ራስወርቅ ሙሉጌታ
በምድር ላይ የብዙዎች እምቅ ጉልበትና ብቃት ታምቆ በዚያው እንዲቀርና እንዳይወጣ ከሚያደርጉ ቀዳሚ ምክንያቶች መካከል ትኩረት ማጣት አንዱ ነው። ትኩረት ያጣ ሰው ሃሳቡን፣ ገንዘቡን፣ ስሜቱን፣ ጊዜውንና ማንነቱን ጭምር መሰብሰብ ሲያቅተው ይስተዋላል። ለመሆኑ የትኩረት ማጣት እንዴት ሊከሰት ይችላል? በምን አይነት መልኩስ ይህንን ችግር መቅረፍ እንችላለን? ስንል የማህበራዊ ልማትና አመራር ባለሙያ ከሆኑትና በቲቪ ዘጠኝ የክሊፍ ሞቲቬሽን ወይም አፋፍ ለመድረስ ዝግጅት አዘጋጅና አቅራቢ አቶ ዘላለም ይትባረክን አነጋግረን የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አጠናክረን አቅርበነዋል።
ትኩረት ማለት የመጨረሻውን ግባችንን ወይም ኢላማ በማድረግ በመንገድ ያሉትን ሁሉ ችላ ብሎ በአጽንኦት ማዬት የመቻል ክህሎት ነው። ልንይዘው ወይም ልንደርስበት አቅደን ያሰብነውን ነጥሎ መመልከት መቻል እንደማለት ነው። ወይም እግረ-መንገድን በመተው፤ በተጓዳኝ ያሉትን በመርሳት በሙሉ አቅምና ብቃት ላሰብነው ብቻ የመኖር ጥበብም ነው። ስለዚህ ብዙ ወጥነን ጥቂት ካከናወንን ወይም ብዙ አቅደንና ጀምረን የቀጠልናቸው ነገሮች ግን ጥቂት ከሆኑ የትኩረት ችግር ሊኖርብን ይችላል ማለት ነው።
የትኩረት ሃይል
“በአዕምሮኣችን መጨረሻው የሚታወቅ ግብ ማስቀመጥ” በማለት ናፖሊዮን ሒል “ራስን መሸጥ” በሚለው መጽሐፉ ይተረጉመዋል። ለስኬት የሚበቁ ሰዎች የጋራ ባህሪ ተደርጎ የሚወሰደው ግባቸውን የሚጀምሩት የታቀደ መድረሻ በማስቀመጥ መሆኑ ነው። ውድቀት የገጠማቸውን 25 ሺህ ሰዎች መሰረት በማድረግ በተሰራ ትንተና ሁሉም አዕምሮኣቸውን መከተል የማይችሉና ትኩረት የማይሰጡ መሆናቸው ተረጋግጧል። ይህም ሆኖ የውድቀት መሰረት የሆኑ ሰላሳ ዋና ምክንያቶችን ትኩረት በመስጠት መቆጣጠር ወይም ማጥፋት ይቻላል። ለዚህም በቅደሚያ ትኩረት ስናደርግ ያለንን ማወቅ፣ ማደራጀት (መሰብሰብ)፣ ቅደም ተከተል ማስያዝ ወዘተ ከማስቻሉ ባለፈ ተጨማሪ ብቃት፣ አቅምና ብልሃትን ያስገኝልናል።
የስሜታችን መዝጊያና መክፈቻ መቆጣጠሪያ ቁልፍ ሃሳባችን ሲሆን ሃሳባችን ደግሞ ስሜታችንን ማስተዳደር የሚችልበትን አቅም የሚያገኘው ትኩረት ከማድረግ ነው። በስሜት ህዋሳቶቻችን ትኩረት ማድረግ ስንችል በሃሳባችን ምክንያታዊና እውቀታዊ በማድረግ ስሜታችንን ማስተዳደር እንችላለን። በጩኸት ውስጥ በፀጥታ፣ በረብሻ ውስጥ ሰላም ወይም በጨለማ ውስጥ በብርሃን ወዘተ የመሆን አቅማችን ሁሉ በትኩረት ማድረግ ውስጥ የምንጨብጠው ነው። ትኩረት ማድረግ ስሜታችንን መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ያለንን መቆጣጠርና ማስተዳደር ከመቻል አልፎ የሌለንም እንዲኖረን የሚያስችል ብልሃትም ነው።
በዚህም ትኩረት የአካሎቻችን ቁልፍ ነው ያልንበት ምክንያት ምላስም የሚያጣጥመው፣ አይንም የሚያየው ወዘተ “ልብ አልኩ” በተለምዶ የምንለው ወይም ስናተኩርበት ነው። ወይም ሳናይ ያዬነው፣ ሳንሰማ የምንሰማው ወይም ሳንቀምስ የምናጣጥመው ሁሉ ትኩረት በማድረግ ልምዳችን ነው። እዚህ ላይ “ልብ በሉ፤ … ልብ ግዙ…” ፤ “…ልብ አድርጉ…” የሚሉትን አባባሎች መገንዘብ ይጠበቃል።
በተጨማሪ በትኩረት ሃሳብ የምናዬው እርቀት በአካላችን፣ በስሜት ህዋሳችን ከምናዬው ሩቅ ነው። በእርግጥም ትኩረት ሰውን ከአካላዊ ገደብ ነፃ በማድረግ በዕዝነ-ሃሳብ ያለገደብ እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል። ማለትም በትኩረት ሩቅ ረቂቁን ማዬት ሲቻል፤ ያለትኩረት (ከትኩረት ውጭ) ግዙፍን አጠገባችን ያለውን ለማዬትም ይከብዳል ማለት ነው። ስለዚህ ትኩረት ሰው አካላዊ ህዋሳቱን ያለገደብ የሚጠቀምበት ልዕልና ይባላል።
ሰው ከሰው ያለው መበላለጥ በሁሉም ዘርፍ (በተለይ በሥራ) ዋነኛ ምክንያት ትኩረት ማድረግ ልምድ መኖር ወይም ያለመኖር ነው። ትኩረት የሚያደርግ ያለውን አደራጅቶ አበልጽጎ የሚፈልገውን በጊዜ መጨበጥ የሚችል ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዱ ብዙ የሚበልጥ እያለው ሲጠቀምበት አይታይም። ማለትም ሁለት በተመሳሳይ ደረጃና ሁኔታ ላይ ያሉ ሰዎች እኩል ሥራና እኩል ሰዓት ሰጥተናቸው አንዱ ቀድሞ የሚጨርስበትና ሌላኛው የማይጨርስበት ወይንም የሚዘገይበት ምክንያት በአብዛኛው ትኩረት የማድረግ ልዩነት የሚፈጥረው ሆኖ እናገኘዋለን።
ትኩረት እንድናጣ የሚያደርጉን መሰረታዊ ምክንያቶች
1. ፍርሃት፣ ጥርጣሬ፣ ሥጋት፣ ጭንቀት እና ጉጉት ።
2. የማንጠቀምበትን ብዛት ያለው መረጃ መሰብሰብ።
3. ሥራዎቻችን ቅደም ተከተል ማስያዝ አለመቻል።
4. የሚረብሹንን ማስወገድ ወይም መቀነስ አለመቻል ከቀዳሚዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
ሁለተኛው ክፍል ሳምንት ይቀጥላል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2013