ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ
አዲስ አበባ፡- ባለፉት አምስት ዓመታት የተገኙ ስኬቶች ኢትዮጵያ በተስፋ ሰጪ ጎዳና ላይ መጓዝ የጀመረች መሆኗንና የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና አይቀሬ መሆኑን አመላካች እንደሆነ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ አስታወቁ::
ዶ/ር ቢቂላ ፤ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የተጓዘችው የአምስት ዓመት ጉዞ ስኬት ያስመዘገበችበትና ፈተናም የተጋፈጠችበት ቢሆንም በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲ መስክ ያስመዘገበቻቸው ድሎች ታላላቅ ናቸው። የሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና አይቀሬ መሆኑን ያመላከቱ ናቸው::
ብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያቀፈ፣ ኅብረ ብሔራዊ፣ ሀገራዊና ወጥ ፓርቲ ሆኖ በመፈጠሩ ምክንያት ኢትዮጵያውያን በአንድ ጥላ ስር መሰባሰብ የቻሉበት ነው:: በዚህ ፓርቲው ከተፈጠረ ወዲህ በሀገራችን የትርክት ለውጥ መጥቷል ፤ ከሚለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን እና አብሮነትን የሚፈጥሩ ትርክቶች እንዲጠናከሩ ማድረግ ተችሏል ብለዋል::በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በብሔር፣ በኃይማኖት እንዲሁም በማንነት ሁኔታ ውስጥ ገብታ ዜጎቿ ይበታተናሉ የሚለውን ስጋት በመቀልበስ ፤ ፓርቲው ኢትዮጵያውያንን ልክ እንደ እናትነት በአንድ ጥላ ስር ማሰባሰብ መቻሉን አመልክተዋል::
በፖለቲካው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ባለፉት አምስት ዓመታት በኢኮኖሚውም ትልቅ ለውጥ ማምጣት ተችሏል:: በዚህ ረገድ ብልጽግና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞች በማካሔዱ ኢኮኖሚውን ከመንኮታኮትና ከውድቀት የታደገ ፓርቲ ነው:: የእዳ ማስተካከያ እና የእዳ ሽግሽግ በማስደረግ የሀገሪቱን የእዳ ጫና በማቃለልም ትልቅ ሥራ የሠራ ነው ብለዋል::
ከዚህ ቀደም ዝም ብሎ ግብርና መር ብቻ ይባል የነበረው የኢኮኖሚ እሳቤ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እንዲሆን ግብርናን፣ ማኑፋክቸሪንግን፣ ማዕድንን፣ ቱሪዝምን እና የዲጂታል ኢኮኖሚን አንድ ላይ በማጣመር የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዘርፎች ሚዛናቸውን ጠብቀው እና ተደጋግፈው እንዲያድጉ ማድረግ ያስቻለ ሥራ መሥራቱን አስታውቀዋል:: በዚህ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀደምት ትልልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው አምስት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል::
ብልጽግና በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በስንዴ ልማት እንዲሁም የሌማት ትሩፋት እና ሌሎች ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ አዳዲስ እሳቤዎችንም በማምጣት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ከውጭ ሀገር ማስገባትን ያቆመችበት እንዲሁም አቅሟን አጠናክራ ስንዴን ወደውጭ ሀገር መላክ የምትችል ሀገር መሆኑዋን በተግባር ያስመሰከረችበት ሀገር እንድትሆንም ያስቻለ ፓርቲ እንደሆነ አስታውቀዋል::
በማህበራዊውም ሆነ በዲፕሎማሲው ረገድ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ደፍራ እና አንገቷን ቀና አድርጋ ጎልታ የታየችበት ጊዜ ነው ፤ ለአብነት ያህል ሀገሮች የብሪክስ አባል ሀገር ለመሆን በብዙ ሲጥሩና ሲፈልጉ የነበሩ ኢትዮጵያ ግን ይህን ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠውን ስብስብ በቀዳሚነት መቀላቀል የቻለች መሆኗ ትልቅ ስኬት ሆኖ የተመዘገበ ነው ብለዋል:: ያለፈው አምስት ዓመት ሀገሪቱ በተለይም በዓለም አደባባይ አንገቷን ቀና አድርጋ መኖር እንደምትችል ያሳየችበትን ሥራዎች ብልጽግና ፓርቲ ማከናወኑን ተጨባጭ እውነታዎች የሚመሰክሩት ነው ብለዋል ::
ፓርቲው በዚህ ወር ‹‹የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና›› በሚል መሪ ሃሳብ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማክበር ላይ የሚገኝ መሆኑን አስታውሰው፤ የመሪ ሃሳቡ ዋና መልዕክትም የሀገራችን የፖለቲካ ድባብ ከጉልበት፣ ከመጠፋፋት፣ ከጦርነት፣ ከደም ማፋሰስ መንገድ ወጥቶ ወደ ሃሳብ ልዕልና መሸጋገር ያለበት መሆኑን ገልጸዋል::
ሀገራችን የፖለቲካ ድባብ ዴሞክራሲያዊ እና የሠለጠነ እንዲሆን በሀገራችን ውስጥ ወደ ኋላ ተመልሶ ቂም እና ቁርሾን የሚቆጥር መሆን የለበትም:: የወደፊቱን የትውልድ ተስፋና እድል አይቶ በጋራ መሆንና መሰባሰብ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያስፈልጋል:: ሃሳብን ሸጦ ሃሳብ በመግዛት የሚያምን የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አመልክተዋል ::
ከፊታችን ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም ሀገራዊ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ይኖራል:: የሀገሪቱ ከፍተኛ መሪዎች እና ኃላፊዎች በሚገኙበት ከዚህ በፊት ከቀበሌ ጀምሮ ሲከበር የነበረውን የአምስተኛ ዓመት ክብረ በዓል በሚያጠቃልል ደማቅ በሆነ መልኩ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ጠቁመዋል::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም