ሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደራ ወረዳ ዘግናኝ እና አሰቃቂ ተግባር የፈጸሙ ጽንፈኛ እና አሸባሪ ቡድኖችን ለሕግ ለማቅረብ አበክሮ እየሠራ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ፡፡ ቡድኖቹ ለዘመናት ማንም በማይበጥሰው የወንድማማች እና እህትማማች ገመድ የተሳሠሩትን የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦች ለመነጣጠል እና ወደ ግጭት ለማስገባት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለም አመለከተ።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በደራ ወረዳው የደረሰውን ዘግናኝ እና አሰቃቂ ግድያ አስመልክቶ ትናንት ባወጣው መግለጫ ፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድኑ በሕዝብ ስም እየማለ እታገልለታለሁ የሚለውን የአማራ ሕዝብ ለከፋ ጉዳት እና አሰቃቂ ችግሮች እየዳረገው እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ቡድኑ የሰዎች እና የምርት እንቅስቃሴ በክልሉ ውስጥ እንዳይኖር መሰናክል ፈጥሯል፤ ሰው እያገተ የድሃ ገንዘብ ዘርፏል፤ ሕፃናትን በማገት የቤተሰብ ጥሪት ከሟሟጠጥ ጀምሮ ያገታቸውን ሕፃናት በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፤ አካባቢያቸው ሰላም እንዲሆን የጠየቁ የሀገር ሽማግሌዎችን አግቶ ገንዘባቸውን በመዝረፍ በእንብርክክ አስኪዶ መግደሉንም አመልክቷል።
አዳጊ ሕፃናትን ከትምህርት ገበታቸው እንዲነጠሉ አድርጓል፤ የሙያ ሥነ ምግባራቸውን እና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በትምህርት ገበታ ላይ የተገኙ መምህራንን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏቸዋል፤ በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ ቦንብ በማፈንዳት በተማሪዎች ላይ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አድርሷል፡፡ ከዚህም በላይ የሆኑ፣ የሰሚን ጆሮ ጭው የሚያደርጉ ዘግናኝ ወንጀሎችን መፈጸሙን ጠቁሟል።
ጽንፈኛ ቡድኑ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን እና የሕዝብ አብሮነትን የማይቀበል ኋላ ቀር ኃይል ነው ያለው የክልሉ መንግሥት መግለጫ ፣ ይልቁኑም መቃቃርን የሚፈጥር፤ የኅብረተሰቡን ዕሴት በመሸርሸር እና አሰቃቂ ጥፋቶችን በመፈጸም የተጠመደ አረመኔያዊ ቡድን መሆኑን አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ሽብርተኛው የሸኔ ቡድንም እታገልለታለሁ የሚለውን የኦሮሞ ሕዝብ እጅግ መራር እና አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ግድያ፤ እገታ፤ ዝርፊያ፤ አፈና እየፈጸመበት ይገኛል፡፡ ሁለቱም ጽንፈኛ ኃይሎች ለአንድ አሰቃቂ ዓላማ ሁለት ቦታ የተሰለፉ ዕኩይ ቡድኖች ናቸው። እየፈጸሙት የሚገኙት እኩይ ተግባር በጦር ሜዳ የደረሰባቸውን ኪሳራ ለማስቀየሻ የሚፈጽሙት ነው ብሏል።
መቃብራቸው የሚቆፈረው በሕዝቦች ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ በመሆኑ፣ ሕዝብን እርስ በርስ ማጋጨት እና ንጹሃንን መጨፍጨፍ የትግል ስልታቸው ነው። እነዚህ መቃብራቸው የተማሰ፣ ልጣቸው የተራሰ ጽንፈኛ እና ሽብርተኛ ቡድኖች፤ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደራ ወረዳ ያደረሱትን ዘግናኝ እና አሰቃቂ ድርጊት የአማራ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ በጽኑ ያወግዛሉ፡፡ ይህ ወንጀል ሰው የሆነ ፍጡር የማይፈጽመው የአውሬነት ተግባር መሆኑንም አመልክቷል።
እነዚህ በጣዕረ ሞት ላይ የሚገኙ ጽንፈኛ ኃይሎች፣ ለዘመናት ማንም በማይበጥሰው የወንድማማች እና እኅትማማች ገመድ የተሣሠሩትን የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦች ለመነጣጠል እና ወደ ግጭት ለማስገባት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ነገር ግን ሰላም ወዳዱ እና አርቆ አሳቢው ሕዝባችን ነገሮችን በጥንቃቄ እና በአስተውሎት በማየት፣ ድርጊታቸውን እና ዓላማቸውን ቀድሞ በመረዳት፣ የጽንፈኞችን እና የሴረኞችን እኩይ እና አጸያፊ ተግባር በንቃት እየመከተ እንደሚገኝ በመግለጫው ገልጿል ፡፡
የአማራ ሕዝብና የአማራ ክልል መንግሥት ከኦሮሞ ሕዝብና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን እነዚህን ዘግናኝ ተግባር የፈጸሙ ጽንፈኛ እና አሸባሪ ቡድኖች ለሕግ ቀርበው አስፈላጊውን ቅጣት እንዲያገኙ አበክሮ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልላዊ መንግሥት ከውጭና ከውስጥ ጠላቶቻችን ጋር በጋራ የሚሠሩ፣ እንዲሁም እርስ በርሳቸው የሚናበቡ ጽንፈኛ ኃይሎች፤ በንጹሐን ዜጎች ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ በመፈጸም በሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚፈጽሙትን እኩይ ተግባር በአስተማማኝ ሁኔታ በመቀልበስ ብርቱ ክንዳችንን እያሳረፍንባቸው እንገኛለንም ብሏል።
ወደፊትም ይህን ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል ያለው የክልሉ መንግሥት ፤ መላው የክልላችን ሕዝብና ሌሎች ወንድም እና እህት ኢትዮጵያውያን የሕግ የበላይነት እንዲከበር ከጎኑ በመሰለፍ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም