ለምለም መንግሥቱ
ማረፊያ መኝታ በያዝኩበት አካባቢ ያየኋት ሻይ፣ ቡና እና ቁርስ ቤት መንገድ ዳር መሆኗ ብቻ ሳይሆን፤ የቤቷ ጽዱ መሆን ትኩረቴን ስቦታል። ቤቷ ፈጣን ምግብ የሚቀርብባት መሆኑም ከወንበሮቹ አቀማመጥና ቤቷም አነስተኛ መሆኗ ግምቴን ከፍ አድርጎታል። ከሌሎች ተጓዦች ጋር በመሆን በማግሥቱ በጠዋት በዚህች ቤት ቁርስ በልተን ወደ ሥራችን ለመሄድ በማስጠንቀቂያ ጭምር ማምሻችን ላይ ወስነን ተለያይተናል።
ማስጠንቀቂያ መስጠታችን ያለምክንያት አልነበረም። በሁለት ቀን ቆይታ እንደታዘብነው ምግብ ቤቶችም ሆኑ ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት በጠዋት ሥራ የመግባት ልምድ የላቸውም ። በሌላ ምግብ ቤት ቁርስ እስኪሰራ ጠብቀን በልተን ስለነበር በተመሳሳይ እንዳይገጥመን በጠዋት ገብተው ቁርስ እንዲያዘጋጁልን አንድ ሰአት ላይ ተመግበን እንደምንወጣ ነግረናቸው ነበር፤ ያንን ያደረግነው ቀድመን ማስጠንቀቂያ የሰጠነው ያለፈው እንዳይደገም ነበር ።
በተባባልነው መሠረት ቁርስ ለመብላት ተያይዘን ሄድን። እኛ ስንደርስ ለአንድ ሰአት ቁርስ ሊያደርሱ ቀርቶ ቤቱ ገና መከፈቱ ነበር ። የለመዱት ሆኖባቸው ሳይሆን አይቀርም በፊታቸው ላይ ንቃት አይስተዋልም ። ደስተኞችም አይመስሉም ። እኛ ተጠቃሚዎች ከውጭ ሆነን እነርሱ ደግሞ ከውስጥ ሆነው እየተያየን ቁርስ የሚያዘጋጁት ድስት በከሰል ምድጃ ላይ ጥደው እያርገበገቡ ነበር ። ከፊት ለፊታችን በደንብ ባልተያያዘ እሳት በከሰል እያርገበገቡ መሥራታቸውና የምግቡ አለመድረስ ምንም አልመሰላቸውም።
ማብሰያ ድስታቸው ቤቱን የሚመጥን አልነበረም። የኤሌክትሪክ ማብሰያ(ስቶቭ) አለመጠቀማቸው የኃይል አቅርቦት ችግር ይሆናል ብለን በመጠራጠር አልፈነው ነበር ። ነገር ግን አካባቢው ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል አልነበረም ለማለት ይቸግራል። እንደምንም የታዘዘው ቁርስ ከመጣልን በኋላ የሚጠጣ ሻይ አዘዘን። እሱም ከብዙ ቆይታ በኋላ መጣልን ። ነገር ግን አምስት ስለነበርን በቂ የሻይ መጠጫ ብርጭቆም አልነበረም።
ነገሩን በቀልድ ከመውሰድ ሌላ መናደዱ ትርጉም አልነበረውም ። መስተንግዶ ከተባለ ተስተናግደን ሂሳብ ከፍለን ወጣን ። አማራጭ ስላልነበረን በማግሥቱም እዚሁ ቤት ለቁርስ ተመለስን ። እንደተለመደው ከሰል ማርገብገብ እስኪቀረን ድረስ ኩሽና ገብተን እንዲያፈጥኑልን ለመንን ። ሻይማ የሚታሰብ አልሆነም ። የሻይ ይቅረብልን ጥያቄ ስናቀርብ የተባልነው ‹‹ዛሬማ ሻይ አይደርስም›› የሚል ነበር ። ነገሩ ግራ ያጋባል ። ሁሉም ገና ሰርተው ያልጠገቡ ወጣቶች ናቸው ። በወጣትነት እድሜያቸው የሥራ ትጋት አለማሳየታቸው አስገርሞኛል። አስር ሰው የማይሞላ ደንበኛ በአግባቡ ማስተናገድ ካልቻሉ ለምን ንግድ ውስጥ ገቡ የሚል ጥያቄ ይፈጥራል።
መቼም ቤቱን ተከራይተው ሊሆን ይችላል። በዚህ ሁኔታ ሰርተው በየወሩ የሚጠበቅባቸውን ክፍያ እንዴት ይፈጽማሉ ። በግላቸው ለንግድ የሰሩት ነው እንኳን ቢባል ለግንባታው ያወጡትን ወጭ ለመመለስ አይጨነቁም? ዛሬ ሰርተው ከሚገኙበት ደረጃ ከፍ ለማለት ራዕይ የላቸውም? እነዚህ ሁሉ በአዕምሮዬ ይመላለሱ ነበር። ጠጋ ብዬ ስላልጠየኳቸው እንጂ እንዲህ በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በጋራ መንቀሳቀስ የተለመደ ስለሆነ የሥራ ትጋቱ እኩል አይሆንም ። አንዱ ሌላውን እያዩ በፉክክር ወደኋላ ከተባለ ውጤታማ አይሆኑም ። የንግድ ሥራ እንቅልፍ አይወድም ። ፍጥነት፣ ተወዳዳሪ መሆንና በልጦ መገኘት ይፈልጋል ። ይህ ውጤት የሚገኘው ደግሞ ደንበኛን በአግባቡ በመያዝና ፍላጎት በማክበር ነው።
አገልግሎት ፈልገው ወደ አንድ ተቋም ሲገቡ ከመልካም ፈገግታ ጋር ጥሩ መስተንግዶ ሁሉም የሚጠብቀው ብቻ ሳይሆን የሚፈልገው ነው ። ከነአባባሉስ ደንበኛ ንጉሥ ነው ። ከፍትፍቱ ፊቱ ይባል የለ ። በተለይ ደግሞ ምግብ ፈልገው ጎራ በሚሉባቸው ሥፍራዎች እነዚህን መስተንግዶዎች በተሟላ ሁኔታ ይፈልጋሉ ። ለመመገብ ጎራ የሚሉበት የመስተንግዶ መስጫ አገልግሎቱ የተሻለ እንዲሆን ይጠብቃሉ ። ለሥራ ተቻኩለው ከሆነ ደግሞ አገልግሎቱ ፈጣን ቢሆን ይመርጣሉ።
ነገሩን አዋዝቼ አቀረብኩት እንጂ ያየሁት ነገር የሥራ ባህላችን መፈተሸ እንዳለበት የሚያመለክት ነው ። በትንሽ ነገር መርካት ከተፈጠረና የበለጠ ሰርቶ ሌሎችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር ካልተሞከረ ‹‹ንግድ ቤት ከፍቻለሁ›› ወይም ‹‹ተደራጅቼ እየሰራሁ ነው›› ማለቱ ትርጉም ያጣል። በአሁኑ ጊዜ ተምሮ የትምህርት ውጤት የያዘውም፤ በተለያየ ምክንያት ከትምህርት ገበታ የራቀውም እኩል ሥራ ፈላጊ ነው። ሰርቶ ያልደከመ ጉልበት ያለሥራ ሲቀመጥ ለቤተሰብም፣ ለሀገርም ሸክም ይሆናል ። ወላጆች ደክመው ካሳደጓቸው ልጆቻቸው ውለታ ብቻ ሳይሆን፣ ትልቅ ነገር ላይ ደርሰውላቸው ማየትም ይመኛሉ። በተገላቢጦሽ መልሰው የእነርሱን እጅ ጠባቂ ሲሆኑ ግን ሀዘናቸው የከፋ ይሆናል ። በዚህ ከቀጠለ ከቤተሰብ አልፎ አገርንም ይጎዳል ።
መንግሥት በተለይ ለሴቶችና ለወጣቶች በተለየ ሁኔታ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ያለው ሥራ በማጣት ለሱስና አላስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች መጋለጥ እንዳይኖር፣ ጊዜያቸውም እንዳይባክን ከማሰብ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ካለው ኃላፊነት ጭምር ነው። በመንግሥት ድጋፍም ይሁን በግል ጥረት የሚፈጠር ሥራ በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ ከትርፉ ኪሳራው ያመዝናል።
ሥራ አጥ የበዛባት ሀገር ፈተናው ብዙ ነው ። የሥራ ዕድል ሲፈጠር በንቃት አለመሳተፍ እና ስንፍና ብቻ ሳይሆን፤ አለመረጋጋት ሲፈጠር ወጣቶች በአጥፊ ኃይሎች ተገፋፍተው ነገ ለእነርሱ ሊጠቅም የሚችል ብዙ መዋለንዋይ የፈሰሰበትንና ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ተቋማትን እስከማውደም ይደርሳሉ፤ ሲያደርሱም አይተናል። የሰው ደም በከንቱ ፈሷል ። ህይወት ጠፍቷል። የአካልና የንብረት ጉዳቱም ከፍተኛ ነበር ። በተለይ በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ ጥላቻ ተነዝቷል ። የቤተሰብ፣ የወገን፣ የሀገር ፍቅር እንዳይኖራቸው ተደርገዋል ። የሰው ልጅ ትልቁ ሥራው ልማትና ዕድገት መሆን ሲገባው ሀገር ቁልቁል የምትሄድበት መንገድ እንዲመረጥ ሆኗል ። የዚህ ሁሉ ማጠንጠኛው ደግሞ ሥራ አጥነት ነው ። በሥራ ላይ ያሉት ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር ካልቻሉና ትጋታቸው ለሌሎች አርአያ በሚሆን መልኩ ማስተላለፍ ካልቻሉ ሥራ መፍጠሩ ብቻውን ዋጋ የለውም ።
ክፍተቶቹ ብዙ ቢሆኑም በመንግሥት በኩል ሥራ የመፍጠሩ ጥረት አሁንም አላቋረጠም። ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2017 ዓ.ም ለ14 ሚሊዮን፣ በ2022 ዓ.ም ደግሞ ለ20 ሚሊየን ዜጎች በተለያየ ዘርፍ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል። ኮሚሽኑ ኃላፊነቶቹንም አስቀምጧል ። ማስተባበር፣ መረጃ መስጠት፣ ሀብት ማሰባሰብ፣ ጠቃሚ ፖሊሲ ሥራ ላይ እንዲውልና መደገፍ ከተግባራቱ መካከል ይጠቀሳሉ ። ይህ የሚያጓጓም የሚያስደስትም ተግባር ነው ። ነገር ግን ኮሚሽኑም ሆነ ሌላው የሚመለከተው አካል እንደ ሀገር የሥራ ባህል ላይም ፍተሻ በማድረግ የሥራ ባህል እንዲያድግ ማስተማሩና ግንዛቤ መፍጠሩ ላይም ጎን ለጎን ማስኬድ ይገባል ።
እኔ ለጊዜው ስሙን በማልጠቅስላችሁ አካባቢ በነበርኩበት ጊዜ የታዘብኩትን ነገርኳችሁ እንጂ በተለያየ አካባቢ ተመሳሳይ ትዝብት እንደሚኖር እገምታለሁ ። አለ ብዬ መግለጽ እችላለሁ ። ነገ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ሆና ለዜጎችዋ ጠቃሚ የሆነች ሀገር እንድትኖረን ከፈለግን መድከማችን ግድ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 21/2013