(ክፍል አንድ)
በዚህ አምዳችን ላይ በጉዞዋችን የገጠመን ስናሳያችሁ፤ የታዘብነው ስናስቃኛችሁ ጥሩውን ስናወድስ የሚስተካከለውንና የሚታረመውን ስንጠቁም ቆይተናል።ዛሬ በጋዜጠኛው ቅኝት አምዳችን ወደ ደቡብ ምዕራብ የአገራችን ክፍል ያስጉዘናል።መነሻችን ሸገር አዲስ አበባ ሲሆን መዳረሻችን ደግሞ ጉራጌ ዞን ጌቶ ወረዳ ስላሴ ቀበሌ ነው።
ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ከስራ ገብቼ ልብሴን እንደቀያየርኩ ሴልኬ ባትሪው ዘግቶ ነበረና ከቻርጀር ጋር አገናኘሁት። እራት በልቼ የበላሁት እስኪንሸረሸር ወደ አልጋዬ ከመሄዴ በፊት ስልኬን ከሰካሁት ቻርጅ ላይ ነቅዬ ከፈትኩት። የበዙ መልዕክቶችና ያመለጡኝ ጥሪዎች ተካታትለው በመልዕክት መልክ ገቡ።
ቀዳሚ የሆነውን መልዕክት ስከፍት ጥሩ ያልሆነ ዜና ሰማሁ። አንድ የቅርብ ዘመዴ ሞት ዜና ነበር። መልዕክት የላከልኝ ሰው ጋር ደወልኩ። ወደ ለቅሶው ስፍራ ለመሄድ በመሰናዳት ላይ እንደሆኑና በተደጋጋሚ ስልኬ ቢሞክርም እንቢ እንዳለው ለመሄድ ካሰብኩ እንድዘጋጅ ነገረኝ። መነሻ ሰዓቱ ተነጋገርን። መሄድ ግድ ይለኝ ነበረና ሳላስበው ድንገት የሰማሁትን ለቅሶ ለማስተዛዘን መሰናዳት ጀመርኩ።
ሌሊት 11 ሰዓት ስልኬ ቀሰቀሰኝ። ቤቴ በር ላይ መድረሳቸውና እንድወጣ ያ ማታ ላይ ደውዬለት ያወራሁት ሰው ነገረኝ። ተጣድፌ ወጣሁ። አንድ ሚኒባስ መኪና በር ከፍተውልኝ ገባሁ። መኪናው ውስጥ ያሉት ሰዎች ሁሉ ፊት ላይ ሀዘን አጥልቷል።ሁነቱ ለሰላምታ የማይመች ነበርና “እንዴት አደራችሁ” ማለት ከበደኝ። በዝምታ ገብቼ ወንበር በአይኔ መፈለግ ጀመርኩ።የመኪናው ወንበር ግጥም ብሎ ሞልቷል።
በአይኔ ወንበር አልኩት ረዳቱን እሱም ተደራቢ 3ኛ ሰው ሆኜ መጓዝ ግድ እንደሚለኝ ነገረኝ።በሁለት ሰዎች መቀመጫ ሶስት ሆኖ መጓዝ አጭር ርቀት ቢሆን ግድ የለም መቶ ኪሎ ሜትሮች ልንሄድ አልኩ በልቤ ወዲያው ግን የምሄደው ለቅሶ መሆኑንና ብዙም ድሎት መጠበቅ እንደሌለብኝ ለራሴው ነገርኩት። ወግ ያለው ሰላምታ ሳንለዋወጥ ልክ እንደተኳረፈ ሰው ጉዞ ቀጠልን። መኪናው ውስጥ ካሉት ተሳፋሪዎች የማላውቀው ከረዳትና ሹፌሩ ውጪ ሁለት ሰው ብቻ ነው። አብዛኛው ቤተሰብና እርስ በርሱ የሚተዋወቅ ነው።
መኪናው እንደ ጉድ ይከንፋል። ጥሎብኝ ሞገደኛ ሹፌር አይመቸኝም። መናገር ግን አልፈለኩም፤ዝምታን መረጥኩ። በመኪናው የጎን መስታውት የንጋት ፀሀይ ብቅ ስትል ከምስራቅ አቅጣጫ አየኋት። ከመንገዱ ግራና ቀኝ ለአዝርእት ተብሎ የታረሰ ሰፊ መስክ ይታያል። አንዳንዱ እስከ አድማስ ጥግ ድረስ በነፃነት የተዘረጋ ጥቁር ምንጣፍ ይመስላል። አሁን ላይ ለእረሻ የተዘጋጀው ይህ ሰፊና ለጥ ያለ ሜዳ መስከርም እና ከመስከረም በኋላ አረንጓዴ ንጣፍ ደርቦ ሲታይ እንዴት ያማልል ይሆን።
የመኪናው ፍጥነትና የሹፌሩ መቅበጥበጥ ላለማየት የጀመርኩት የአካባቢው መልካም ምድር የማድነቅ ጅማሮዬ እዚያው ውስጥ ስምጥ ብዬ ተፈጥሮን እንዳስብ አደረገኝ። ከቆይታ በኋላ ሞባይሌን አውጥቼ ሰዓት ተመለከትኩ፤ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ያመለክታል። ቀና ስል ወሊሶ ከተማ መግቢያ ላይ መሆናችንን አወኩ። ጠዋት በጭለማ የተመልኳቸው አብረውኝ የሚጓዙ ሰዎች በድጋሚ ዞሬ ወደ ኋላ ሳይ መኪናው መጫን ከሚገባው ሰው በላይ መጫኑን አረጋገጥኩ። አምላኬ ይሄን ሁሉ ሰው ይዞ ነው የሚከንፈው። ሰው በሰው ላይ ደራርቦ ሲጭን እንዴት ትራፊክ አልፈራም? ለነገሩ ለቅሶ ነው ብለው ትረፊክ ፖሊሶችን ይለምናሉ። ለቅሶ ብሎ ትራፊክ ፖሊሶችን ማለፍ እንኳን እንደዚህ የእውነት ለቅሶ በሚኬድበት ጉዞ ይቅርና በሌላም ጉዞ ወቅት ረዳትና ሹፌሮች ትራፊክ ፖሊሶች የሚያታልሉበት ዘዴ ነው።
ወሊሶ ጠዋት ላይ ሞቅ ደመቅ ብላ እግዶችዋን በማስተናገድ ላይ ናት። የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን መናገሻ የሆነችው ወሊሶ ከአዲስ አበባ በስተ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 114 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ከተማዋ በፈጣን እድገት ላይ ትገኛለች። በከተማዋ አልፎ አልፎ ይታዩ የነበሩ ህንፃዎች አሁን በረድፍ ተሰልፈውና ከተማዋን አስጊጠው በዝተው ይታያሉ። ብዙዎች የሚተላለፉባት የንግድ ማዕከል መሆንዋ ድግሞ ለእድገትዋ ዋንኛ ምክንያት ነው። ከአዲስ አበባ ወልቂጤ፣ አጋሮና ጅማ የመሳሰሉና በዚያ መስመር የሚገኙ ከተሞች ለመድረስ ወሊሶን ማየት ግድ ይላል።
በፍልውሀ ምንጭነትዋ ብዙዎች የሚያውቋት ወሊሶ ባላት ተፈጥሯዊ መስህብ ቱሪስቶች ደጋግመው የሚጎበኝዋት ከተማ ነች። በከተማው ታሪካዊው የደጃዝመች ገረሱ ዱኪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ አምቦ ዩኒቨርሲቲ(ሶሻል ሳይንስ ካምፓስ)፣የኦሮሚያ ውሀ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት፣ የግል ኮሌጆች፣ትምህርት ቤቶችና ልዩ ልዩ ተቋማት ይገኛሉ።እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2009 በወጣ አንድ ጥናት የከተማዋ ህዝብ ብዛት ከ65 ሺ በላይ ይገመታል።
ወሊሶን ወደኋላ ትተን ምቹ በሆነው የአስፓልት መንገድ ወደፊት መጓዛችን ቀጥሏል። በአስፋልት መንገድ ለሁለት የተከፈለው ሰፋፊ የእርሻ መስክ ሄደው የሚጨርሱት አይመስልም። ይዞን የሚሮጠው ክልፍልፍ ሹፌር ከወሊሶ በ55 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኘው ወልቂጤ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ለመድረስ ተቃረብን። የከተማው መግቢያ ላይ ወደዞኑ እንኳን በደህና መጣችሁ የሚል ፅሁፍ ስናይ ለከተማው መቃረባችን አወቅን።
ወልቂጤ ላይ ጠዋቱ በሰዎች እንቅስቃሴ ጠዋት መምሰሉን ትቶ እኩለ ቀን አስመስሎታል። ሱቆች ተከፍተው ሆቴሎች ሞቀው እንግዶቻቸውን በመጠባባቅ ላይ ናቸው።የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ወልቂጤ እንደ አውፓውያን አቆጠያጠር በ2007 በተደረገ አንድ ጥናት የከተማዋ ነዋሪዎች ብዛት ከ29 ሺ በላይ መሆኑ ያመለክታል።
በዋናው የአስፋልት መንገድ ዳርና ዳር አንገታቸው አስግገው ብቅ ብቅ በማለት ላይ ያሉት ፎቆች የከተማዋ ዕድገት ማሳያ ናቸው። የንግድ ማዕከል የሆነችው ወልቂጤ በዚያ መስመር የሚመላለሱ መንገደኞች ለምሳ አርፈው ጊዜአዊ ቆይታ የሚያደርጉባትና ሞቅ ያለች ከተማ ነች።ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግባት፤ ብዙዎች ለስራ የሚመርጧት ከተማ ነች።
ሳር ቅጠሉ ሁሉ ሰራተኛ በሚመስልባት በዚህች ታዳጊ ከተማ አውራ መንገዶች ላይ የተለያዩ ሸቀጦች ዘርግተው የሚነግዱ በእጃቸውና በጀርባቸው አዝለው ለተጠቃሚ ለመሸጥ የሚራወጡ ወጣቶች በብዛት ይታያሉ። ቡና፣ ስኳር፣ ለስላሳ፣ ውሀ፣ ሙዝ ብርቱኳንና ፍራፍሬዎችና አትክልቶች በጎዳናው ላይ የሚቸበቸቡ፤በከተማዋ ወጣቶ የሚቀርቡ ነገሮች ናቸው።ምን አልባትም በጎዳና ላይ የሚታየው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ለህገ ወጥ ንግድ ዋንኛ ማሳያም ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል።
ከተማዋ ላይ ቁርስ ነገር ቀማምሰን ወደ መኪናችን ተመልሰን ጉዞ ወደመድረሻን ማድረግ ጀመርን። ከተማው ጨርሰን ቀጥ ብሎ ወደ ደቡብ አቅጣጫ የሚያስጉዘውን መንገድ ትተን በግራ በኩል ታጥፈን ቁልቁለት ወረድን። ቀድመን ያየናቸው ሰፊና ለጥ ያሉ ሜዳዎች በሰንሰለታማና አረንጓዴ በለበሱ ተራሮች ተተኩ። የጊቤን ወንዝ ተሻግረን በወልቂጤ ከተማ ጉብሬ ክፍለ ደረስን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ቁጥራቸው በዛ ያሉ የውሀ ፋብሪካዎች መንግስታዊና የግል ተቋማት ይገኙባታል ጉብሬ። ክፍለ ከተማዋ አዳዲስ ግንባታዎች በስፋት በዋናው መንገድ ግራና ቀኝ ሲካሄዱ ይስተዋላል። … ይቀጥላል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 29/2013