በዛሬ የጋዜጠኛው ቅኝታችን የአዲስ አበባ የዓድስ ዓመት ዋዜማ ድባብ ተዘዋውረን ልናስመለክታችሁ ወደድን። በዚህ ጊዜ አዲስ ትለያለች። ከእግረኛ መንገደኝነት ወደ ገበያነት የሚለወጡ የአዲስ አበባ ዋና ጎዳናዎች ሞቅ ደመቅ ብለው በአውዳመት ሙዚቃ የበዓል ድባብ ተላብሰዋል። መንገዱ ሁሉ አዲስ ነገር በዝቶበታል፣አካባቢው ሁሉ በበዓል ድባብ ታጥሯል።
አውዳመት በራሱ ልዩ ሽታ አለው። ግርግሩ የሚናፍቅ ትርምሱ የሚታወስ ድባቡ ከአይን የማይጠፋ ልዩ ነው። ደጆች ትክክል ተደርገው በተሰሩ ወጦች በሙያተኛ እጆች በተሰሩ ዳቦዎች ሽታ ይሞላሉ። ዋዜማው ልዩ ነው፤ ሕፃናት አዳዲስ ልብስ ለብሰው አዲስ የተባለው ቀን መምጣቱን ይጠባበቃሉ። መንገዱ ሁሉ በበዓል ሸማቾችን ሻጮች ውክቢያ ፋታ ያጣል። ይህ ድባብ በሚስተናገድበት ዋንኛ ቦታ ላይ ቆሜያለሁ።
ውስጤ መታደስን እየተመኘ አዲሱን ዓመት ለመቀበል የሚሯሯጡ መንገደኞችና መንገድ ላይ የሚነግዱ ነጋዴዎችን ሁኔታ መመልከት ጀመርኩ። አራት ኪሎ ዳግማዊ ሚኒሊክ መሰናዶ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት እገኛለሁ። ተላላፊው ሁሉ አሮጌውን ወደኋላው ጥሎ ላይመለስ ወደፊት በመጓዝ ላይ ያለ ይመስላል። ከትምህርት ቤቱ ፊት ለፊት በዓል በመጣ ቁጥር ገበያ ሚሆን ለወትሮው እግረኛውን ፍስስ አድርጎ ሳያጋፋ የሚያስተላልፍ ሰው ጎዳና ነው።
በስፍራው አዲስ ዓመት እንደመሆኑ ከወትሮው በተለየ ገበያዋ በዝቷል። መንገዶች እግረኞችን ከማመላለስ ወደ ገበያ ስፍራነት ተቀይረዋል። የአላፊ አግዳሚ መንገደኞች ሳይሆን የሸማችና ሻጩ ድምፅ ጎልቶ ይሰማባታል። ሽጥልኝ… ግዛኝ፣ቀንስልኝ..ትንሽ ጨምረህ ውሰድ ተግባቦትና መፋረስ ይሰማል። እዚያ ቦታ ላይ በርክቶ የሚገኛው አውዳመቱን የሚያደምቁ ቤትንና አካባቢን አዲስ የሚያደርጉ እራስን ግርማ ሞገስ የሚያጎናፅፉ አልባሳትና ቁሳቁሶች እንዲሁም የምግብ ዓይነቶች ናቸው።
ሰው ግን ተከራክሮ መግዛቱን አልተወም ሸማቹ ክርክሩን ከፍ ማድረጉ እንጂ መግዛት መሸጡ ዛሬም አልቆመም። ገበያው ደርቶ ቀጥሏል። አውዳመት በመጣ ቁጥር ጥሎብን ደጋሽ፤መላሽ እንሆን የለ። እዚህ ቦታ ላይ አስቦበት ለሸመታ የመጣ ብዙም ሳይጨነቅ ቀድሞ ያሰበውን ወስኖ ገዝቶ ይሄዳል።
ድንገት ሲተላለፍ ባየው ልቡ የማለል ወይ ሊገዛ አልያም ደግሞ እንዲሁ “ዋጋው ማወቁ በጎም አይል” ብሎ ጠጋ ብሎ ይጠይቃል። ኪሱ ካለ ገባ ብሎ አውጥቶ “እንደው ይሞላልኝ” ይሆን እያለ ከራሱ ጋር ሙግት ይገጥማል። ካለለት ያላሰበውን ገዝቶ ይሄዳል፤ካልሆነልት ሻጩን ሲከራከር ያረፍዳል። “እባክህ ቀንስልኝ” እያለ ይሟገታል።
ቦታው ላይ የምግብ ቅመማ ቅመሞች፣ የባህል አልባሳት፣ የቆዳ ውጤቶች ጫማ፣ ቦርሳ፣ ቀበቶ፣ማር፣ቡና፣የአልጋ ልብስና ትራስ ጨርቅ፣ባህላዊ ዕቃዎችና ልዩ ልዩ ለአውዳመት ስጦታ የሚሆኑ የዕጅ ሥራዎች በተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ድንኳን ተሠርቶ መደብ ተበጅቶና በዓይነት በዓይነት ተበጅቶ ይገኛል። ሸማቹ ቀረብ እያለ ይጠይቃል፤ ሻጩ ያዋጣኛል ባለው እንካችሁ ይላል።
ሰላም አየለ ትባላለች። እዚሁ ቦታ ላይ ጫማ ስትጠይቅ አገኘኋት ጠጋ ብዬ አወራት ጀመር። በፈገግታ ምለሻ ትሰጠኝ ጀመር። ስለገበያው አጠቃላይ ሁኔታ ስጠይቃት። ኑሮ ተወዷልና ይህ ነው ማለት ይከብዳል። ብላ ጀመረች። የዕቃ ዋጋ መወደደ የምግብ ፍጆታ ዕቃዎች መናር አውዳመቱ ላይ ትንሽ ከባድ ቢያደርገውም ኢትጵያዊያን ተሟሙቶ ደጋሽ ነን አንታማም። በማለት ሃሳቧን አጋራችኝ። እሷም የአቅሟን ለመሸመት እዚያ ቦታ ላይ መገኘቷና ከሌላ ጊዜ አንፃር ግን የምትገዛቸው አልባሳትና መገልገያ እቃዎች ላይ እንደተቆጠበች ዘረዘረችልኝ። ኑሮው ያስክነው አዲሱ ዓመት ብስራትና በረከት ይዞ ይምጣልን ብዬ አመስግኜ ተለያኋት።
ወጣት ግርማ መድን ነጋዴ ነው። አውዳመት ምክንያት በማድረግ እዚሁ ቦታ ላይ ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር በመሆን የቆዳ ውጤቶችን ሲሸጥ አግኝቼ አወራሁት። ገበያ እንዴት ነው? የሚል ነበር የእኔ መግቢያ ጥያቄዬ። ከወትሮ ጋር ቢራራቅም ደህና ነው ተመስጌን ነበር የእሱ ምላሽ። የተጠቃሚዎች ስሞታና ዋጋ ጭማሪ ጉዳይ አነሳሁለት። ምን እናድርግ ሲጨምሩ ጨመርን አለኝ። ነገር ግን የጭማሪው በጣም ጣራ መድረስ ተገቢ እንዳልሆነና ያልተመጣጠነ ግነት እንዳለ እሱም ያምናል።
ዞር ስል አንዲት እናት አገኘሁ። አልጋ ልብስ ለመግዛት ከሻጭ ጋር ይደራደራሉ። ቆሜ በገዢ አይን የተለያዩ ዓይነት የአልጋ ልብሶች እየጠየኩ የሁለቱን ምልልስ አደምጣለሁ። “ኧረ ልጄ ተይ ሺጪልኝ…ቤቴም አውዳመት ነው ይመርበት” እያሉ ደጋግመው ሻጯን ያግባባሉ” የምትሸጠውም የዋዛ አይደለችምና “እማማ ለማንም በዚህ ዋጋ አልሸጥኩም ለእርሶ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ሺ አራት ልሽጥሎ ያልኩት…በእውት ከዚያ አያዋጣም። ” አለቻቸው ትተው ሄዱ በአይን ሸኘኋቸውና ሌሎች እቃዎች መጠያየቅ ጀመርኩ። ከሌላ ጊዜ አንፃር ለእኔም የከበደ ዋጋ ሆነብኝ። ተዘዋውሬ ባየሁት ሁሉ ዘንድሮና ገበያው ከሌላ ጊዜ አንፃር ማነፃፀር ውስጥ ገባሁ።
እንደድሮ ውስን ብር ይዞ ወጥቶ የፈለጉትን መግዛት በርክት ባለ ብር ያልፈለጉትን ይዞ ወደ መግባት ተሸጋግሯል። ዘንድሮ እንደወትሮው አይደለም። ያስፈለገህን ያህል ሳይሆን ግድ የሚልህን ገዝተህ ያማረህን ሁሉ ሳይሆን እንዳይጎድል ምትፈልገውን ብቻ ገዝተህ ዓውዳመቱን ለማሳለፍ የምትገደድበት ወቅት ነው። አውዳመት ሲሆን ነጋዴም ይከፋል። በኑሮውድነት የተማረረውን ወገኑን በዋጋ መናር የተከዘወን ዘመዱን ከማሰብ ይልቅ አጋጣሚውን ተጠቅሜ ልክበር ይላል።
በእርግጥ የእኛም አጉል ልማድ ለችግራችን መባባስ ዋንኛ ምክንያት ነው። በዕቅድና በተጠና መልክ የሚያስፈልገን ምን እንደሆነ ጠንቅቆ አለማወቅ፣ ለበዓሉ በአቅም ምን አድርጌ ላሳልፍ ማለትን አለመልመድና፣አቅም ያገናዘበ የበዓል አከባበር ባህል የለንም። በዓሉን እንካለፈ በኋላ ይዞ የሚመጣብን ዕዳን ፈፅሞ አናስብም። የቀኑ ደምቆ ምንሽንሽ ብሎ መዋል እንጂ አድሮ የሚያመጣውን ጉድለት አንለካም።
ገበያ ገብተን ጠይቀን ባላሰብነው እንገዛለን ገቢያችን ግን የተወሰናና የምናውቀው በመሆኑ የጨመረው በገቢያችን ልክ መጥነን ካላጣጣምነው፤ በዓሉን ስናስብ ዓውዳመቱ ስንቀርብ በዓልነቱ ጣዕም ያሳጣብናል። በዓል ሲመጣ ከመደሰት ይልቅ ወደ ትካዜ ይለወጣል። ስለዚህ ነጋዴውም ለወገኑ አስቦ አገበስብሼ ልብላን ቢተው ሸማቹም ባቅሙና በመጠን ባለው ልክ ቢሸማምት ገበያችንም አዲሱ ዓመታችን ያማረና የደመቀ ደስታችንም የዘለቀ ይሆናል። መልካም አዲስ ዓመት ተመኘሁ፤ ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም