ዳግም ከበደ
ስንቶቻችን ነን በዓለማችን ጩኸት ተወጥረን ማስተዋ ላችንን የተቀማን? ኧረ እንዲያው ምን ያህሎቻችንስ በሚሆነውና እየሆነ ባለው ነገር ግራ ተጋብተን መስመራችን የጠፋን? አንዳንዶቻችን ዛሬ ስለጨለመብን የነገው ተስፋ ተጋርዶብናል። አንዳንዶቻችን ዛሬ ኃያል ስለሆንን ነገም ከከፍታው ላይ ሳንወርድ የምንቆይ ይመስለናል።
ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም ላይ አንድ ቦታ ላይ ተገትረን ነገን በዛሬ መስፈሪያ ለመለካት የምንሟሟተውን ሰዎች ቤታችን ይቁጠረን። የዛሬው መከራችን ነገ የማይሽር የሚመስለን ስንቶቻችን ነን? ዛሬ የምንሰራው ግፍ በነገው ማንነታችን ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሎ የእጃችንን የማናገኝ መስሎን ሴራ ስንሸርብ የምንውል የምናድር ተፈጥሮን መረዳት ያቃተን እኩያኖችስ።
ዓለም ተቀያያሪ ነች ። የዛሬን ነገ አናገኘውም ። ይሄ ተፈጥሯዊ ኡደት ነው። የማንቀይረው ሃቅ። ተፈጥሮ እንዲህ ከሆነች ዘንዳ እኛስ ከራሳችን አፈጣጠርና በዙሪያችን ካሉት ሁነቶች ምን መረዳት ይኖርብን ይሆን ብለን ጠይቀን እናውቅ ይሆን? አይመስለኝም። ከዚያ ይልቅ በስሜት መጋለብ ይቀድመናል። ሳያስተውሉ መራመድ መገለጫችን ነው ። ዛሬ ሲደፈንብን ነገ አብሮ ይጨልምብናል ። የዛሬ ጉልበታችን ነገም ልክ እንደ አሁኑ እንደፈረጠመ የሚዘልቅ የሚመስለን እውቀት የከዳን ተቅበዝባዦች ከሆንን ቆየን ።
እንዴት ግን ማስተዋል አቃተን? የክርስትና እምነት ተከታዮች መመሪያ በሆነው በታላቁ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተመለከው፤ የአዳምና የሄዋን አብራክ ክፋይ የሆነው ቃኤል ወንድሙን አቤልን በጭካኔ በበረሃ እንደወጣ ደሙን አፍስሶ ይገለዋል ። በቅናት በተልካሻ ምክንያት የወንድሙን ደም በማፍሰሱም በአምላክ ቁጣ የአቤል ደም እድሜውን
ሙሉ ትከተለውና ታስጨንቀው ነበር ። ድርጊቱን ከፈፀመ በኋላ ውስጡ ሃሴት አላደረገችም ይልቁንም ፀፀት እና ሃዘን ወረሰው እንጂ ።
ይህ ድርጊት ከተከወነ ብዙ ዘመናት አለፉ ። ይሁን እንጂ ከቃኤል ስህተት የተማረ ትውልድ ጥቂት ነው። ዛሬም ወንድም የወንድሙን ነብስ በጭካኔ ይነጥቃል ። ግቡን ሳያሳካ የሃዘን ማቅ ለብሶ እርሱም እድሜውን በቁጭት ያሳልፋል ሟችም ያለእድሜው አፈርን ይቀምሳል።
የሰው ልጅ ለእኩል አላማ ያለልዩነት በምድር ላይ የተፈጠረ ቢሆንም ምግባሩን የከዳ ግብሩን የሳተ ይመስላል ። በቆዳው ቀለም፣ በቋንቋው አለመመሳሰል፣ በባህሉ ልዩነት፣ በአመጋገቡና በልዩ ልዩ ነገሮች ድንበር መስራት ይቀናው ከጀመር ዘመናትን ተሻግሯል ። ሲፈጠር ጀምሮ ቁራሽ የራሱ መሬት ይዞ ከእናቱ ማህፀን የተፈጠረ ይመስል ድንበሬን ገፋህ ግዛቴን ነጠቅክ በማለት ክቡር የሆነውን ነብስ ያለ አንዳች ሰብዓዊ ርህራሄ ይቀጥፋል ።
ዓለም አቅላቸውን በሳቱ እኩያን እጅ ከወደቀች ሰነባብታለች ። ያሻውን ያደርግበት ዘንድ የሚያስችለውን ስልጣን ለመቆናጠጥ ሲል በሕዝቦች መካከል ጥላቻን እንደ ስንዴ የሚዘራውን ቤት ይቁጠረው ። እልፍ ዓመት ለማይቀመጥበት መንበረ ስልጣን በአንድነት የሚኖሩ ሕዝቦችን ፍቅር ሸርሽሮ ወንድም በወንድሙ ላይ አጠና ይዞ እንዲወጣ፤ ወጥቶም ያለርህራሄ እንዲጋደል ተግቶ የሚሰራ ልቡ ምንኛ የደነደነ እንደሆነ እንጃ ።
ስህተት በትክክል እንጂ በራሱ በስህተት አይታረምም። ጥላቻን የምናርቀው በይቅርታ እንጂ በተመሳሳዩ በራሱ ጥላቻ አይደለም ። ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ አፍጋኒስታን፣ ኢራቅና መሰል አገራት ለትእግስት ለወንድማማችነት እንዲሁም ሰክኖ ነገሮችን በጥሞና ለማየት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ዜጎቻቸው አገር አልባ ሆነዋል፤ ህጻናት በማያውቁት ጦስ ሳቢያ በየባህር ዳርቻው ፣በዱር፣ በገደሉ አይሞቱ አሟሟት እየሞቱ አውሬ እራት ሆነዋል ።
የቅርብ ጎረቤታችን ሶማሊያ በወንበዴዎችና ልባቸው ባበጠ ማፊያዎች በመንደር ተከፋፍላ ፍትህና ዲሞክራሲ ስትናፍቅ ግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚሆን ጊዜ ዘልቃለች፤ ከብዙ ዓመታት መንግስት አልባነት ከዓመታት በፊት ብትላቀቅም ፣ዛሬም ብዙ ፈተና ውስጥ ትገኛለች ።
ይሁን እንጂ ክፋት ሁሌም የበላይ ሆኖ አይቀርም፤ ጥፋትም እንዲሁ አይኖርም ብሎ መዘናጋት ሞኝነት ነው። ይሄን ሳስብ ከዚህ ቀጥሎ የማቀርብላችሁ ታሪክ ይታወሰኛል። ፅሁፉ ዶክተር ሪቻርድ ካርሰን ከትበውት ወደ አማርኛ የተመለሰ ነው።
አዛውንቱ ሰውዬ
በአንድ መንደር ውስጥ አንድ ጠቢብ ሽማግሌ ይኖሩ ነበር ፡፡ የመንደሩ ነዋሪዎች ሁሌም ጥያቄዎቻቸውን ይዘው እርሳቸው ዘንድ ይሄዳሉ ፡፡ አንድ ቀን አንድ ገበሬ ወደ ጠቢቡ ሽማግሌ መጥቶ ግራ በተጋባ ድምፀት ” እባክዎ ይርዱኝ ፡፡ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነኝ ፡፡ በሬዬ ሞተ ስለዚህም የማርስበት እንሰሳ የለኝም። ከዚህ የከፋ ምን ሊሆን ይችላል?›› ይላቸዋል።
ጠቢቡ ሽማግሌ በእርጋታ “ከዚህ የከፋ ነገር ሊኖርም ላይኖርም ይችላል››ብለው ይመልሱለታል ፡፡ እሱም በጥድፊያ ወደ ሰፈሩ ተመልሶ ለጎረቤቶቹ ሽማግሌው አብዷል፤ ከዚህ የባሰ ነገር ምን ሊኖር ይችላል? እንዴት ይህንን ማወቅ ይሳናቸዋል? ሲል ይገልጽላቸዋል።
በነጋታው ገበሬው እርሻ ውስጥ አንድ ፈረስ ይመለ ከታል። ምንም በሬ ስላልነበረው በፈረሱ ባርስስ? የሚል ሀሳብ ይመጣለታል ፡፡ ከዚያ ፈረሱን ጠምዶ ማረስ ይጀምራል። እርሻ እንደዛን ቀን ቀሎት አያውቅም ፡፡ በሚገባ ሲያርስ ዋለ።
አሁን ደግሞ ጠቢቡን ሽማግሌ ይቅርታ ለመጠየቅ ሄደ። ልክ ብለው ነበር ፡፡ በሬን ማጣት የመጨረሻው አስከፊ ነገር አይደለም ፡፡ እንዲያውም በረከት ነው ፡፡ በሬዬ ባይጠፋ ኖሮ ፈረስ አላገኝም ነበር ፡፡ እንዲያውም በሬዬ መሞቱ በጣም ጥሩ ነገር ነው አይደል?” አላቸው ።
ሽማግሌው በተረጋጋ ድምፀት አሁንም ምናልባት ሊሆን ይችላል፤ ምናልባት ላይሆንም ይችላል ብለው መለሱለት። ገበሬው እኝህ ሰው አእምሯቸውን ስተዋል ብሎ አሰበ። ይሁንና በቀጣይ የሚፈጠረውን አላወ ቀም።
ከጥቂት ቀናት በኋላ የገበሬው ልጅ ፈረሱን እየጋለበ ይወድቅና እግሩ ይሰበራል፡፡ እርሻ ላይ ማን ያግዘኛል? ብሎ ይጨነቅና ገበሬው ሽማግሌው ዘንድ ፈረስ ማግኘቴ ምርጥ ነገር እንዳልነበረ እንዴት አወቁ? ልጄ ፈረሱን ሲጋልብ እግሩ ተሰብሯል፤ እርሻ ላይም አያግዘኝም፤ ይሄ በእርግጠኝነት እጅግ አስከፊ ነገር ነው፤ በዚህስ ይስማማሉ ?ይላቸዋል ፡፡
ሽማግሌው ግን አሁንም ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሁሉ በእርጋታ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል ብለው ይመልሱ ለታል። አሁንስ መሳሳታቸው እርግጥ ነው! ብሎ በንዴት ጥሏቸው ይሄዳል ፡፡
በነጋታው በመንደራቸው ጦርነት ታውጆ ወታደሮች አቋማቸው ብቁ የሚመስሉ ወጣቶችን በግዳጅ ሰብስበው ይዘው ሄዱ ። ከመንደራቸው የቀረው የገበሬው ልጅ ብቻ ሆነ ።
ከዚህ ታሪክ ትልቅ ትምህርት እናገኛለን። በእውነታው ዓለም ቀጣይ የሚከሰተውን ነገር ማወቅ አንች ልም። የምናውቅ ይመስለናል እንጂ አናውቅም። ቀጣይ ይፈጠራሉ ብለን የምንሰጋቸውን ነገሮች በአእምሯችን ውስጥ እናሰላስላቸዋለን፣ እንጨናነቅባቸዋለን ። ብዙ ጊዜ እንሳሳታለን። ተረጋግተን ነገሮችን ለመቀበል ከተዘጋጀን ግን ሁሉ ይቀላል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2013