አዲስ አበባ፡- በአሁኑ ወቅት ያለው የሲቪል ሰርቪሱ ቁጥር ሀገሪቷ ከምትሸከመውና አገልግሎቱ ከሚፈልገው በላይ የበዛ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ ዶ/ር አስታወቁ::
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው ነገሪ (ዶ/ር) በተለይም ለኢፕድ እንዳስታወቁት፤ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ ያለው የሠራተኛ ቁጥር በጣም በርካታ ነው:: ሀገሪቷ ከምትሸከመውና አገልግሎቱ ከሚፈልገው በላይ የበዛ ነው:: ከአደረጃጀት አንጻር ሲታይም በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ መዋቅሩ የሚሸከመው ብዙ የሰው ኃይልን ነው፤ ብዙ የሰው ኃይል በተሸከመ ቁጥር ደግሞ የሚያገኘው ጥቅም አናሳ ነው::
የመንግሥት ሠራተኞች የብዛታቸውን ያህል የሚሠሩት አገልግሎት የሚያረካ አይደለም ያሉት ዶ/ር ነገሪ ፤ የተወሰኑ ይሠራሉ፤ ሌሎቹ ግን የተወሰኑ ሠራተኞች ሌሎቹ ግን የተወሰኑ ሠራተኞች በሠሩት ትከሻ ላይ ተንጠላጥለው የሚኖሩ ናቸው:: የሚለፋው ሠራተኛ ጥቂት ሲሆን፣ የሚያገኙት ጥቅምም በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ አመልክተዋል::
ይህ የሆነው ከላይ በሕግ የሚመራ፣ የሚወስን፣ በበላይነት ሥራን በአግባቡ የሚመዝንና ለዚህ ሥራ ይህን ያህል ሰው ያስፈልጋል የሚል ማዕከላዊ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ነው ያሉት ዶ/ር ነገሪ ፣ የተለያዩ ተቋማት መዋቅራቸውን ሠርተው ያመጣሉ፤ ያጸድቃሉ:: ይህ አይነቱ አሠራር እስከ ወረዳ ድረስ በስፋት የሚስተዋል ነው ፤ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይም ችግር እየሆነ ነው ብለዋል::
በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የፌዴራል ሠራተኞች አዋጅ በዋናነት ያስፈለገው በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ነው:: የዓዋጁ ዓላማም የኢትዮጵያን ሲቪል ሰርቪስ መቀየር ያስፈልጋል ፤ መቀየር ካልተቻለ እንደ ሀገር የተጀመረው ሪፎርም ከግቡ መድረስ እንደማይቻል ጠቁመዋል::
እንደ ሀገር በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊውም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ ትልልቅ ሪፎርም እየተካሄደ ነው:: በጸጥታውም ሆነ በሚሊታሪ እንዲሁም በደህንነቱ ዙሪያ በተመሳሳይ መልኩ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በርካታ ሪፎርሞች እየተካሔዱ ናቸው:: እነዚህ ትልልቅ ሪፎርሞች ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት በጣም ግዙፍ የሆነው የሲቪል ሰርቪስ ሴክተር ሪፎርም ተደርጎ ውጤታማ አገልግሎት ሲሰጥ ነው ፤ አዲስቷ ኢትዮጵያ ልትፈጠር የምትችለው በዚህ መልክ ነው ብለዋል::
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የመንግሥት መስታወት ናቸው ተብለው የሚታሰቡ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ነገሪ ፣ በፐብሊክ ሰርቪሱ ላይ ጥራት ያለው አገልግሎት ካለመኖሩም በተጨማሪ እጅ መንሻና ማጉላላት የተለመደ መሆኑን ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት ያለእጅ መንሻ አገልግሎት ማግኘት አይቻልም ተብሎ የተደመደመበት ሁኔታ እንዳለ የተሸሸገ አለመሆኑን አስረድተዋል::
እርሳቸው እንደተናገሩት፤ የወጣው አዋጅ ይህንንም አይነት ችግር የሚፈታ፣ የሠራተኛውንም ጥቅማጥቅም ያካተተ ፤ ተወዳድረው የተሻለ የሚሠሩ ሠራተኞች የተሻለ ነገር የሚያገኙበትን ሁኔታ ያስቀመጠ ነው:: አዋጁ እንደከዚህ ቀደሙ ዝም ተብሎ የመንግሥት ሠራተኛ የሚል ስም ይዞ መቀጠል የማያስችል ነው:: የተዘጋጀውም ይህን ታሳቢ በማድረግ ነው::
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የመንግሥት ሠራተኞች ቁጥር ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ይጠጋል፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ የፌዴራሉ 250 ሺ ያህል ነው ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም