፋት የሚለካውም በባሕሉ መሠረት በተመረጡ አባቶች ወይም የመሬት ልኬት ዳኞች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ጀፎር በሁለት መንደሮች ትይዩ በመካከላቸው አቋርጦ የሚያልፍና አረንጓዴ ሣር የለበሰ ውብና ጽዱ ባሕላዊ አውራ መንገድ ነው።
በመስከረም ወቅት ልዩ የበዓል ድባብ በዚህ አውራ ጎዳና (ጀፎር) ላይ ይስተዋላል። ማህበረሰቡ በእነዚህ አረንጓዴና ፅዱ ጎዳናዎች ላይ በባሕላዊ አልባሳት ደምቀው ይታያሉ። ሕፃናት ይቦርቃሉ፤ የቤት እንስሳት ለምለም ሣር እየተመገቡ በዓሉ በድምቀት ያልፋል።
ጡር (ባሕላዊ ሽምግልና ሥርዓት)
የጉራጌ ማህበረሰብ በበዓላት ወቅት ብቻ አይደለም አብሮ የሚበላው፤ የሚጠጣው። የደስታ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይም ይተባበራል። ከዚህ ውስጥ በነዋሪዎች መካከል በሚነሳ አለመግባባት፣ ዘመድ ከዘመድ፣ ጎረቤት ከጎረቤት ቢቀያየም እና ፀብ ቢፈጠር አለመግባባቱን የሚፈታበት የራሱ ባሕላዊ ሥርዓት አለው። ይህ ሥርዓት ‹‹ጡር›› ይባላል።
ጉራጌ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ባሕላዊ ሸንጎ ያስቀመጣቸውን ማህበራዊ ሥርዓቶችና ድንጋጌዎችን ጠብቆ ከሁሉም ጋር በሰላም፣ በመቻቻልና በፍቅር ይኖራል፤ ይህን እንዲያደርግ ካስቻሉት ባሕላዊና መንፈሳዊ እሴቶች አንዱ ጡር መሆኑንም መረጃው ያመለክታል፡፡
በጉራጌ ታሪክ ጡር በሁለት መንገድ እንደሚገባ ይታወቃል፡፡ አንዱ መንገድ ሰዎች በብዙ በደል በብዙ መገፋትና ስቃይ ታግሰው አምላኬ ለትውልዴ ለዛሬ የተሻለ ቀን ያመጣል፣ ስለዚህ በእኔ ላይ የሚፈፀመው ግፍ አንድ ቀን ያቆማል ብለው ተስፋ በማድረግ የሚያገኙት መልካም ነገር ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ትዕግስት ተበዳዩ ለበዳዩ ሁልጊዜ በአምላኩ ፊት ቆሞ ‹‹ኤበርየ ጡር የህርብኸ፣ ጡራኸ ይያ ሸመነ የግባ›› በአማርኛው ‹‹እገሌ ጡር ይሁንብህ፤ ጡርህ እኔ ቤት ይግባ›› በማለት ከአንደበቱ ቃል አውጥቶ ይናገራል፡፡
እግዚአብሔር አምላክም የምስኪኖች ወዳጅ ነው፤ የችግረኞችን ጩኸት ከመስማት ዝም ያለበት ጊዜ የለም ሲሉ አባቶች እንደሚናገሩ መረጃው ይገልጻል፡፡ በዚህ ሁኔታ በእግዚአብሔር ጊዜ የበዳዩ ቤት ጡር ወደ ተበዳዩ ቤት እንደሚዞር የባሕላዊ ሸንጎ አካላት ይገልጻሉ፡፡ ይህንን እውነታ በምሳሌ ሲያስረዱ አንዳንድ ጊዜ አንድ አያት ከወለዳቸው ቤተሰቦች መሀል እንኳ ባላቸው ሀብትና የልጅ ብዛት ትልቅ ልዩነት ይከሰታል፡፡
የቀደሙት የፖለቲካ ሥርዓቶች ሴቶችን ከንብረትም ሆነ ከመሬት ባለቤትነት ያገሉ የነበረና ባሕሉም በራሱ ለወንዶች ያደላ የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ወንድ ልጆች የወለደ አባት ወንድ ሳይወልድ የቀረን የወንድሞቹን ሴት ልጆች በመግፋት መሬቱን ለራሱ በመከለል በመጨረሻም ለራሱ ልጆች ያከፋፍላል እንበል፡፡ ይህ ዓይነቱ መሬት በባሕሉ የፈነጠበያር አፈር ይባላል፡፡
ሴቶች ልጆቹም በኃይል መሬታቸውን ሲቀሙ ማስጣል ስለማይችሉ መስማት ለሚችለው አምላክ አባታችንና አጎታችን ከአንድ እናትና አባት የተገኙ ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ፤ ዛሬ ግን አባታችን ወንድ ባለመውለዱ የተነሳ እኛን ሴቶች ልጆቹን ገፍቶ መሬታችንን ወሰደ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ሆይ አንተ ዓይን አለህና ይህን በደሉን እይበት፤ ጡር ይሁንበት፤ በእኛ ላይ እንደሆነብን በተራ በእርሱም ቤት እንዲሁ ይሁንበት፤ እኛም ዛሬ በተገፋንበትና በተበደልንበት ለልጆቻችንና ለዘራችን ጡር ይግባልን ይላሉ፡፡ ማንም የዘራውን ማጨዱ አይቀርምና በዳይ አጎት የእጁን እንደሚያገኝ ሽማግሌዎች ያመለክታሉ፡፡
ሁለተኛው ጡር የሚወጣበት ሁኔታ ደግሞ አንድ ሰው አባት፣ አያት፣ ቅድመ አያት ወዘተ ያቆዩለትን ጡር እርሱ ስልጣኑን ወይም ሀብቱን ያለ አግባብ ተጠቅሞ በሰዎች ላይ ግፍ በመፈፀምና የሰዎችን መብት በመግፈፍ በሚፈፅመው በደል የተነሳ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ቤቱ የቆየውን ጡር ገፍቶ ሲያስወጣው ሲሆን፣ ይህም በጉራግኛ ‹‹ጡር ተቤተህኖ ኦነሞ ወጣም›› (ጡር ከቤታቸው ጮሆ ወጣ) ይባላል ሲል መረጃው ያብራራል፡፡
ጉራጌ አንዱ ተበዳይ ጊዜ በሰጠው ሰው ወይም ጉልበተኛ ሲበደል ሲያይ ለተበዳዩ ‹‹ጡር የህርኸ›› ‹‹ጡር ይግባልህ›› እንደሚለው መረጃው አመልክቶ፣ ለበዳዩ ደግሞ ‹‹ጡር የህርብኸ›› ማለትም፡ – እግዚአብሔር የሰጠህን መልካም ነገርህና ጸጋህን ካንተ ላይ አንስቶ ይውሰድ እንደማለት ነው ሲል ያብራራል፡፡ ይህ ደግሞ ጉራጌን በሕይወት ጉዞው ነገሩ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጠና ሊሰወር እንደማይችል በመረዳት በፍርሃት፣ በቅንነትና በትዕግስት እንዲመላለስ አስችሎታል፡፡
ስለሆነም ባሕሉን ጠንቅቆ የሚያውቅ በየትኛውም ማዕዘን የሚኖር ጉራጌ ነፍስ ማጥፋትን፣ በሀሰት መመስከርን፣ ቤት ማቃጠልን፣ ግፍ መሥራትን፣ ድንበር ማለፍን፣ ክህደትን፣ የሰው ሀብት መንጠቅን እና ሌሎች ያልተገቡ ነገሮችን በእጅጉ ይጠየፋል፡፡ የብሔረሰቡ ባሕል እሴት የሆነው ‹‹ጡር›› ሰዎች ከክፉ እንዲርቁና መልካሙን እንዲያደርጉ ያደርጋቸዋል፡፡
እንደ መውጫ
የዝግጅት ክፍላችን ለዛሬው ሀገርኛ ዓምድ ከላይ ባነሳናቸው የጉራጌ ባሕላዊ እሴቶች ላይ ያተኮረ እንጂ ማህበረሰቡ በመስከረም ወቅት በሚያከብረው ተወዳጅና ተናፋቂ በሆነው የመስቀል በዓል ወቅት ተግባራዊ የሚያደርጋቸው ልዩ ልዩ ባሕላዊ ክንውኖችም አሉት። ከእነዚህ መካከል የአመጋገብ ሥርዓት አንዱ ሲሆን፤ በተለይ የእርድ ሥነ ሥርዓቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ይታወቃል። ከእንሰት፣ ከሥጋ፣ ከጎመን እንዲሁም ከተለያዩ ተዋጽኦዎች የሚዘጋጀው የክትፎ፣ ቆጮ አይቤ እና ልዩ ልዩ ምግቦች የመስከረም ድምቀቶች የኢትዮጵያውያን ተወዳጅ ምግቦች መሆናቸው ተመስክሮላቸዋል።
ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም