አሁን አሁን ከተማችን፣ በተለይ አዲስ አበባ ባልተጠበቀ ፍጥነት በኤሌክትሪክ በሚሰሩ መኪኖች እየተሞላች ትገኛለች። በአይነታቸውም ሆነ በቁጥራቸው፤ እንዲሁም በ”እንከን የለሽ” ሞዴላቸው እየበዙ የመጡት እነዚህ ተሽከርካሪዎች በትራንስፖርቱ ዘርፍ ለማህበረሰቡ ያመሰጡት ኢኮኖሚያዊም ሆነ አገልግሎታዊ ፋይዳ ገና በውል ባይታወቅም መሬት ላይ ያለው እውነታ እንደሚያሳየው ከሆነ ግን ተሽከርካሪዎቹ በየእለቱ እየጨመሩ በመሄድ ላይ ናቸው።
የመኪኖቹ የተመራጭነት ምንጭ:-
መኪኖቹ የአየር ብክለትን የማያስከትሉ መሆናቸው፤ የተፈጥሮ አካባቢን ከመጠበቅ አንጻር ሀገራችን የፈረመችውን ስምምነት ለማክበር ማስቻላቸው፤ በነዳጅ ከሚሠሩ መኪኖች ይልቅ በተሻለ ዋጋ መገኘታቸው፤ ከመቆሚያ ስፍራ አጠቃቀም፣ ፍጥነት ወዘተ አኳያ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል።
ከዚህ አንፃር ይመስላል የኢትዮጵያ መንግሥት በነዳጅ የሚሽከረከሩ መኪኖች ታግደው በኤሌክትሪክ የሚሰሩቱ ብቻ እንዲገቡ የወሰነው (የፈቀደው)። መወሰን ብቻ አይደለም፤ በ2030 500ሺህ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ግብ አስቀምጧል። ይህ ደግሞ በባለሙያዎች ሳይቀር እያስመሰገነው ይገኛል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታወጣው ለነዳጅ ግዢ መሆኑን ያነሱት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ፤ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርኼ ጉዳዩን አስመልክተው ከአዲስ ዘመን ጋር አድርገውት በነበረው ቆይታቸው “በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች በተለይ ነዳጅ አምራች ላልሆኑ ሀገራት ለነዳጅ የሚያወጡትን ወጪ በከፍተኛ መጠን በመቀነስ ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ” እንዳላቸው ሲገልፁ ።
“በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ላለው ሀገር፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪኖችን መጠቀሙ የትራንስፖርት ዘርፉን በራስ አቅም የማንቀሳቀስ መልካም ጅምር” መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ፣ ዝቅ ብለን የምናነሳቸው፣ እነ አብራክ እየሰሩት ያለው ፖሊሲ ተኮር ተግባር ከገበያ ትርፍና የቢዝነስ እንቅስቃሴ ባሻገር ከላይ ለተጠቀሱት መሰረታዊ ጉዳዮች ሁሉ የበኩላቸውን እያደረጉት ነውና ሊያስመሰግናቸው ይገባል ማለት ነው።
ዛሬ፣ ዛሬ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖችን በማስመጣት ገበያ ላይ የሚያውሉና ሌሎች የተለያዩ የቢዝነስ ተቋማትን የሚመሩ አካላት የመንግስትን ርምጃ ተከትሎ ሀገርን አንድ እርምጃ ወደ ፊት በሚያራምድ ሁኔታ ኢኮኖሚውን መደጎም ላይ እየሰሩ መሆናቸው እየተስተዋለ ነው።
ይህ በጣም ጥሩ ጅምር ነው። እንዲህ አይነቱ አሰራር እየተጠናከረ ከሄደ ተቋማቱ በህብረተሰቡ ከመወደዳቸው፣ መታቀፋቸውም ባለፈ ይከበራሉና “የውጪ ባለ ሀብቶች በገቡ” የሚለውን፣ የአንዳንዶች የብሶት አስተያየት የሚያስቀር ይሆናል።
“ያብራክ ብድርና ቁጠባ ሕብረት ስራ ማኅበር” በትራንስፖርት ዘርፍ ስራ ላይ ለተሰማሩ አሽከርካሪዎች፣ የመኪና ረዳቶች፣ እንዲሁም በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ለሚሰሩ ሰራተኞችና በቂ ቁጠባ ላጠናቀቁ ሰዎች እያንዳንዳቸው 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኤሌክትሪክ መኪኖችንና አውቶሞቢሎችን በአነስተኛ ወለድ ለባለዕድለኞች ቁልፎቻቸውን “እነሆ” ብሏል።
ማህበሩ ለ3ተኛ ጊዜ 24 (በ2ተኛው ዙር 54) የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለባለዕድለኞች (ለቁጠባ ሻምፒዮኖች) ባስረከበበት ወቅት (ሕዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም መስቀል አደባባይ) እንደ ተነገረው መኪኖቹን ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባው “ጎሸር ትሬዲንግ” ሲሆን፤ “ዘመን ኢንሹራንስ” ደግሞ የኢንሹራንስ ድርሻውን ይዟል። እነዚህ እንደ አንድም ሶስትም ሆነው የሰሩና እየሰሩ ያሉ ድርጅቶች ከመንግስት ፖሊሲ አኳያ ብቻ ሳይሆን፤ መኪኖቹ ከሚያበረክቷቸው ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ አበርክቶዎች ባለፈም ለፈጠሩት ወደ ፊትም ለሚፈጥሩት ሰፊ የስራ እድል ከወዲሁ ሊመሰገኑ ይገባል።
እነዚህ አንድም ሶስትም የሆኑ የቢዝነስ ተቋማት በሚቀጥለው ዙር (በቅርቡ ነው የተባለው) ተጨማሪ 35 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በተመሳሳይ መንገድ ለተጠቃሚዎች እንደሚያስተላልፉ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፤ ሌሎች ተቋማትም ይህንኑ መንገድ እንደሚከተሉ አንዳንድ መረጃዎች እያመለከቱ ይገኛሉ።
የቱሪዝሙን ሴክተር ለማልማትና በአስደናቂ ሁኔታ ከለሙት የቱሪዝም መዳረሻዎች አኳያ ‹‹ለቱሪዝም ታክሲ የሚያገለግሉ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለማስገባት የመንግሥትን ምላሽ እየጠበቅን ነው›› በማለት ለሪፖርተር ጋዜጣ ድምፃቸውን የሰጡት የቱኤምቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ አክሲዮን ማኅበር መሥራች አባልና የማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ወንደሰን ለገሰ፤ በአሁኑ 3ሺህ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ አስመጥተን አሁን ለተመዘገቡት የማኅበሩ አባላት (በስሩ በገንዘብ ሚኒስቴርና ቱሪዝም ሚኒስቴር እውቅና ያላቸው 55 ማህበራት አሉ) የምናስረክብ ይሆናል፡፡
አገልግሎቱ በእነዚህ ማኅበራት ብቻ ይቆማል ማለት አይደለም፡፡ በቀጣይ ክፍተቶችን ተመልክቶ ባልተዳረሱ የቱሪስት መዳረሻዎች፤ በተለይም በሀገር ውስጥ ቱሪዝም ዙሪያ ለመሥራት ዕቅድ አለን፡፡ ይህም በሀገር ውስጥ ቱሪዝም የተለያዩ ተቋማትንና ተማሪዎችን ጨምሮ በቱሪዝም መዳረሻዎች ለማንቀሳቀስ ሃሳብ አለን፡፡
በዚህም መሠረት 1.2 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለማጓጓዝ አቅደናል፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ ከ25 እስከ 60 ተሳፋሪዎች የመያዝ አቅም አላቸው፡፡ ለራይድ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችንም በማስመጣት ለግለሰቦች በሽያጭ መልክ እያቀረብን እንገኛለን፡፡ በቅርቡም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በሀገር ውስጥ ገጣጥመን ለማቅረብ ሒደቱን በማጠናቀቅ ላይ ነን፡፡ በማለት እቅዳቸውን ይፋ አድርገዋል። ዘርፉ ከዚህ የበለጠ ይስፋፋ ዘንድም የሚመለከታቸውን ሁሉ አሳስበዋል።
እነዚህ እዚህ የጠቀስናቸው ብቻ ሲሆኑ፤ ሌሎች በርካቶችም ተመሳሳይ ተግባራትን እያከናወኑ ስለመሆናቸው መጠራጠር አይቻልም። ይህ የመንግሥት አቋምም ሆነ ወቅቱ ያስገደደው ሁኔታ (የአየር ንብረት ለውጥ መከሰትና ሌሎችም) በተወሰኑ ሰዎች ወይም የቢዝነስ ተቋማት ብቻ የተደገፈ አይደለም።
በተለያዩ ሀገርና አህጉር አቀፍ ተቋማት ጭምር ወደ ተግባር የተገባበት፤ ለዚህም የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ሌሎችም ከእንግዲህ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ቤት ላለማስገባት ደንብና መመሪያን ያዘጋጀበት፣ ግዥንም በተመለከተ የእነዚሁ ተሽከርካሪዎች ግዥ የሚፈፀምበት ሁኔታ ተፈጥሯልና ኢትዮጵያ “ብቸኛዋ የነዳጅ መኪና የከለከለች ሀገር” ከሚለው የተነሳ የዓለም ሚዲያዎች የአንድ ሰሞን ውርጅብኝ ነፃ ስለመሆኗ ጥሩ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል።
ባጠቃላይ፣ ሂደቱን እያደነቅን፣ ማንኛውም ነገር ሄዶ ሄዶ ሰው ተኮር መሆን አለበትና ይህ የኤሌክትሪክ መኪኖች በቁጥርም ሆነ በአይነት እየጨመረ መምጣት “ለትራንስፖርት ተገልጋዩ ሕብረተሰብ ምን ይዞለት መጣ?” የሚለው ቀላል፤ ግን ደግሞ እጅግ አስፈላጊና ተገቢውን መልስ የሚሻ ጥያቄ በማንኛውም የተሽከርካሪዎቹ ባለ ድርሻ አካላት አእምሮ ውስጥ ተደጋግሞ ሊመጣና ሰው ተኮር በሆነ መልኩ (የሚቀንስ የትራንስፖርት ታሪፍም ካለ) ሊስተናገድ ይገባል እንላለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም