እየሩስ አበራ
በአሁን ወቅት በስፋት እየታየ ያለው ጥራዝ ነጠቅ እውቀትን ተመርኩዞ መወዛወዝ በብዙዎች ዘንድ እየተንሠራፋ መሆኑ ይስተዋላል። እኔ ብቻ አዋቂ፤ እውቀት ከኔ ወዲያ ላሣር ባዮች እየተበራከቱ ነው። አወቅኩ ያሉትን ነገር ከሥሩ አያውቁትም፤ ብቻ ጫፍ ይዘው በሚፈልጉት መንገድ ተርጉመውና ተንትነው ለሌሎች የሚያስተጋቡ እጅግ በርካቶች ሆነዋል። ነጠላ ሃሳብ አንጠልጥለው ስለምንም ነገር ግድ ሳይሰጣቸውና ሳይጨነቁ በየማህበራዊ ሚዲያው እንደፈለጋቸው የአሰቡትን ጽፈው ሌላው እንዲያነብላቸው እየጋበዙ የአንባቢውን ቀልብ ለመሳብ የሚጣጣሩ የዚያውን ያህል እጅግ ብዙ ናቸው ።
የእነርሱ ሃሳብ ከፍ ብሎ እይታቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ በማድረግ አመለካከታቸውን በሌላው ላይ በማጋባት ለማደናገር የሚጥሩና የሚፍጨረጨሩም እንዲሁ። ሊያስተላልፉ የፈለጉት ነገር ምንም ይሁን ምንም ግድ ሳይሰጣቸውና ቀጥሎ ለሚመጣው ነገር ቅንጣት ያህል ማሰብ ሳያስፈልጋቸው በቀደዱት ቦይ እንደፈለጋቸው የሚፈሱላቸውም ሞልተዋል። የሚጽፉት ሆነ የሚሰጡት መረጃ ምንነት በሚገባ ለማጤን የማይፍልጉ፤ ግድየለሾች እነሱም ተከትለው ያልተጣራ ወሬውን ይነዛሉ።
ስለሀገር ሆነ ስለግለሰብ የፈለጉትንና የመጣላቸውን ሃሳብ እንደወረደ ያሰፍራሉ።ምን ለምን ሆነ ? በምንስ ምክንያት ሆነ የሚለው ጥያቄ መጠየቅ የማይፈልጉ በግምትና በይሆናል ብቻ ታጥረው ምክንያታዊነት ያልታከለበት ሃሳብ የሚያሰፍሩ፤ የፈለጉትን በፈለጉት ጊዜና ሁኔታ ላይ ተመርኩዘው ያብጠለጥላሉ። እውነት የሆነን እውነት እንዳልሆነ፤ ውሸት የሆነ ደግሞ በተቃራኒው እውነት አስመስሎ የማቅረብ አባዜ የተጠናወታቸው የትየለሌ መሆናቸውን እያየን ነው። የሚያዩትን እውነት የማያምኑ ፤ የሰሙትን ለማረጋገጥ የማይሞክሩ በፈለጉት አቅጣጫ ብቻ የሚጓዙ ምክንያት የለሾች ሆነው ሌላውን ለማደናገር የሚሞክሩ ጥራዝ ነጠቅ እውቀት ያላቸው ተማርን ተመራመርን ባዮች በተጣመመ መንገዳቸው የሚያስከትሉትን ማየት ደግሞ እጅግ ያበሳጫል።
ይህንን እንድል ያስገደደኝ በዕለት ተዕለት የህይወት ውጣ ወረድ ውስጥ የማገኛቸውን ሰዎች ጨምሮ በርካቶች ማለቂያ የሌላቸው የእውር ድንበር ጉዞ ሃሳብ ውስጥ ስለከተተኝ ነው። በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ መገናኛ መስመሮች ላይ ለመጻፍ ብዕራቸውን ያሳረፉ ብዙ ሰዎች አቅጣጫዎችን በመሳት የሚያስተላልፉት መልክት አደገኛ መሆኑን ስለታዘብኩ ነው። ለሀገር የሚበጀውን ከመጠቆም ይልቅ ምንም ነገር ከግንዛቤ ውስጥ ያልከተተ ትችት በማቅረብ እርባና የለሽ የሆነ ጉዳይ በማተኮር ጣትን ሌላው አካል ላይ የመቀሰር አባዜ ብቻ ከተጠናወታቸው ዋል አደር ብሏል።አሁን ግን ከዚህ አለፍ ያለ ይመስላል፡፡
አወቅን ያሉትን ለሌላው ለማካፈል መሽቀዳደሙ ባይከፋም፤ ጫፍ ይዞ ሩጫ ክፋቱ የሚበረታው ውሎ አድሮ ነው።በውል ያላወቁትና ያላጣሩትን መረጃ ልክ እንደሚያወቁ ወይም ከእነሱ በላይ የሚያውቀው ሰው እንደሌለ አድርገው ማቅረብ የብዙዎች መገለጫ ባህሪ እየሆነ መጥቷል። ብዙ ተናግረውም ሆነ ጽፈው፤ በርካታ መረጃዎች፤ በፍጥነት በመልቀቅ ብዙ ተከታዮችን ለማፍራት ካላቸው ጉጉት የመነጨ አገኘነው ያሉትን መረጃ ከለቀቁ በኋላ ለሚመጣው ማንኛውም ነገር ግድ የላቸውም።
የፈለጉትን ለብዙዎች ካጋሩ በኋላ ለሌሎች እድል ለመስጠት ሆነ ሃሳባቸውን ለማደመጥ የማይጨነቁ በዝተዋል። የሌሎች ሃሳብ ካለመቀበል ባሻገር የሰዎችን ንግግር ከአፋቸው በመንጠቅ ነጠላ ሃሳብ መዞ በመውሰድ መተቸት እየተለመደ መጥቷል። የእነሱ ሃሳብ የሁሉም እንዲሆን የሚጥሩ በእነሱ መነጽር ሌላው እንዲያይ የሚፈልጉ፤ በሁሉም ጉዳዮች በሚመለከታቸው በማይመለከታቸውም ገዥ አስተያየትና ሃሳብ በመስጠት የሚቀደማቸው የሌለ የእውቀት ጥግ ላይ የተቀመጡ መስሎአቸው የሚዘባርቁም እንዲሁ ከልክ በላይ እየሆኑ ነው።
በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉት ፈጻሚ የለሽ ቁንጽል ሃሳቦች እየተበራከቱ መምጣት ከሀገር አልፎ የግለሰቦች ህይወት ሳይቀር አደጋ ላይ ለመጣል ያለመ ነው። የአንድን ነገር ጫፍ ይዞ ማራገብ፤ አንድን ክስተት መነሻ አድርጎ በርካታ አሉባልታዎች ማናፈስ፤ አንድ ሰው ከተናገረው ንግግር ውስጥ ቁንጽል ነገሮች በመውስድ በሚፈልጉት መልክ አድርጎ ማስተላለፍ —ወዘተ ተነገረው የማያልቁ ክስተቶች ኃላፊነት በጎደላቸው ሃይ ባይ የለሾች ከሚሰሩት ሥራዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። የሚገርመው ነገር ጉዳዩ ማስተላለፋቸውን እንጂ በዚያ ምክንያት የሚመጣው ጦስ ምንም አለ ብሎ ማሰብ አለመፈለጋቸው ነው። ‹‹ አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል›› እንዲሉት አይነት ተግባር ይዘው የሚናገሩት አያውቁትም።የነገሩ ምንጭ ምንድነው? ከየት መጣ? ለምን ተባለ? የሚለውን ማጣራት ብሎ ነገር አይታሰበም። ለዚህ ነው ዛሬ የተናገሩት ነገ የማይደግሙት፤ እርስ በእርሱ አንዱ ከአንዱ የሚጋጭ መረጃን በየጊዜው የሚናገሩት የአላዋቂነታቸው ብዛቱ የነገሮች ጫፍ ይዞ ብቻ ከእዚያና ከእዚህ የሚረገጡት።
በቅርቡ እንኳን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ ከተናገሩት ንግግሮች በተለይ ትኩረት ተሰጥቶች ማህበራዊ ሚዲያ ለትችት ተሰጥቶ የዋለውንና የከረመውን ጉዳይ ተመልከቱ እስኪ። በቴክኖሎጂ በመታገዝ ከደመና ዝናብ ማዝነብ መቻል ሲናገሩ የታየበት መንገድ እጅግ አስገርሞኛል። በተለይ ተምረናል ከምንል ከኛ ደመናን ማዝነብ እየተለመደ የመጣ የሳይንስ ግኝት መሆኑን አናወቅም ብዬ ለመገመት አልደፍርም።
ይሁን እንጂ ለምን? እንዴት? መቼ? የሚሉት አጋዥ ጥያቄዎች በማቅረብ በማረጋገጥ አገራችን የጀመረችውን አዲስ ምዕራብ ከማበረታታት ይልቅ በተቃራኒው ትችትና ማብጠልጠል የተሄደበት መንገድ ነው የታየው። የሆነው ሆኖ የሚገርመ ግን ደጉ የሀገሬ ህዝብ የተሻለ እውቀት ያለው መሆኑ ነው። እነሱ ግን ከሠሩት ሰህተት ተምረው ከተናገሩ በኋላ እንኳን ይቅርታ ሊጠይቁ ቀርቶ ፀድቁ ቀርቶብኝ በወጉ በኮነነኝ አይነት ዓይነ ደረቅ ሆነው እርፍ ይሉታል።
በነገራችን ላይ ይህንን ሰህተት የሚፈጽሙት ግለሰቦች ብቻ አይደሉም፤ ታዋቂ ሚዲያዎች፤ ድርጅቶች ሁሉንም ተሳታፊ አካላት የሚጨምር ነው። አንዱ የለጠፈው ወደድኩት ብሎ ለራስ መወደድን ከገለፁ በኋላ ለሌላ ማጋራት ወዶት ለሌለው የሚያጋራ ሁሉ የጥፋቱ አካል ነው። ስለሚጽፉትና ስለሚናገሩት ነገር ካላወቁ፤ የሚያውቁትን አካላት መጠየቅ ማንን ገደለ? አወቅን ብሎ በራስ ስሜት ብቻ ታውሮ ሌሎች ላለመቀበል መሞከር የጤና ነው። ለኔ ትክክለኛ ነኝ ብሎ የሚያስብ ስለራሱ ትክክለኛነት እንጂ ስለሌላው አይጨነቅም፤ በፍፁም ማንም አያምንም።
ይህ ሊገነባ የሚችል ሳይሆን ሊያጠፋን የሚችል ልማድ እርግፍ አድርገን መተው ለነገ የሚባል ነገር አይደለም። ያለፈንበት የጠመመ መንገድ በማቃናት አገራችን ከኛ የምትፈልገው ባናደርግ እንኳን የቻልነው ባለመንፈግ የድርሻችንን መወጣት አለብን። ቸር ይግጠመን::
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2013