በሰብል አሰባሰብ ወቅት የሚደርስን የምርት ብክነት ለመቀነስ ተገቢው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል!

የ2016/17 የምርት ዘመን ክረምቱ የተስተካከለ በመሆኑ፣ የማዳበሪያ አቅርቦት እና የተጠናከረ የቅድመ ዝግጅት ሥራ በመከናወኑ ከፍተኛ የሰብል ምርት ማምረት ተችሏል። በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምዕራብ እና በምስራቅ በየአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የሚታየው ይህ የምርት መጠን ታጭዶ የሚያልቅ ፣ ምርቱ ጎተራ የሚበቃው አይመስልም። በመሆኑም ምርቱን ከስብሰባ ጀምሮ እስከ አጓጉዞ ማከማቸት እንዲሁም ወደ ገበያ እስከ ማቅረብ ያለውን ሥራ በተገቢው መንገድ መም ራትና ሳይባክን ጥቅም ላይ እንዲውል ማ ድረግ ያስፈልጋል ።

የግብርና ሥራ በሀገራችን ረጅም ታሪክ ያለው ቢሆንም እስካሁን ድረስ የአብዛኛው አርሶ አደር አስተራረስም ሆነ የሰብል ምርት አሰባሰቡ ጊዜ የሚወስድ ፣ በርካታ የሰው ኃይል ጉልበትን የሚጠይቅ ባህላዊ መንገድን ብቻ የተከተለ ነው። የተሰበሰበው ምርትም የሚጓጓዘው በጋማ ከብት ፣ ገበያ ላይም የሚቀርበው ለብክነት በተጋለጠ መልኩ በመሆኑ በተለያየ መልኩ የምርት ብክነት ይከሰታል።

በባህላዊ መንገድ የሚደረግ የሰብል አጨዳ ፣ መከመር ፣ ውቂያና ማጓጓዝ የሚወስደው ጊዜ ወቅቱን ላልጠበቀ ዝናብ የማጋለጥ ዕድሉንም ሰፊ እንዲሆን ያደርገዋል። በመሆኑም አሁን የተገኘውን ከፍተኛ የሰብል ምርት ተገቢው ጥንቃቄ በተሞላበትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከብክነት ማዳን ይገባል።

በሀገራችን በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጉድለት ምክንያት በየዓመቱ ከሚመረተው አጠቃላይ የምርት መጠን 70 ሚሊዮን ኩንታል ይባክናል። በየዓመቱ ከሚገኘው አጠቃላይ ሰብል መካከልም ከአሰባሰብ ጀምሮ ምርቱ ጥቅም ላይ እስከሚውል ድረስ 25 በመቶ ምርት ጥቅም ላይ ሳይውል ይቀራል።

ይሄንን የምርት ብክነት ለመቀነስ አርሶ አደሩ በአንድነት ወይም በኅብረት ሥራ ማህበራት አማካይነት ብክነትን ለመቀነስ የሚያግዙ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ማበረታታት ያስፈልጋል። በሃገሪቱ ባለፉት አራት ዓመታት የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርት ብክነት መጠንን ከነበረበት 35 በመቶ ወደ 25 በመቶ ማውረድ ተችሏል። ይህም ሆኖ አሁንም በየዓመቱ 70 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ጥቅም ላይ ሳይውል ይባክናል።

በሀገሪቷ በአብዛኛው ሰብል ከመሰብሰብ ጀምሮ ምርትን ለገበያ እስከ ማቅረብ ወይም ጥቅም ላይ እስከማዋል ድረስ የሚከናወነው በተለምዶ በበሬና በሰው ጉልበት ነው። ይህም መሆኑ ምርቱ ለብክነት ይዳረጋል። በሰብል መሰብሰብ ወቅት የሚፈጠርን ብክነት በመቀነስ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀምበትን መንገዶች ማመቻቸት፣ የአርሶ አደሩን ንቃተ ህሊና የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን መስጠት ያስፈልጋል።

ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የብክነት መጠኑን እስከ 15 በመቶ ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። አሁን ላይ ከምርት አሰባሰብ እስከ ማስቀመጥ የሚከሰተውን ብክነት ለማስቀረት ዘመናዊና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን አርሶ አደሩ ተግባራዊ እንዲያደርግ በማድረግ ላይ ይገኛል። በዘንድሮው የሰብል መሰብሰቢያ ወቅት አርሶ አደሩ ኮምባይነርን በመጠቀም ምርቱን እንዲሰበስብና ብክነቱን እንዲቀነስ በተለይ በአርሲና በባሌ አካባቢ ያለውን ቴክኖሎጂ የመጠቀም ልምድ ወደ ሌሎች ክልሎች በስፋት እንዲመጣ እየተሠራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል።

አርሶ አደሩ በማህበር ተደራጅቶ የሰብል መሰብሰቢያ መሳሪያ እንዲገዛ የብድር አገልግሎት እንዲመቻችለትና ባለሀብቱም በኪራይ መሳሪያውን የሚያቀርብበት ሁኔታ በቂ ባይሆንም እየተሠራበት ይገኛል። ሌላው ከሚባክነው ምርት 25 በመቶ የሚሆነውን የሚይዘው እህል በጎተራ በማስቀመጥ ሲሆን አንዳንድ የሰብል አይነቶች ለረጅም ጊዜ በጎተራ ሲቀመጡ በተባይ ለብልሽት ይጋለጣሉ።

ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አርሶ አደሩ ምርቱን በአቅራቢያው ለገበያ የሚያቀርብበት የግብይት ቦታ ማመቻት እና ከኅብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ጋር የገበያ ትስስር እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል። የምርት ብክነት መጠንን መቀነስ የሚቻለው አርሶ አደሩ አካባቢ ያሉትን ችግሮች በመለየት የተቀናጀ መፍትሄ በመስጠት እንደመሆኑ ምርቱን ከብክነት ለማዳን አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን ጠንክሮ መስራት ይገባል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You