“ሕዝቡ የጤና ምርምሮችንና ክትባቶችን የፈራው ፈዋሽነታቸው ባልተረጋገጡ መድኃኒቶች ጉዳት በመድረሱ ነው፡፡›› ተሳታፊዎች
‹‹የሚያጠራጥር እና ሀሰተኛ መረጃ እየተሰራጨ በክትባቶቹ ላይ ጥላቻ ፈጥሮ በጥርጣሬ የሰው ሕይወት እና ንብረት ጠፍቷል።›› አቶ ንጉሡ ጥላሁን
‹‹ክትባትን የሚያስቆም የተሳሳተ መረጃ ለማንወጣው ወረርሽኝ ይዳርገናል፡፡›› የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ
የጦማርያን እና የጤና ጥበቃ ቢሮ በባሕር ዳር ተወያይተዋል፡፡ በውይይቱ ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄና አስተያዬቶችን በጤናው ዘርፍ ዙሪያ አንስተዋል፡፡ ‹‹የበላችው ያስታውካታል፤ በላይ በላይ ያጎርሷታል›› በሚል ተረት ንግግራቸውን የጀመሩት አንድ ተሳታፊ ‹‹የአማራ ክልል ዛሬም ዓለም በረሳው እከክ እየታመሰ ነው›› ብለዋል፡፡
የክልሉ ጤና ፖለቲካዊ ጫና ተደርጎበት የመድኃኒት እጥረት መከሰቱና የሚመጡ መድኃኒቶች አስፈላጊነት እና ፈዋሽነት ዝቅተኛ መሆንም በተወያዮች ጠንካራ አስተያዬቶች የተሰጡባቸው ናቸው፡፡
‹‹ሕዝቡ የጤና ምርምሮችንና ክትባቶችን የፈራው ፈዋሽነታቸው ባልተረጋገጡ መድኃኒቶች ጉዳት በመድረሱ ነው›› ብለዋል ጦማርያኑ በውይይት መድረኩ። የፌድራል እና የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ትኩረት ባለማድረጋቸው ጥርጣሬ መንገሡም ተነስቷል።
በተሳሳተ መረጃ ትክክለኛ ክትባቶች ሳይሰጡ ዜጎች እንዲሞቱ ማድረግ እንደማይገባ ያሳሰቡት ጦማርያኑ ይልቁንም የመድኃኒቶችን አመጣጥ እና ፈዋሽነት አስቀድሞ በማረጋገጥ ወደ ኅብረተሰቡ ማድረስ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የጤና ባለሞያዎች በማኅበራዊ ድረ-ገፅ ትክክለኛ መረጃ መስጠት ቢጀምሩ ግምታዊ መረጃዎችን መቀነስ እንደሚችሉም ጦማርያኑ አስተያዬቶችን ሰንዝረዋል፡፡
‹‹የሚያጠራጥር እና ሀሰተኛ መረጃ እየተሰራጨ በክትባቶቹ ላይ ጥላቻ ፈጥሮ በጥርጣሬ የሰው ሕይወት እና ንብረት ጠፍቷል›› ያሉት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው፡፡
እንደ አቶ ንጉሡ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚሠራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ምክንያት የጤና ሥራው ችግር ገጥሞታል፤ በክትባቶቹ ላይ የሚያጠራጥር እና ሀሰተኛ መረጃ እየተሰራጨና ጥላቻ እየተፈጠረ በጥርጣሬ የሰው ሕይወት እና ንብረት ጠፍቷል።
ችግሮቹ የተፈጠሩት የሕዝቡን አቅም ወደአንድነት ማምጣት ስላልተቻለ እንደሆነና ለሕዝቡ ሲባል ‹‹እንትና ማር ቢሰጠኝም አልበላም›› የሚል አመለካከት ካለ ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የግል ድርቅና ሰለሚሆን ተቀባይነት እንደሌለውም አቶ ንጉሡ አብራርተዋል።
‹‹አንድ በሚያደርገን የሕዝብ ጥቅም መለያዬት የለብንም። ጦማርያን በጤናው ዘርፍ ያለሞያችሁ ‹ይህ ትክክል አይደለም› ከማለት ይልቅ ባለሙያ አጣቅሰው ስህተቱ እንዲታረም፤ ቀናውም እንዲጠናከር የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባል›› ሲሉም አቶ ንጉሡ አሳስበዋል።
‹‹ኅብረተሰቡን የሚጎዳ ተቆርቋሪነት የለም፤ ተቆርቋሪ በመምሰል ክትባትን የሚያስቆም የተሳሳተ መረጃ ለማንወጣው ወረርሽኝ ይዳርገናል›› ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶ.ር አበባው ገበየሁ ናቸው፡፡
አብመድ እንደዘገበው በጤናው ዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ጥናት መደረጉን የገለጹት ዶ.ር አበባው ‹‹የመድኃኒት ጥራት ቁጥጥሩ በቢሮው ተጠናክሮ ይቀጥላል›› ብለዋል።
በውይይቱ በክልሉ ክትባቶች እንዲሰጡ በጋራ እንደሚሠሩ ከጦማሪዎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል። “ለሰው ልጅ ከውኃ ቀጥሎ ፍቱን መድኃኒት ክትባት በመሆኑ ክትባቶቹ እንዲሰጡ በጋራ እንሠራለን›› ብለዋል የውይይቱ ተሳታፊዎች በውይይቱ ማብቂያ ላይ በሰጡት አስተያዬት።