‹‹የእግር ኳስ ሥልጠና መንገዳችን መመርመር ይኖርበታል››  -አሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በቅርቡ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ቡድኑ ውጤት ለማጣቱ የሥልጠና መንገዶች፣ ከሜዳ ውጪ መጫወት፣ ከጉዳትና ከሌሎች ችግሮች ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ተፅዕኖ መፍጠራቸውን አሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ተናግረዋል፡፡ የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ቡድናቸው ከታንዛኒያ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች አስመልክተው ከትናንት በስቲያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያውን እና ሁለተኛውን የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎቹን አከናውኖ በአንዱም ግብ ማስቆጠርና ማሸነፍ ሳይችል መቅረቱ ይታወቃል፡፡ ቡድኑ ከታንዛኒያ ጋር ያለምንም ግብ ሲለያይ በዲሞክራቲክ ኮንጎ 2ለ0 ተሸንፏል፡፡ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫና በሌሎች የነጥብ ጨዋታዎች ማሸነፍ እየተሳነው መምጣቱ የሥልጠና መንገዶች፣ ከሜዳ ውጪ መጫወት፣ ከጉዳትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የተገናኙ ችግሮች ምክንያት መሆናቸውን አሠልጣኙ አስረድተዋል።

አሠልጣኙ ከታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የተደረገው የመጀመሪያው ጨዋታ ጥሩ ቢሆንም በዋልያዎቹ የአጥቂ ስፍራ ላይ ትልቅ ችግር መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ብዙ የመስመር እና የፊት አጥቂዎች ከጤና እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ቡድኑ ውስጥ አለመካተታቸውን አንስተዋል፡፡ በሁለተኛው ጨዋታ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በአፍሪካና በዓለም እግር ኳስ ደረጃ ከፍተኛና ተጫዋቾቻቸውም በትልቅ ደረጃ የሚጫወቱ በመሆኑ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመዋል ብለዋል፡፡ እንደ አሠልጣኙ ማብራሪያ፣ ቡድኑ የአጨራረስ ችግር ቢኖርበትም ተጭኖ ለመጫወትና ኳስ ለመቀማት የሚያደርገው ጥረት ጥሩ ነው፡፡ ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች በዓለም እግር ኳስ ደረጃ በ30 እና በ83 ደረጃዎች መብለጣቸው ትልቅ ልዩነት መኖሩን ማሳያ ነው፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ በስደት ጨዋታዎች ጎል ማግባት ያልቻለው ብዙ ዕድሎችን መጠቀም ሳይችል ቀርተው እንጂ ቡድኑ መጥፎ በመሆኑ አይደለም፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግና ብሔራዊ ቡድን ሁነኛ ዘጠኝ ቁጥር አጥቂ እንደሌለና የውጪ ሀገር ዜጎች ኮከብ ግብ አግቢ መሆናቸው የዚሁ ማሳያ መሆኑን አሠልጣኙ ጠቅሰዋል፡፡ የአጥቂ ችግሩን ለመፍታት የረጅም ጊዜ እቅድ በመያዝ ከስር መሠረቱ ሊሠራ ይገባል ያሉት አሠልጣኝ ገብረመድኅን፣ የሥልጠና መንገዱም መመርመርና ትክክለኛ መንገድ የሚከተልበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡ የእግር ኳስ ፕሮጀክቶች ላይ አብዛኛውን ጊዜ ኳስን ማንሸራሸር ላይ ብቻ የተመሠረተ ሥልጠና እንደሚሰጥ በመጠቆም፣ ፕሪሚየርሊጉ ላይ ብዙ ግቦች የማይቆጠሩትም በዚሁ ምክንያት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ወጣቶች ላይ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የመድረስና የማስቆጠር ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት ይኖርበታል፡፡›› ያሉት አሠልጣኙ፣ አጥቂ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የሚፈጠር እንዳልሆነና ከመጀመሪያውም ለቦታው የሚሆን ተፈጥሯዊ ክህሎት ይዞ መገኘት እንደሚኖርበት ጠቅሰዋል፡፡ አብዛኛዎቹን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆነው የሚያጠናቅቁ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ማብቃታቸውን የገለጹት አሠልጣኙ አጥቂ ለማብቃት ረጅም ጊዜ ተወስዶ የሚሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሁለቱም ጨዋታዎች የቡድኑ አቋም የወረደው ብሔራዊ ቡድኑ የተሰባሰበው ውድድር በማይካሄድበት ወቅት በመሆኑ ተጫዋቾች እረፍት ላይ መሆናቸው የአካል ብቃት፣ ክብደት መጨመር እና ከጉዳት ጋር የቅንጅት ሥራዎችን ለመሥራት ጊዜ እንደወሰደ ተናግረዋል። በአጭር ጊዜ የተጫዋቾቹን ብቃት በማስተካከል እና ተጭኖ ተጫውቶ አራት ነጥቦችን ለማሳካት አቅደው እንደነበር ገልፀዋል፡፡ ይሁንና ከሜዳ ውጪ እየተጫወቱ ውጤት ማምጣት አስቸጋሪ ነው የሚሉት አሠልጣኝ ገብረመድኅን፤ ለብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማነት ችግሮቹ ምን እና የት እንደሆኑ በዝርዝር ለማወቅ ብዙ ጥናቶች መደረግ እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል፡፡

በሜዳና ደጋፊዎች ፊት የመጫወት ዕድል አለመኖሩ እግር ኳሱን በብዙ መልኩ ጎድቶታል፡፡ በሚያውቁት አየር፣ በደጋፊ እና ከተፅዕኖ ነፃ ሆኖ የመጫወት ለውጤታማነት የሚያበቃ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ ይገባል። በሜዳ ማሸነፍ በብሔራዊ ደረጃ በሊጉና በሀገር ደረጃ የመነሳሳት ኃይል ስለሚፈጥር ብሔራዊ ቡድኑ እንዲያሸነፍ ለሜዳ ተጠቃሚነት ትኩረት መሰጠት ይኖርበታል፡፡

ለሀገር መሥራት የሚያስደስት ቢሆንም ውጤት ባለመሳካቱ በክለብ ሆነ ብሔራዊ ቡድን መሥራት ሰልችቶኛል በማለትም ተናግረዋል፡፡ አሠልጣኙ አክለው እንደገለፁትም፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾች አሁን የሚገኙበት አቋም ጥሩ ደረጃ ነው ማለት አይቻልም። ብሔራዊ ቡድኑ ከሚገጥሙት ሽንፈቶች ጎን ለጎን ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም ውጤታማ እንዳልሆነና ብዙ መሥራት እንዳለበት ያሳያል፡፡ ተጫዋቾች የአንድና ሁለት ጨዋታ ኮከቦች ብቻ በመሆናቸው በመገናኛ ብዙኃን ሊተቹና ሊመከሩ እንደሚገባ አሠልጣኝ ገብረመድን ጠቁመዋል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You