ታምራት ተስፋዬ
በዓለም የሜትሮሎጂ ድርጊት የሚታወቁ ከ50 በላይ የዝናብ ማበልጸጊያ መንገዶች እንዳሉ የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ ። ከእነዚህ መካከልም የተለያዩ ኬሚካሎችን በመጠቀም ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ ‹‹የክላውድ ሲዲንግ›› አንዱ ነው።ይሕ ዘዴ እውን መሆን ከጀመረ ከሰባ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። የመጀመሪያው የክላውድ ሲዲንግ ሙከራ እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1946 በአሜሪካዊው ኬሚስትና ሜትሮሎጂስት ቪንሰንት ሻፈር እንደተከናወነ ይነገራል።
በተፈጥሯዊ ሂደት ደመና የተለያዩ ዑደቶችን አልፎ ዝናብ ይሆናል ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም ፣ በአንድ ደመና ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወደ ዝናብ ያልተቀየሩ የዝናብ ነጠብጣቦችን ይኖራሉ።እነዚያም መጠናቸው አድጎ በመሬት ስበት ዝናብ ሆነው እንዲመጡ መሰባሰብ አለባቸው። ዑደቱ ተጠናቆ ወደ ዝናብ ለመቀየር በቂ ንጥረ ነገርም ያስፈልገዋል። ይህ ካልሆነ ዝናብ አይኖርም።
የክላውድ ሲዲንግ ሳይንስም አስፈላጊውን ተጨማሪ ንጥረ ነገር በመጨመር በዋናነት እርጥበት ይዞ ያለውን ደመና ወደ ዝናብ የሚቀይር ነው። የጨው ዝርያ ያላቸው እንደ ሶዲየም፣ ፖታሺየም፣ ክሎራይድና ናኖ ቴክኖሎጂ ለዚህ ተግባር ይውላሉ ። እነዚህን ንጥረ ነገሮች ወደ ደመና ለማድረስ የተለያዩ አገራት የተለያዩ ዘዴዎች ይጠቀማሉ።ለምሳሌም ቻይና ሮኬት ስትጠቀም ኢራን ደግሞ በሰው አልባ አውሮፕላኖች (በድሮን) ወደ ደመና ትደርሳለች።
እንደ የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት መረጃ ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂን ከ70 በላይ አገራት እየተጠቀሙ ይገኛሉ ። በተለይ ቻይና የገዘፈ ስም ያላት ሲሆን እስራኤልም ጨምሮ ሌሎች ምዕራባውያን አገራትም ቴክኖሎጂን ይጠቀማሉ ። ቻይና በተለይም እኤአ በ2008 ባዘጋጀችው የቤጂንግ ኦሎምፒክ በተመረጡ ቀናት ከደመና ዝናብ ማዝነብን ችላ አሳይታለች ። በዚህ ቴክኖሎጂም በዓመት እስከ 55 ቢሊየን ቶን ተጨማሪ ውሃ ታገኛለች ።
ዝናብ ማግኘት ፈታኝ ከሆነባቸው አገራት አንዷ የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስም በቴክኖሎጂው ትግበራ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን መቋደስ ችላለች።ከ 15 እስከ 30 በመቶ ተጨማሪ ዝናብ ታገኛለች።በአህጉራችን አፍሪካም የኒጀር፣ ማሊ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሞሮኮ ያሉ አገራት ቴክኖሎጂውን በመተግበር በቀዳሚነት ስማቸው ይጠቀሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በስድስተኛው ዙር 11ኛው የተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በጎጃም እና በሸዋ አካባቢዎች በሰው ሠራሽ ቴክኖሎጂ አማካይነት ዝናብ ማዝነብ መቻሉን በሙከራ መረጋገጡን አስታውቀዋል። ከሕዝብ ቁጥር እና የእርሻ መሬት ፍላጎት መጨመር ጋር በተያያዘ ደረቅ አካባቢዎችን ለም እና ምርታማ ለማድረግ ቴክኖሎጂው እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ፣ኢትዮጵያ ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ቴክኖሎጂ የሙከራ ተግባር እያከናወነች መሆኑን አረጋግጠዋል ። ተግባሩንም የምታከናውነውም ከተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ መንግስት እና የሜትሮሎጂ ማዕከል ጋር በመተባበር ባገኘችው የቴክኖሎጂና የባለሙያዎች ድጋፍ እንደሆነ መሆኑን ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያን በመሳሰሉ አገራት የዝናብ እጥረት እና ድርቅ ለመከላከል ተጨማሪ የቴክኖሎጂ አማራጮችን መፈለግን እና መተግበር ያስፈልጋል። ኢትዮጵያም ይህን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሯ በተለይ በውሃ አጠር አካባቢዎች ከፊል አርብቶ አደሮች እንደአጠቃላይም የግብርናውን ዘርፍ ለማጎልበት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ያስረዳሉ ። ‹‹በተለይ የበጋ ስንዴ ልማቶችን በማስፋት ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ያስችላል›› ብለዋል።ቴክኖሎጂውን በመጠቀምም የዝናብ መጠንን ከ 30 እስከ 35 በመቶ ማሳደግ እንደሚቻልም አስረድተዋል።
ይህንን ሥራ በዋናነት የሚያስተባብረውና የሚመራው ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲሆን የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ፣ብሔራዊ ሜትሮሎጂ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋም፣ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየተሳተፉበት ይገኛሉ።በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜያት ሲሞከር የቆው የቴክኖሎጂው አተገባበር በስፋት የሚገኙትን የሶዲየም ክሎራይድ እና ፖታሺየም ክሎራይድ ድብልቅ (ሃይድሮስኮፒክስ) በመጠቀም በአውሮፕላን የሚረጨው አተገባበር መሆኑ ታውቋል።
ቴክኖሎጂው በሀገር ደረጃ ምን ምን ጉዳይ ላይ ሊተገበር እንደሚችል መጠናቱን እና በዋጋ ደረጃ አነስተኛ የሚባለው መሆኑን ተመላክቷል። ቴክኖሎጂን ለመተግበር የሚመቹ አካባቢዎችም በተለያዩ መስፈርቶች አማካይነት እንደሚመረጡም ታውቋል ። ለኬሚካል ርጭቱ በዋነኝነት የሚያስፈልጉት የሶዲየም ክሎራይድ እና ፖታሺየም ክሎራይድ ንጥረ ነገሮች በኢትዮጵያ እንደልብ መገኘታቸው ቴክኖሎጂውን ይበልጥ ለማስፋፋት እድል እንደሚሰጥ ተገልጿል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሚሰጡ ምሁራንም፣ኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂው ልታገኘው የምትችለው ሁለተናዊ ጥቅም በተለያየ ፈርጅ አስቀምጠውታል ። ቴክኖሎጂው የግድብ ስራዎች ላይ ውሃን በፍጥነት ለመሙላት እና ሌሎች የግብርና እንቅስቃሴዎች ለማፋጠን፣ ዝናብ አጠር በሆኑ ቦታዎች የውሃ ሃብትን ለማስፋት ትልቅ አቅምን እንደሚፈጥር እንደሚያግዝ ያስረዳሉ ። እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት የዝናብ ውሃን መጠበቅ ሳያስፈልግ በፍጥነት ለመሙላት እንደሚያግዝም ሳይገልፁ አላለፉም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2013