(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
“ሀገር ማለት…” ብሎ ንግግርን መጀመር እንደ ቀዳሚ ዘመናት ከአኩሪነቱ ይልቅ አሸማቃቂ ደረጃ ላይ ለመድረስ ማኮብኮቡ የሀገራዊ ግራ መጋባታችንን ከፍታ በግልጽነት የሚያመለክት ተቀዳሚ ማስረጃ ነው ።“ሀገር” ብሎ ንግግርን ለመጀመር ገና አፍ ሲሟሽ “የቷ ሀገር?” የሚሉ በርካታ የቅዠት ድምጾች ከወዲያ ወዲህ እየተወናጨፉ ግራ ሲያጋቡን የተመለከትንባቸው የግል ገጠመኞችና አጋጣሚዎች በርካታ ሳይሆኑ እንደማይቀሩ እገምታለሁ ፡፡
“ሀገርማ…” ብሎ ሃሳብን ለማብራራትና ለማስረዳት ሲሞከርም “ለእኔ ያልሆነች ሀገር…” ወይንም “እከሌ ለተባለው ቡድንና ብሔር ያልሆነች አገር…” እየተባለ በደመ ሙቆችና ግራ ገቦች የእብሪት ንግግር አየሩ ይበከላል ።ይህን መሰሉ መርዝ የተቀላቀለበትና “የጎጣቸው ማንነት አብሾ” አናታቸው ላይ ወጥቶ ያሰከራቸው ግለሰቦች የትዕቢት ምላሽ ውይይቱን ወደ ጠብና ያልተገባ ጭቅጭቅ ማምራቱ ብቻም ሳይሆን ለከፋ ጉዳትም ሲዳርግ መመልከት ብርቃችንም ድንቃችንም አልሆነም ፡፡
እጅግ ክፉ የሚባሉ ሥርዓተ መንግሥታትን ዓለማችንም ሆነች ሀገራችን በገፍ ሲያስተናግዱ መኖራቸው ለማንም ሰው እንግዳ ታሪክ ተደርጎ የሚጠቀስ አይደለም ።ስለ እንዴታው የቅርብና የሩቅ ማስረጃዎችን እየጠቃቀሱ ማስረዳቱ እጅግም ባይከብድም ወደ ዝርዝር ታሪኩ መዝለቅ የንባብ ጊዜን ከማባከን ውጭ አዲስ እውቀት አያስጨብጥም ።የበርካቶቹ የነባር ታሪኮች ገመና እውነታ ይህን መምሰሉ እንደተጠበቀ ሆኖ የትናንቱ የሀገሬ ሟች ሥርዓት ተክሎብን ያለፈውን ያህል የከፉ ስለመሆናቸው ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም ፡፡
የፖለቲካ ሥርዓቱ (ለሃያ ዓመታት ያህል ጫካ ውስጥ ሲጎነጎን የኖረው ለጊዜው ቁጥር ውስጥ ባይገባም) እንደምን በሃያ ሰባት ዓመታት የአገዛዝ ዘመን ውስጥ የሀገሬን ክብር ገሎ ከመቃብር አፋፍ ለማድረስ ተቻለ? እንደምንስ የዜጎችን የሰብዓዊነት ክብር አድቅቆና ፈጭቶ በእንቶ ፈንቶ ርዕዮተ ዓለም ፍልስፍና ሊያደናቁረን ቻለ? የሀገሪቱን ሀብት ሙጥጥ አድርጎ ለመዝረፍና ለማዘረፍ ኅሊናን ብቻ መግደል በቂና ከበቂ በላይ ሆኖ እያለ መንበረ ስልጣኑን የተቆጣጠረው ቡድን ጥቂት ግለሰቦች በቀፎ ሰብዕናቸው ወደ አውሬነት ተለውጠው የዋሁን ሕዝባችንን ወደ መራርነትና ጭካኔ በመምራት እንደምን በመገዳደልና በመጠፋፋት ሊያሰክሩት እንደቻሉ መመርመሩና ማሰቡ በራሱ ሰብዕናን የሚፈታተን ክፉ ድርጊት ነው ።ይህን መሰሉ ክፉ የ“ፖለቲካ ነቀርሳ” ታሪክ ምን ተብሎ ለተከታዩ መፃኢ ትውልድ ተጽፎና ተተርኮ እንደሚተላለፍ ማሰቡም የዚያኑ ያህል ግራ ያጋባል።
ስለዚህ ስለ ሀገራችን የጋራ ቤትነት በድፍረትና በጽናት ለመናገር አንደበታችን መሸበቡ ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ራሱ የግራ መጋባታችን ምክንያት ሆኖብናል የምንለውም ስለዚሁ ነው።ክቡርና ንዑድ የሚባሉት የሕዝባችን የማንነትና የአብሮ መኖር ታሪኮች፣ የጋራ ባህሎቻችንና እሴቶቻችን እንዲደበዝዙ ሆን ተብሎ ሲሰራ ስለኖረ በቀላሉ ለመፈወስ ጊዜና ትዕግሥት ይጠይቃል ።
“ሀገር…” ብሎ ስለ ታላቋ ኢትዮጵያ ለመናገር “የአፍ ቁስል” የሆነብንም በዚሁ ምክንያት ነው ።የግራው ነገር ግራ ሆኖብንም የየዕለቱ ሀገራዊ ክስተታችን በረቂቅና ውስብስብ ችግሮች ጠፍሮ ስለተበተበን እውነቱን እንዳንናገር በአንደበታችን ምሥክርነት ብቻም ሳይሆን ኅሊናችንም ጭምር በግራ መጋባት ልጓም ተሸብቦ አንገት እንድንደፋ ግድ ብሎናል።ከዚህ የበለጠ የማንነት መኮስመንና ከዚህ የከፋ መዋረድ ከቶውንስ ምን አቻና ተወዳዳሪ ይኖረዋል?
የእውነታው ግዝፈት ይህን ይምሰል እንጂ “የእንቆቅልሽ/ህ?” – “ምን አውቅልሽ/ህ” የክርክራችን መቋጫ መልስ “ከሀገር ስጠኝ፣ ሀገር ስጭኝ” እውነታ ስለማይዘል “ዞሮ ዞሮ ከሀገር፤ ኖሮ ኖሮ ከአፈር” እንዲሉ በዚሁ ድፍረት ጀግነን ዛሬም እንደ አምና ካቻምና ስለ ታላቋ ኢትዮጵያና ስለ ምትክ አልባዋ “እናት ዓለም” ከመመስከር ውጭ ምንም አማራጭ የለንም።ክፉዎች እንደሚተነብዩት ሳይሆን በአንደበታችንም ሆነ በጽሑፋችን እውነቱን ከማሳየትም አንቦዝንም፣ አንሰንፍም፣ አንደነግጥም፣ አናመነታም።መደም ደሚያው ይኼ ነው፡፡
ስለዚህም “አገር ማለት…” እያልን እንቀጥል፤
የጂኦግራፊ ኮርሶቻችን ስለ ኢትዮጵያ የትነት የሚያስተምሩንን የኬክሮስና የኬንትሮስ ቀመር፣ ከምድር ሰቅ በታችም ይሁን በላይ የመገኘቷን ጥቁምታ፣ የምሥራቅ አፍሪካን ቀንድ የመጋራቷን እና ስለ ዳር ድንበራችን የቆዳ ስፋትና ጥበት የሚያወሳውን ሥነ ምድራዊ ሀተታ ለጊዜው እናቆይና ስለ ምንነቷና ሥሪቷ ከክፍል ትምህርትና ከንባብ እውቀታችን ሳይሆን ነፍሳችን የሚመሰክርልንን እውነታ እየጠቃቀስን ጥቂት እንቆዝም፡፡
የሀገሬ መልክዓ ምድር የተገነባው በገዘፉ ተራሮች፣ በአማላይ ሸለቆዎች፣ “ከገነት ምንጭ” በሚፈልቁ ወንዞች፣ እንደ ክብር ዘብ በተደረደሩ ተረተሮች፣ በጎፈሬያማ ደኖችና ጫካዎች፣ በፈረሶች መፈንጫ ሜዳዎች ወዘተ. ውበት መገለጫነት መሆኑን መተረኩም ኢትዮጵያን በመልዓት አይገልጻትም።እርግጥ ነው ሰው ነፍስና ሥጋ እንዳለው ሁሉ የተዘረዘሩት የተፈጥሮ ፀጋዎችም የሀገራችን “ዐፀደ ሥጋዎቿና እስትንፋሷ” መሆናቸው አይካድም።
“ተራሮች፤ ጉልበቶቿ፣ ወንዞቿ፤ ደም ሥሮቿና ደሟ፣ ሜዳዎቿ፤ ደረቶቿ፣ ኮረብታዎቿ፤ ያጋቱ ጡቶቿ ወዘተ.” እያለ እንደተረከው ደራሲ የሀገራችንን የአየር ንብረቶች፣ ተፈጥሯዊ የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውበቶቿንና ሀብቶቿን እየዘረዘሩ ቅኔ ማመሳጠሩም እንግዳ ባህላችን አይደለም።በተለይም የኪነ ጥበቡ ዘርፍ ሀገራችንን በማድነቅ ረገድ ሲጓዝ የከረመበት ጎዳና በውሃ መንገድነት ሊመሰል መቻሉ ስለዚሁ ነው ።ግሩምና ድንቅ ይሏል እንዲህ ነው ፡፡
ሀገር የተገነባቸው በቀደምት ዘመናቱ ጀግኖች አበውና ቆራጥ እማሁት የነፍስ ውርርድ ብቻም ሳይሆን በዚህ ትውልድም የደምና የአጥንት ክስካሽ ተለውሳ ጭምር ነው። እጅጋየሁ ሽባባው፤
የቆምኩበት ምድር ዛሬ በነጻነት፣
ሰው ተከፍሎበታል በደምና በአጥንት
በማለት ያዜመችውም ይህ እውነት ግድ ብሏት ነው።እንደ ቀደምት ጀግኖች ወላጆቻችን እያንዳንዱ ዜጋ ለነጻነት ተዋድቆ ለሀገሩ ክብር በጦር ሜዳ የደምና የሥጋ ግብር ባይገብርም ቢያንስ ግን ሁሉም ሰው በተወለደበት እለት እትብቱ ለዚህች አፈር ግብር መግባቱ ሊዘነጋ አይገባም።በመወለድ እትብት በመሞት ከአፈር ጋር የመደባለቃችን ምሥጢር ረቂቅ ነው የሚባለውም ስለዚሁ ነው፡፡
ሀገር ኅብር ነች! ሲባል ከተራሮቿ የገዘፉ ታሪኮች ባለቤት ስለሆነች ነው።ታሪኮቿን የሸመኑት ደግሞ የውብ ባህሎችና ቋንቋዎች ባለቤቶቹ ብሔረሰቦቿ ናቸው።ታሪኳ እንደ በጋ ፀሐይ ደምቆ የሚያበራው በአፈሯ ላይ እንደ ጠንካራ አእማድ ፀንተው የቆሙትና ለነጻነት የተከፈሉት የጀግኖች ልጆቿ አጽሞች የማይደበዝዝ ብርሃን የማፍለቅ አቅም ስላላቸውም ነው።የጀግኖች የነፃነት አሻራ በግፈኞች አቧራ አይከደንም ።የፈሰሰው ክቡር ደማቸውም ክፉዎች በሚያጋግሉት “የምላስ ሰደድ” አይደርቅም።
ትቢያ ሆኖ ከትቢያ ጋር ተቀላቅሎ ኮሲ ላይ የሚደፋው የከሃዲያን ከንቱ ደም ብቻ ነው። የጀግኖች ክብር አይደበዝዝም የሚባለውም ኃይሉ አይበገሬ ስለሆነ ነው። የጀግና ድምጽ ከአድማስ አድማስ ያስተጋባል፣ ሌጋሲውንም ብልና ዝገት አያበ ላሸውም። ሀገር የምንላት ሀገር የተሰራችው እንዲህ ነው። ኢትዮጵያ ማለት በእንደዚህ ዓይነቱ የልጆቿ ደምና አጥንት የተሸመነች ስለሆነች የምንጎናጸፋት የክብር ልብሳችን ነች የምንለውም ስለዚሁ ምክንያት ነው ። ጌጣችንም ስለሆነች እንዋብባታለን ። የሚሞቀን እርሷን ስንደርብ፣ የምንኮራውም በእርሷ ታዛ ሥር ስንጠለል እንጂ ያለበለዚያማ “የቅኝ ተገዢ” ሀገራትን ሕዝቦች አኗኗር ብቻ ማየቱ በቂ በሆነ ነበር፡፡
ባለ አገርነት፤
“የባለ ሀገር ዜማና እንጉርጉሮ ዘመንና መንግሥታዊ ሥርዓቶች ሲለዋወጡ እንደሚለዋወጠው የብሔራዊ መዝሙር ዓይነት አይደለም ።ግጥሙም ሆነ እምነቱ ዘመን ተሻግሮ የሚያሻግር አቅም ያለው ነው”። “ባለሀገርነት የሀገር ሰውነት፤ ባለርስትነት ነው” ይሉታል መዛግብተ ቃላት አዘጋጁ ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ግጽው ። የኢትዮጵያዊው ባለሀገር መዝሙር እንዲህ የሚል ይዘት ያለው ነው፤
እናት አባት ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣
ወንድም እህት ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣
ዘመድ ወዳጅ ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣
አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል፡፡
ይህ ነው የባለአገር ውርስና ቅርሱ ።ይህ ነው የጽናቱ መገለጫና ማስረጃው ። ባለሀገር ውርስ ተቀባይ ብቻም ሳይሆን አውራሽም ነው ።ለአባቱ መቃብር፣ ለእናቱ ዘላለማዊ ማረፊያ ክብር ነስቶ በአጽማቸው አያሾፍም፤ በታሪካቸውም አያላግጥም ። የዛሬ መሠረቱ ትናንት እንደሆነ በሚገባ ያምናል እንጂ ትናንትን እየኮነነ በዛሬው ማንነቱ አይመጻደቅም ። ባለሀገር የትናንትን ክብርና በጎነት ያጎላል እንጂ “ታሪካዊ ስህተትን እየመዘዘ” የራሱን የታሪክ አቁማዳ አይሰፋም ። ባለሀገር ሀገሩን ተሸክሞ የሚዞረው በጫንቃው ላይ ሳይሆን በልቡ ላይ አትሞ ነው ። የጫንቃ ሸክም ለድካም ይዳርጋል ። ጉልበት ሲዝልም ሸክምን ማሳረፍን ግድ ይሏል ። የልብ ማኅተም ግን አብሮ ይኖራል፤ አብሮም ይቀበራል ።ባለሀገር ይህ ነው፤ እንዲህም ነው ፡፡
ባእድ ባለሀገር፤
ባእድነት ጽናት የለውም። አድሮ ሂያጅ ነው። ያገኘውን በልቶ፣ ባገኘው ቦታ አድሮ ለቀጣዩ ጉዞው ይዘጋጃል እንጂ እንደ ቋሚ ነዋሪ ሩቅ አልሞ ሩቅ አይናፍቅም ።ባእድ ባለሀገርም እንደዚያው ነው ። የሀገርን ክብር የእኔ፣ ለሕዝብ ፍቅርም ከእኔ ብሎ አይጨክንም። ለመተግበርም የሞራል ብቃት አይኖረውም ። ባእድ ባለሀገር ምንግዴ፣ ነገን ሳይሆን ዛሬን ናፋቂ ነው። ሀገር ፈተና ሲገጥማት ተግቶ የሚፈልገው መውጫውን ብቻ ነው ።የተቃኘውም “ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል” ሳይሆን “ሁለት ባላ ትከል አንዱ ቢነቀል በአንዱ ተንጠልጠል” በሚለው ብሂል ነው። ስለዚህም ሀገር ለእርሱ የእለት እንጀራ ገበያ እንጂ የዘላለም ማዕዱ እንደሆነች አይቆጥርም፡፡
የሀገር ታሪክ ለእርሱ ከተረት ተረት ያነሰ ተረክ ነው።ባእድ ባለሀገር ደፋርም ነው።ነገሮችን የሚመዝነው በራሱ ጥቅምና ሚዛን ልክ እንጂ በሀገር የክብር ልክ አይደለም ።የአመለካከቱ መንሸዋረር በማንነቱ ላይ ቀውስ ስለሚያስከትልበትም የነገን ብራ ቀን አይቶ ተስፋ ከማድረግ ይልቅ ዛሬውን ብቻ አሳምሮ መኖር የሕይወቱ መርህ ነው። ሀገር የባለሀገሩ እንጂ የባእድ ባለሀገር አይደለችም፤ ልትሆንም አት ችልም ። ሀገር ነበረች፣ አለች ትኖራለች ። ባለሀገር ለታሪኳና በታሪኳ ኮርቶ በሕዝቡ ፍቅር ወዝቶ ይኖራል። ባእዱ ባለሀገር ግን እያለ የለም ።ልቡ መንታ፤ ግብሩም ክፋት ነው። ውሎ አድሮ በሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ተግባሩም ጭምር ስለሚከረፋ “ቅዱሱ የሀገር አፈር” ራሱ ይጠየፈዋል ።
“ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!” መፈክር የባለሀገሮች መፈክር ነው ።የሀገር ቤትና የውጭ ሀገራት ውጭ አደር ባእዳን ውርጃዎች ጩኸትማ በነጋ በጠባ ሲያጥወለውለን እያስተዋልን ነው ።አሃ! ለካንስ ኢትዮጵያ ችግሮቿን ሁሉ እየጣሰች በወጀብና በአውሎ ነፋስ ውስጥ ቀዝፋ በአሸናፊነት ስትወጣ የኖረችው በባለሀገር ልጆቿ ፍቅር ተከልላና ተሸፍና ነው ።ለከሃዲያን ባእድ ባለሀገሮችማ ይህ እውነት ተሰውሮባቸው የለ መች ይገባቸዋል? ለኢትዮጵያውያን ባለሀገሮች ግን የኢትዮጵያዊነት ምሥጢር ባህላቸው ስለሆነ ይኮሩበታል፣ ይመኩበታልም ።ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2013