ፌኔት ኤልያስ
ለትጥቅ ትግል ጫካ የገባው አካል ሳይታሰብ የደርግ ዘመን እንዲያበቃ ማድረግ ቻለ ። ሕዝቡ በደርግ ዘመን ይፈፀሙ የነበሩ ግፎች አንገሽግሸውታልና መቋጫ ያገኛሉ በሚል ተስፋ አጨብጭቦ ኢህአዴግን ተቀበለ። ነገር ግን የታሰበው ቀርቶ ያልታሰበው ሆነ ። ፍትሕ ይሰፍናል እኩልነት ይረጋገጣል ተብሎ ቢገመትም ፍትሕና እኩልነት በአፈና እና በመድሎ ንፋስ እንደደመና ጉም በነው ጠፉ። ጫካ ውስጥ በተሳተፉ የጦር ሰዎች ቁጥጥር ስር የዋለችው አገር ፤ የደህንነት መስሪያ ቤቷም ሆነ የአገሪቱ ጦር አጠቃላይ ስልጣኑ በነዚሁ ሰዎች ቁጥጥር ሥር መዋሉ አደጋ ይዞ መጣ።
ላይ ላዩን ዴሞክራሲ እየተገነባ እንዳለ እንዲታሰብ የማስመሰል ተግባር ቢፈፀምም ፤ ውስጥ ውስጡን አፈናው ተጠናከረ። ተቃውሞ የሚያሰሙ ግለሰቦች በደህንነት ኃይሉ እየታፈኑ ደብዛቸው ይጠፋ ጀመር። እንደደርግ ፊት ለፊት ከመድፋት ይልቅ በድብቅ እያፈኑ ማሰቃየት ቀጠለ ። ሰላምና መረጋጋት ቢኖርም በነፃነት መናገር መዘዝ ማምጣቱን ቀጠለ ። እስር ቤት ይፈፀሙ የነበሩ የግፍ ጥጎች ሰዎችን በጨለማ ቤት ከማሰር፣ ዘቅዝቆ ከመግረፍና አካል እስከ መቁረጥ በሰዎች ላይ ይፈፀማሉ ተብለው የማይታሰቡ ድርጊቶችን እስከመፈፀም ተደረሰ ።
በዚህ የሥልጣን ዘመን የጸጥታ ኃይሎች በይፋ እርምጃ ወሰዱ ተብሎ ባይገለፅም በደህንነቱ እየታሰሩ ያለፍርድ ቤት ውሳኔና ያለተመልካች የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ ሄደ ። ዘመን ዘመንን እየተካ ዓመታት ተቆጠሩ ። የጊዜው መርዘም የጭካኔውን ጥግ አልቀነሰውም ። ነፃነት አፈር በላ። ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም ንጋት ላይ ግን ኢትዮጵያውያን አዲስ ዜና ሰሙ ። የሀገሪቱ መሪ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሞት በመገናኛ ብዙኃን ተገለፀ። የኢህአዴግ የደም ስር ተደርጎ የሚወሰደው ህወሓት አደጋ ላይ ወደቀ።
በዚህ ምክንያት በስልጣን ሽሚያ አገር አደጋ ላይ እንዳትወድቅ ቢሰጋም፤ በአቶ መለስ ዜናዊ ምትክ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣንን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱ ጋር ደርበው ይዘውት የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደ መሪነት መጡ ። ነገር ግን የሥልጣን ቆይታቸው ከፍተኛ እንቅፋት የተጋረጠበት
ከመሆኑም በተጨማሪ በአቶ መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን በተለያዩ እስር ቤቶች ይፈፀሙ የነበሩ ግፎች የቀጠሉበት ሁኔታም ነበረ ።
ቀስ በቀስ ኢትዮጵያ የተለየ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ገባች ። በዚህም በዚያም የተለያዩ ሕዝባዊ አመፆች መነሳት ጀመሩ ። እንደተለመደው ሕዝባዊ አመፆችን መቆጣጠር አልተቻለም ። መንግሥት ብቻ ሳይሆን አገርም አደጋ ውስጥ ትገባለች የሚል ስጋት ተፈጠረ ። የፖለቲካ ጥያቄና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታዩ ግጭቶች መቀጠላቸውን ተከትሎ በ2010 ታህሳስ ወር ላይ ለ17 ቀናት የኢህዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ አካሄደ ።
መሰረታዊ መፍትሔዎችን ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ የተጣለበት ስብሰባ፤ መጠናቀቁን ተከትሎ የተሰጠው መግለጫ በእርግጥም አገር በለውጥ ጎዳና ውስጥ እንድትራመድ መንገድ እየተከፈተ ነው የሚያስብል ሆኖ ተገኘ ። ነገር ግን በተለየ ሁኔታ የህውሓት የተወሰኑ ቡድኖች ዘንድ የሕዝቡን ፍላጎት ተረድቶ ለውጥ እንዲመጣ ከማገዝ ይልቅ ወጣ ገባ አመጡ። አንዳንዶችም ከውስጥም ሆነ ከውጭ ለውጡን ለማደናቀፍ ጥረት ማድረግ ጀመሩ ። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሳይጠበቅ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው የለውጡን መስመር ውል እንዲኖረው አስቻለ ።
ዶክተር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ስልጣን መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ልክ በዛሬዋ ዕለት ሲረከቡ፤ በብዙ ኢትዮጵያውያኖች ዘንድ ትልቅ ተስፋ ፈነጠቀ ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ በእስር የነበሩ ሰዎች ማስፈታት፣ የተዘጉ የህትመትና ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃንን መክፈት፣ የአገሪቷን ወሳኝ ቦታዎች ተቆጣጥረዋል የተባሉትን የደህንነትና የመከላከያ አመራሮች በሌሎች መተካት፣ ለ20 ዓመታት የተቋረጠውን የኢትዮጵያንና የኤርትራን ግንኙነት ክፍት በማድረግ ቀረቤታን መፍጠር የመሳሰሉትን ትልልቅ ፖለቲካዊ እርምጃዎች በመውሰድ አገር የማረጋጋት ስራቸውን ቀጠሉ ።
በመላው ዓለም የተበተነው የኢትዮጵያ ሰላምና ዕድገት የሚያሳስበው በሙሉ በተለይ ኢትዮጵያኖች በደስታ ተዋጡ። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት እንደታየው በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን የደስታ እንባን አነቡ ። ሆኖም ግን በተለያዩ አካባቢዎች ደግሞ አለመረጋጋቶች፣ መፈናቀልና ጥቃቶች መድረሳቸውን ቀጠሉ ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው መንግሥት በትዕግስት ጥፋቶች እንዳይቀ ጥሉ ለመከላከል ቢሰራም፤ በተቃራኒው አገሪቱን ለመበታተን የሚሰሩ ኃይሎች እና ባለፉት ሶስት ዓመታት ከተዘራው መልካም ነገር በላይ ባለፉት 27 ዓመታት የተዘራው መጥፎ አመለካከት በማየሉ እስከ አሁንም የሰዎች ህይወት እየተቀጠፈ ይገኛል ።
እርግጥ ነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የ3 ዓመታት ቆይታ በከፍተኛ ድህነት ከሚጠቀሱ አገሮች መካከል የሆነችው ኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ ወደ ዕድገት በሚያመራ መንገድ ላይ መጓዝ መጀመሯን አስመልክቶ ትልቅ ተስፋ እውን መሆኑን የሚያረጋግጡ ምልክቶች ታይተዋል ። ነገር ግን አሁንም ድረስ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል ።
ባለፉት ሶስት ዓመታት ካጋጠሙ ፈታኝ ነገሮች መካከል በህውሓት ቡድን የተፈፀመው መከላከያን የማጥቃት ተግባር (ምንም እንኳ ድርጊቱ የቡድኑን ውድቀት ቢያፋጥነውም) ትልቅ ጠባሳን ትቶ አልፏል። ያ ብቻ ሳይሆን አሁንም ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች የለውጡ ትልቅ ፈተና ሆነው በመቀጠል ላይ ይገኛሉ ። ያንን ከባድ አደጋን ማለፍ እንደተቻለው ሁሉ ወደ ፊትም የሚካሄዱ ጥቃቶችን ቀድሞ ለመከላከል መንግስት ወይንም አንድ ሰው ብቻውን የሚያመጣው መፍትሄ የለም ።
በእርግጥ መንግስት ውስጡ ያለውን አመራር በመፈተሽ በድርጊቱ ውስጥ የሚሳተፉት ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት ። አጠቃላይ ሕዝቡ ደግሞ ሕግ እንዲከበር በሕግ እና በሕግ መመራትን በሚመለከት ሃሳቡን ከማስረፅ ጀምሮ ተግባር ላይ እንዲውል ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ ችግሩን በመንግሥት ብቻ ማለፍ አዳጋች ነው።
በተለይ ሃሰተኛ መረጃን በማራገብ ከመተባበር ይልቅ ቢቻል፤ እውነታውን አረጋግጦ መግለጥ ካልሆነም የነገር ጫፍ ይዞ አብሮ ከማውራትና ከማስወራት መታቀብ ይበጃል ። በተረፈ ትልቁ መፍትሔ ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ ስልጣን ላይ የሚወጣው መንግሥት የሚነሱ ጥያቄዎችን መላ ማበጀት ሲችልም ጭምር ነው የሚል እምነት እንዳለኝ ሳልጠቁም አላልፍም። ሰላም !
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2013